የ2008 ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባኤ ባለ 17 ነጥብ ውሳኔ በመወሰን ተጠናቀቀ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀፅ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉኤው የዘንድሮውን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዐሉ ዋዜማ ከግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለ16 ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፎአል ፡፡
ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ፡፡
1.የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ጉባኤን በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳበቃ ጉባኤው ሥራውን ቀጥሏል ፡፡
2.የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በጽሑፍ ቀርቦ ጉባኤው ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱ የሚወሰኑት ሁሉ የአፈጻጸም ችግር እንዳይደርስባቸው ክትትል ይደረግ ዘንድ ተወስኗል፤
3.እስከአሁን እየተሠራበት ያለው ቃለ ዓዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል በተሰጠው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ረቂቅ ቀርቦ ምልዓተ ጉባኤው ከተነጋገረበትና ከታየ በኋላ የረቂቁ ዝግጅት በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲታተም ተወስኗል፤
4.ስለቅዱስ ፓትርያርክ እንደራሴ አስፈላጊነት ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተነጋገረ በኋላ የእንደራሴ አስፈላጊነት በምን ዓይነት ሕግ ላይ ተመሥርቶ መመረጥ አለበት የሚለውን በማጥናት ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርብ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት ሰባት አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል፤
5.ተፈጥሮ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ ርዳታ፤ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ለመልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎት የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ርዳታ ይደረግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ የድርሻዋንም አስተዋጽኦ አድርጋለች
6.በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚያገለግል ሕንፃ መገንባት ይቻል ዘንድ ቦታ እንዲሰጥ ከገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት የቀረበውን ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው የተቀበለው ስለሆነ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር በኩል ቦታ ተፈልጎ እንዲሰጥ ተወስኗል፤
7.ቅዱስ ሲኖዶስ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በሆኑ መንበረ ጵጵስናዎች ብቁ የሆኑ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ለመሾም ባለው እቅድ መሠረት፤
-ፈተናውንና መሰናክሉን ሁሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን
-በብሔር አቀፍና በዓለም አቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤
-የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸውን፤
-ለተልዕኮ የሚፋጠኑትን መነኰሳት በመመርመር፣ በማጥናትና በማጣራት ውጤቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፤
8.ሀ/ብፁዕ አባ ያሬድ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሥራን እንደያዙ በአርሲ ሀገረ ስብከት፣
ለ/ብፁዕ አባ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት፣
ሐ/ብፁዕ አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት፤
መ/ብፁዕ አባ እንድርያስ ሊቀ ጳጳስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኃላፊነቱን ሥራ እንደያዙ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ በመሆን ተመድበው እንዲሠሩ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል ፡፡
9.በውጭ ላሉት አህጉረ ስብከት ጥናት ተደርጎ በቋሚነት የሚሠሩ አባቶች እስከሚመደቡ ድረስ፤ ሀ/ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት፤
ለጊዜው በብፁዕ አባ ሙሴ የደቡብ ምዕራብና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ለ/አውስትራልያ ሀገረ ስብከት፤
በብፁዕ አባ ሄኖክ የምዕራብ ወለጋና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ሐ/ምሥራቅ አፍሪካ ኬንያና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት፤
በብፁዕ አባ ዳንኤል የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
መ/ ምሥራቅ አፍሪካ ሰሜን ሱዳንና ግብፅ አህጉረ ስብከት፤
በብፁዕ አባ ሉቃስ በክልል ትግራይ ዞን ወልቃይት ጸገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሆኖ በተጨማሪም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ፤
ሠ/ ደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት፤
በብፁዕ አባ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሲል ምልዓተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
10.በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው የሰላሙ ንግግር ይቀጥል ዘንድ ሰላም ለማንኛውም መሠረት መሆኑ ታምኖበት ይህኑ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንዲደረግ፤
11.ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወያየ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50 መሠረት ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል በያዙት የሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ ደርበው እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ድረስ የፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ተስማምቷል፤
12.በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ምርጫ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በማወዳደር፡-
ሀ.ብፁዕ አባ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣
ለ.ብፁዕ አባ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ሆነው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል ፡፡
13.በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ኃላፊነት በቤተ ክርስቲያናችን እየተረዱ የሚያድጉ እጓለ ማውታ ሕፃናት በየአህጉረ ስብከቱ መኖራቸው የሚታወቅ ነው፤
ይኸው የሕፃናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት እጓለ ማውታ ሕፃናትን በማሳደግና በማስተማር ረገድ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ አለኝታ ስለሆነ እስከአሁን ከነበረው ይዘት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኗል፤
14.የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስካሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ አሁንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቶአል፤
15.በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር ቀልጣፋና ቅንነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር፤ በየደረጃው የተዘረጉትም የልማት አውታሮች የበለጠ ውጤት እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ ከመንበረ ፓትርያርክ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ሁሎችም የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኃላፊነት ያለባቸው ስለሆነ ተከታትለው እየሠሩ እንዲያሠሩ ተወስኗል፤
16.በመከናወን ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጀማመር ሁሉም ኅብረተሰብ እጁን ሲዘረጋ እንደቆየ ሁሉ፤ አሁንም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም መላው ኅብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ይፈጽም ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
17ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጭ ባሉት አንዳንድ አህጉር እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር በጀሮአችን እንሰማለን፤ በዓይናችንም እናያለን፣ ለማስረጃም ያህል፤
-በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ ማጥለቅለቅና በሰደድ እሳት ዘግናኝ አደጋ የሚደርስ ኅልፈተ ሕይወት፤
-በእርስ በርስ የውስጥ ጦርነት የደረሰውና እየደረሰ ያለው ዕልቂት፤
-የእግዚአብሔርን ህልውና በሚፈታተኑ አንዳንድ ግለሰቦች ግንዛቤ ጉድለት እየደረሰ ያለው የጦርነት አደጋ፤
-በየብስ በውቅያኖሶችና በሰማይ ላይ በሚበሩ አውሮፕላኖች የሚደርሰው ዘግናኝ ዕልቂትና የመሳሰሉት ከሚጠቁሰት መካከል ናቸው፤
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላየካችን ጉዳት ለደረሰባቸው መጽናናትን መረጋጋትን እንዲሰጥልን ቅን ልቡና፣ ትሑት ሰብእና ለሚጎድልባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ትዕግሥቱን፣ ርኅራኄውን እንዲያበዛልን እንጸልያለን ፡፡
ከሁሉም በላይ ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ የሚፈለገውን ሰላምና አንድነት እንዲሁም የልማት ውጤት ማምጣት እንዲቻል ሁሉም ኅብረተሰብ ተግባብቶ፣ ተፋቅሮና ተከባብሮ በአንድነት መንፈስ መነሣሣት እንደሚያስፈልገው ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን ጎልቶ የሚታየው ድኅነት እንዲወገድ የተራበው፣ የተጠማው፣ የታረዘው፣ መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት እንዲኖር፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለሙም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ በመጸለይ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም.