የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመደበኛ ሴሚናሪና በትርጓሜ መጻሕፍት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ

0236

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የ6ኛ ዓመት የብሉያት ትርጓሜ ተመራቂ ዕጩ መምህራን ብዛት ስምንት የ5ኛ ዓመት የሐዲሳት ትርጓሜ ተመራቂ ዕጩ መምህራን ብዛት ሁለት የቀን (Regular) ሴሚናሪ ተመራቂ ዕጩ መምህራን ብዛት ሃያ አራት የማታ (Extension) ተመራቂ ዕጩ መምህራን ብዛት ሁለት መቶ ስምንት በድምሩ ሁለት መቶ ሰላሳ ስድስት ተመራቂ ዕጩ መምህራንን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የኮሌጁ መምህራንና ማህበረሰብ፣ የአዲስ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የተመራቂ ዕጩ መምህራን ቤተሰቦች በተገኙበት ቅዳሜ ሰኔ 18 ቀን 2008 ዓ.ም በዲፕሎማ አስመርቋል፡፡
የዕውቀት ምንጭ እና የሊቃውንት መፍለቂያ ሆኖ በሺዎች የሚቆጠሩ ዕጩ መምህራንን ያፈራውና ለረጅም ጊዜ ለቤተ ክርስቲያናችን የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በኮሌጅ ደረጃ ሊሰጥ የሚገባ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ብቃት ያላቸው መምህራን ተመድበውለት በቀንና በማታው የትምህርት መርሐ ግብር እያስተማረና እያሰለጠነ በሰርተፍኬትና በዲፕሎማ ሲያስመርቅ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኮሌጁ ውስጥ በመማርና ማስተማሩ ዙሪያ የሚፈጠር ሰው ሰራሽ ችግርና መሰናክል ቢኖርም መምህራኑም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ያንን በመቋቋም ተመራቂ ዕጩ መምህራንን በማፍራት የተቻለ መሆኑን ለምረቃው ከተዘጋጁ ሕትመቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከብዙ ድካም በኋላ የተገኘው ጥልቅ ዕውቀት በመጋረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር ተመራቂ ዕጩ መምህራን የምርጥ ዘር ባለቤት መሆናቸውን በማረጋገጥ ጽሙድ እንደ በሬ፣ ቀኑት እንደ ገበሬ ሆነው የሐዋርያትን ተልእኮ ማፋጠን እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡
ከዘመኑ የኑሮ ውድነት አንጻር በቢሮ ደረጃ ታይቶ የተመራቂ ዕጩ መምህራን የደመወዝ እስኬልም ከፍ እንደሚል ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምስራቅ ትግራይና የማይጨው አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በምረቃው ላይ ተገኝተው አብራርተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ብፁዕነታቸው በሰጡት ማብራሪያ በዚያው ዕለት ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለምረቃ በዓሉ የሰጡትን ጋዜጣዊ ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
“አንትሙ ውእቱ ዘርእ ክቡር ወንዋይ፣ ኅሩይ፣ እናንተ ምርጥ ንዋይና ክቡር ዘር ናችሁ”
የዚህ ጥቅስ ኃይለ ቃል የተነገረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በተነሳው ኢትዮጵያዊ ሊቅ በቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እየተቃኘ ሲዘምር የነረበው ቅዱስ ያሬድ ይህን ቃል የተነገረው ጌታችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርቶስን በቅርብ ያገለግሉ የነበሩትን የቅዱሳን ሐዋርያትን ማንነት ለማመልከት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር የዛሬው የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመራቂዎችንም፣ የዓላማና የእምነት ጽናት ሰንቃችሁ፤ በመማር ማስተማሩ ዙሪያ የሚፈጠረውን ሰው ሠራሽ ችግርና መሰናክል ተቋቁማችሁ፤ በየአህጉረ ስብከቱ ከሚገኙት የአብነት መምህራን በቀሰማችሁት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርት ብቻ ሳትወስኑ፤ የብሉይ ኪዳን ትርጓሜ፣ የሐዲስ ኪዳን ተርጓሜ፣ የሰሜናሪ ኮርስ አጠቃላይ ጥናት በሚሰጥበት ታላቅ ዕውቅናን ባተረፈው በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በተደራጀና በተደላደለ ዘመናዊ የትምህርት አሰጣጥ መርሐ ግብር መሠረት ሁሉንም በየመልኩ ተከታትላችሁ አጥንታችሁና አጠናቃችሁ ለመመረቅ በመብቃታችሁ ከላይ እንደተገለፀው ዘርእ ክቡር ወንዋይ ኅሩይ በሚለው ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሐየር መገለጽ የሚገባችሁ ሆናችሁ በመገኘታችሁና የምረቃ በዓላችሁንም ለማክበር  በመብቃታችሁ እኳን ደስ አላችሁ እንላለን፡፡ ከግብርና ዘርፍ በሚገኝ ምርጥ ዘር የተመሰላችሁት ያለ ምክንያት አይደለም፤ ከመልካም መሬት በቅሎ ከአረም ርቆ ለፍሬ የሚበቃ  ገዝፎ የወጣ ምርጥ ዘር፤ ለዘራው ገበሬ ደስታን እንደሚያጎናጽፍ ሁሉ እሾህ አንቆት፤ አረም ውጦት፣ ሙጃ ሸፍኖት በተዘራ ሜዳ ብቻውን መክኖ የሚኖር ዘር ደግሞ ተስፋ አድርጎ በሚጠብቀው ገበሬ ሥነ ልቡና ላይ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የታወቀ ነው፡፡
አሁን ተመርቃችሁ ወደ የሀገረ ስብከታችሁ ስትመለሱ በጉጉት የሚጠብቃችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ከናንተ የሚሻውን ቃለ እግዚአብሔር በማስተማር ሃይማኖታዊ ፍላጎቱ እንዲሟላ፤ ምሥጢራዊ ጥያቄው እንዲመለስና መንፈሱ እንዲታደስ በማድረግ ካስተናገዳችሁት የምትሰጡት ትምህርትና የምታስተላልፉት መልእክት ፍሬ ማፍራት ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር በምርጥ ዘር ዙሪያ  የተንቀሳቀሰው ገበሬ ባለ ሙሉ ተስፋ በመሆን እንደተደሰተ ሁሉ እናንተም የደስታ ተካፋይ እንድትሆኑ ያስችላችኋል፡፡
ስለዚህ ከብዙ ድካም በኋላ የተገኘው ጥልቅ ዕውቀት በመጋረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር የምርጥ ዘር ባለቤት  መሆናችሁን በተግባር ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ ጽሙድ እንደ በሬ ቅኑት እንደ ገበሬ ሁናችሁ ለተመረጣችሁበት የሐዋርያት ተልእኮ መፋጠን መረባረብ ይጠበቅባችኋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በዘመናዊ መልክ የማስፋፋትና የማሳደግ ሥራን ከጀመረች ውሎ አድሮአል፡፡ ለማስረጃም ያህል ከሁሉም በፊት ተቋቁሞ አገልግሎት ሲሰጥ የኖረ አሁንም አገልግሎቱን አጠናክሮ የመማር ማስተማሩን ሥራ በመቀጠል ላይ የሚገኘው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተጠቃሽ ነው፡፡
ከዚያም ቀጥሎ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ትምህርት ቤት በኮሌጅ ደረጃ ሊሰጥ የሚገባ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት ብቃት ያላቸው መምህራን ተመድበውለት በቀንና በማታው የትምህርት መርሐ ግብር እየስተማረና እያሠለጠነ፤ በሰርተፍኬት፣ በዲፕሎማ፣ በትርጓሜ መጻሕፍት ያስመረቃቸውና የሚያስመርቃቸው ደቀ መዛሙርት ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ የትምህርት ጥራቱም ዕውቅናውን እያጎለበተ በመታየቱ የኮሌጅ ስያሜ ተሰጥቶት እንዲሠራ መደረጉ ሌላው ተጠቃሽ ኮሌጅ ነው፡፡
በሀገረ ስብከት ደረጃ በመቀሌ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የቅዱስ ፍሬ ምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሀን መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶለት የላቀ ዕውቀት ያላቸው መምህራን ተመድበውለት የመማር ማስተማሩን ሥራ እያከናወነ በየበጀት ዓመቱ በሰርተፍኬት በዲፕሎማና በዲግሪ መርሐ ግብር እያስመረቀ የሚገኝ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሦስቱ ኮሌጆች እየተመረቁ የሚወጡ ደቀ መዛሙርትን በማሰማራት ምድብ ሥራዋን የምታከናውን በመሆኑ በሂደት የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕድገት ጉዞ የሚፋጥኑ ኃይሎች እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በሦስት ኮሌጆች መቋቋምና መጠናከር ብቻ ሳይወሰን በየክፍሉ ከፍተኛ  የትምህርት ተቋማትን ለማቋቋምና የተቋቋሙትንም በማጠናከር የማስፋፋትና የማሳደጉን ትግባር አጠናክራ ትቀጥልበታለች፡፡
ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስያናችን ሊቃውንቱን የሚያስገኙ ኮሌጆችን በማቋቋምና በማደራጀት ያደረገችውንና  አሁንም እያደረገች ያለውን ጥረት  ከመግለፅ አኳያ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ አጉልቶ ለማሳየት የተነገረው ህልውና ታሪክ ቢሆንም ከዚህ ኮሌጅ ማለትም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረው እየተመረቁ በብዙ ዓይነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሊቃውንት ብዙዎች ናቸው፡፡
እናንተም የዛሬዎቹ ምሩቃን የዛሬ ሀገር ተረካቢ ሊቃውንት የመሆናችሁን ያህል የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ እርምጃ ፍጹም እንደምታደርጉ በተስፋ የምትጠበቁ መሆናችሁን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ፍሬን አፍርታችሁ የሊቅነትን ስም ወርሳችሁ የደከማችሁበትን ሙያ በሥራ ማሳየት የሚገባችሁ ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ ለሥራ በምትንቀሳቀሱበት ወቅት ሁሉም ነገር ተመቻችቶ ላይገኝ ይችል ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ የእምነትና የዓላማ ጽናት የሃይማኖትና የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል፡፡
ጌታችን “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ” ብሎ የተናገረውን ኃይለ ቃል መሪ በማድረግ የዘመናችን ተኩላዎችን መጥፎ ሥራቸውንና የሐሰት መልክተኞች መሆናቸውን በግልጽ፣ በመመከት በተሟላ እምነትና ሥነ ምግባር ሆናችሁ ማስተማር ይጠበቅባችኋል፡፡
ዛሬ የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል የእምነት ነጻነት ባልነበረበት ጊዜ የነበሩ አባቶቻችን በዱላ እየተደበደቡ፣ በድናጋይ እየተወገሩ፣ በሰይፍ እየታረዱ፣ እየታሰሩና እየተፈቱ በጽኑ መንፈስና በጥቡዕ ልቡና እያስተማሩና እየጠበቁ ያቆዩአት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
ስለሆነም ከላይ እንደተጠቀሰው ከምርጥ ዘር ምርት እንደሚበቅል ሁሉ እናንተም በምታስተላልፉት ትምህርተ ሃይማኖት ይህችን ሉዓላዊት ቤተ ክርስቲያን የሚረከቡ ተከታዮችን በማብዛት በመንከባከብና በመጠበቅ ፍሬ ሃይማኖትን የተላበሰ ትውልድ እንደምታመርቱ ጽኑ እምነት አለን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
አዲስ አበባ
ሰኔ፣2008 ዓ.ም