የግብረ ሰላም በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፤የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅና የክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት ቅዳሜ ሚያዝያ 22 ቀን 2008 ዓ.ም የግብረ ሰላም በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ ለዘተንስአ እሙታን ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትነሣኤሁ አግሀደ የሚለውን ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር ተረኛው የቦሌ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምና መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ካቴድራል ሊቃውንት በዘንግ ዝማሜና በጸናጽል ዘምረዋል፡፡
እንደዚሁም የካቴድራሉ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ይትቀደስ ስምከ በኃይለ መስቀልከ በዕፀ መስቀልከ ዘአእበይኮ ለስምከ ስብሐት ለከ ለባህቲትከ የሚለውን ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር በወረብ አቅርበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ እንድርያስ በበዓሉ ላይ ለተገኘው ታዳሚ በሰጡት ትምህርት ስምኡ ሰብአ እስራኤል (የሐ. 2÷21) የእስራኤል ሰዎች እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ስሙ አስተውሉ ልብም አድርጉ በሚል ርዕስ ተነስተው ምስጢር ሲገለፅ በልማድ የኖረ አእምሮ ይረበሻል፤በጨለማ የተዘጋውን ቤት ለመክፈት ነቢያት አበው በመስዋዕታቸው ዓለምን ማዳን አልቻሉም፡፡ ይህ የምናከብረው በዓል ሰላም፣ በረከት፣ አንድት የተሰጠበት፣ የክርስቶስ ሥጋ የተቆረሰበት፣ ደሙ የፈሰሰበት በዓል ነው፡፡ ክርስቶስ ዓለምን ሲመራ ብዙ ችግር ደርሶበታል፡፡ ቤተ እስራኤል በገጠማቸው ዘመን ለመጠቀም አልቻሉም፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት ለመመለስ አልቻሉም፡፡ ዘመንን ማወቅ ከእግዚአብሔር ጋር አላመጣላት አስፈላጊ ነው፡፡
ለክርስቶስ ደንጊያችና እንጨቶች መስክረዋል፡፡ ሰዎች ግን አላወቁትም፡፡ የሞት ቁራኝነትን አስወግዶ ተነሳ እግዚአብሔርነቱ አስነሳው ሞት ለይዘው አልቻለም፡፡
ሰይጣን በነፍስ በሥጋ የሚያሰቃያቸውን ሰዎች ጌታ በደሙ ቀደሳቸው አከበራቸው ገብረ ሰላ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሀደ፡፡ ዛሬም ሰይጣን ዓለምን እያፋጀ ነው ያለው፡፡ ሰይጣን ሰዎችን ለማጥፋት በነፋስ ተጭኖ ይመጣል፡፡ ጌታ በመስቀል ተሰቅሎ ሕይወታችሁ እኔ ነኝ አለ፡፡
በቅንአት የመጣ በቀል ያለ ደም መፍሰስ አይለቅም፡፡ ሰይጣን አዳምና ሔዋንን በሸሙጥ ቃል አሳታቸወ፡፡ ሳይማሩ የተማሩ ሳይረዱ የተረዱ ብዙ ናቸው፡፡ በክርስቶስ አደባባይ ፍርሃት የለም፡፡ ሞተ በሥጋ ወሀይወ በመንፈስ (1ጴ 3÷14) በሥጋ ሞተ በመለኮታዊ ስልጣኑ ተነሣ ይህ ቃል ለመናፍቃኑ አይመችም፡፡
በ6 ሰዓት ፀሐይ ከብርሃን ተለየ፡፡ ጨረቃ ደም ሆነች ከዋክብት ረገፉ፡፡ እነዚህ ብርሃናት ምስክርነታቸውን ለፈጣሪያቸው ሰጡ አይሁድ ግን ካዱት፡፡
ዓለም የሚተራመሰው በቋንቋ ነው፡፡ ወደ ዕውቀት አልደረሰም፡፡ ጌታ ግን ታሥረው ወደነበሩት ወረደ እሰረኞችን ፈታ ነፃነትን ሰበከላቸው በጠላት እጅ ተይዘው እየተገረፉ ላሉት ደረሰላቸው ጌታ ቀጠሮ አክባሪ ነው በቀጠሮ መጣ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን አላቸው፡፡ ስደት ባርነት ቀረ ነፃነት መጣ አላቸው፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አበታችን የሚከተለውን መልአክት አስተላልፈዋል፡፡
ፈሪሳውያን በጲላጦስ አደባባይ ተሰብሰቡ በ3ኛው ቀን እነሳለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል አሉን፡፡ መቃብሩን ዘጉት አተሙት አይሁድ ፈጣሪያቸውን መሰሐቲ አሉት አዳኞቸው መሆኑን ስለ ልተረዱት ነው፡፡
የክርስቶስን አዳኝነት እንዳይቀበሉና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዳይገቡ አደረጉአቸው አውቀውትስ ቢሆን ኑሮ ጌታቸውን በመስቀሎትም ነበር፡፡ ነገር ግን ስላላመኑ እሡ ለሠራው የመጣበትን ሥራ ሠርቷል፡፡ እነሱ በመቃብር ይቀራል ብለው አስበው ነበር ግን እነሱ እንዳሉት አልሆነም የዛሬው በዓል የምስራቹን የምንገልፅበት ቀን ነው በማለት አባታዊ ምልእክት ካስተላለፉ በኋላ የተዘጋጀውን ቀጤማ ባርከው ካደሉ በኋላ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡