የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ያስገነባውን ባለ13 ፎቅ ሕንጻ አስመረቀ!!
በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንጻዎች ልማትና አስተዳደር ድርጅት ፒያሳ አካባቢ ልዩ ስሙ ባንክ ኦፍ ዲ ሮማ በተባለው ቦታ ላይ ያስገነባውን ባለ13 ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሕንጻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ብዕፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመመሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ጐይቶም ያይኑ፣ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቅዳሜ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም በይፋ ተባርኮ ተመርቋል፡፡
የምርቃ መርሐ ግብሩ በተከናወነበት ወቅት የሕንጻው ባለሙያ ስለህንጻው ይዘትና ጥራት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ውብሸት በበኩላቸው ሕንጻው ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ድረስ ድርጅቱ ብዙ ውጣ ውረዶችን አስተናግዷል በማለት አብራርተዋል፡፡
አቶ ኤፍሬም የተባሉ የመንግሥት ተወካይ በቦታው ተገኝተው የተሠራውን ሕንጻ በማድነቅ ለወደፊትም መንግሥት ለቤተክርስቲያኗ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የወላይታ ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልዕክት በቸርነቱ በመንግሥቱ ያልተለየን አምላካችን ለብዙ ዘመናት ሲታሰብ የነበረውን የቤተክርስቲያናችንን ዕቅድ አሳክቶ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሕንጻውን አስገብተን ለፍጻሜ ያበቃንን አምላክ እናመሰግናለን፡፡
በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ ዛሬ በ2008 ዓ.ም የተጠናቀቀው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሰጪነት ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰጠችንን ኃላፊነት ለመወጣት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ከልማትና ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋር በመነጋገር ሥራው በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅና ቤተክርስቲያን ገቢ እንድታገኝ ተደርጓል፡፡
በዚህም አማካኝነት ሥራውን ለውጤት ያበቃውን ዛምራ ኮንስትራክሽንን እናመሰግናለን፡፡ ሥራው የተሠራው በጥራት ነው፡፡ ኢንጂነር ገ/መስቀል ተስፋዬ ሕንጻውን እየተቆጣጠሩ ስላሰሩልን እናመሰግናለን፡፡ ኢንጂነር አበበ ግርማ ሥራውን በነጻ ስለሰሩልን እናመሰግናለን፡፡ ከአርባ ዓመት በፊት የተሠሩትን ሕንጻዎች ለ17 ዓመት ተወርሰውብን የነበረ ሲሆን ቤተክርስቲያናችን ከ42 ዓመታት በኋላ ገቢ የሚያስገኝ ሕንጻ ስትሰራ የመጀመሪያዋ ነው፡፡
ይህ ሕንጻ የመጨረሻው አይደለም ቤተክርስቲያን የጀመረችውን የሕንጻ ግንባታ ሥራ አጠናክራ ትቀጥልበታለች ብለን እናስባለን፡፡ ይህ ሕንጻ የተገነባበት ቦታ በተለምዶ ባንኮ ዲሮማ ይባላል፡፡
ቅዱስነትዎ ሕንጻውን ባርከው ለሕንጻው ስያሜ እንዲሰጡልን እንጠይቃለን በማለት ብፁዕነታቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ የቤተክርስቲያናችን ሕንጻ ተጀምሮ ለዚህ ውጤት በመብቃቱ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
በዚህ ሕንጻ ሥራ ላይ ሊመሰገኑ ከሚገባቸው ቅድሚያ የምንሰጠው ለቅዱስ ሲኖዶስ ሲሆን በመቀጠልም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኃላፊዎች ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ይህንን ሥራ እየተከታተለ ለፍጻሜ ያበቃ ተቋም ስለሆነ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የሕንጻ ተቋራጩ ዛምራ ኮንስትራክሽን ይህንን ሕንጻ ሰርቶ ስላስረከበን ከነተቆጣጣሪዎቹና ከነማሕንዲሶቹ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ስማቸው ያልተጠቀሱትም በጐ አድራጊዎቹ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
ይህ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ለሃይማኖታችን እድገትና ጥበቃ፣ ለስብከተ ወንጌል ማስፋፊያና ለበጐ አድራጐት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ይህ ሕንጻ ብቻውን ቆሞ የሚቀር ሳይሆን ሕንጻው ሕንጻን እየወለደ በቤተክርስቲያን ባዶ ቦታዎች እንዲበዛ እመኛለሁ፡፡ በደርግ ዘመን የቤተክርስቲያናችን ቤቶች ተወርሰው ባዶአችንን ቀርተን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የአሁኑ መንግሥታችን ሕንጻዎቻችንንና ቤቶቻችንን በመመለስ ባዶ ቦታዎችን ጠብቆ በማቆየት ለወደፊቱ ሕንጻ እንድንሰራባቸው ተስፋ ሰጥቶናል የሥራ ጉዳይ የሁሉንም መነሳሳት ያስፈልጋል፡፡
ምዕመናኖቻችን ለጋሾች ናቸው ለቤተክርስቲያን ሕልውና የማይከፍሉት መስዋዕትነት የለም የቤተክርስቲያን ሀብት ምዕመናን ናቸው፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ማስተባበር ብቻ ነው፡፡
ይህ ሕንጻ ከዛሬ ጀምሮ ትንሳኤ ሕንጻ እየተባለ እንዲጠራ ተሰይሟል በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ አድርገው አባታዊ መልዕክት ከአስተላለፉ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡