“ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም”

በዐቢይ ጾም ወቅት ከሚታሰቡት የሳምንታት በዓላት መካከል ከሆሳዕና በፊት ባለው ዕሑድ  የሚታሰበው ሳምንታዊ በዓል ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡
ኒቆዲሞስ
ኒቆዲሞስ በመባል የሚታወቀው ሰው በዘመነ ብሉይ ኪዳን ፈሪሳዊና የአይሁድ አለቃ የነበረ ሰው ነው፡፡ (ዮሐ 3÷1) የኢየሩሳሌም ሸንጎ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በከሰሰው ጊዜ ኒቆዲሞስ ስለ ክርስቶስ መሰከረ (ዮሐ 7÷45)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ኒቆዲሞስ ለመገነዝ የሚውል መልካም መአዛ ያለው የሽቱ ቅመም ይዞ መጣ (ዮሐ 19÷39) ዮሴፍ ከተባለ ሰው ጋር የክርስቶስን ሥጋ ከመስቀል አውርደው በነጭ አንሶላ ገነዙት፡፡
በዘመነ ትንሣኤ ወቅት በሥርዓተ ቅዳሴው መጀመሪያ ላይ “ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ ገነዝዎ ለኢየሱስ በሰንዱናት” ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ኢየሱስን በነጭ አንሶላ ገነዙት እየተባለ በዜማ ይታወጃል፡፡ ሰንዱናት ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ነጭ አንሶላ ማለት ነው፡፡
ኒቆዲሞስ በተባለው ሰንበት ማለትም ቅዳሜ ለዕሑድ አጥቢያ በሌሊቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሖረኃቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ መልአኮሙ ለይሁድ” የሚለውን የቅዱስ ያሬድ ቃለ እግዚአብሔር ሊቃውንቱ በዜማ ያቀርባሉ፡፡
በጧቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ወቅት በዲያቆናትና በቀሳውስንት፣ በንባብና በዜማ የሚከተሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች ይቀርባሉ፡፡ (ሮሜ 7÷1-14)
1ጴጥ 5÷1-13 የሐዋ 5÷26-32 መዝ 16÷13 ዮሐ 3÷1-20 ከላይ ተጠቀሱት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች መካከል በዳዊት መዝሙርና በዮሐንስ ወንጌል የተገለጹት ጥቅሶች እንደሚከተለው ተብራርተዋል፡፡
“ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮለልብየ÷አመከርከኒ ወኢተረክበ አመጸበላዕሌየ÷ከመ ኢይንብብ አፉየግብረ ዕደ እጓለ እመሕያው፡፡”
ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጎበኘኸኝ÷ፈተንኸኝ ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፡፡ (መዝ 16÷3) ቅዱስ ዳዊት ጻድቅ ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ንጽህናውን አንድ በአንድ በመዘርዘር ይገልጻል፡፡ በእርሱ ላይ የተነሡ ጠላቶች በሄዱበት  መንገድ አልሄድም፡፡ ለዚህም ሁለመናውን በርብሮ የሚያይ እግዚአብሔር ምስክሩ ነው፡፡
ከላይ የተገለጸው ማብራሪያ በዳዊት መዝሙር የተጻፈው ቃል ሲሆን በዮሐንስ ወንጌል 3÷1-20 የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር  ዘንድ እንደ መጣህ  እናውቃለን አለው፡፡ ኢየሱስም  መልሶ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር  የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው፡፡ ኒቆዲሞስም ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት  ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ  ማኅፀን  ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?  አለው፡፡ ኢየሱስም  መለሰ እንዲህ ሲል  እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት  ሊገባ  አይችልም፡፡
ከሥጋ  የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው፡፡ ዳግመኛ ልትወለዱ  ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ፡፡ ነፍስ ወደሚወደው ይነፍሳል ድምፁንም  ትሰማለህ ነገር ግን  ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ መልሶ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን? እውነት እውነት እልሃለሁ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም፡፡ ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመነችሁ ስለ ሰማያዊ ነገረ ብነግራችሁ እንዴት ታምናለችሁ? ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፡፡ እርሱም በሰማይ  የሚኖረው የሰው ልጅ ነው፡፡
ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃና የሃይማኖታዊ ሸንጎ አባል ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሸንጎ ሰባ አባላት ያሉት ሲሆን በማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ  የመጨረሻውን ውሳኔ የሚሰጥ ነው፡፡
ሕዝባዊ ጉዳዮችን በሙሉ የሚመለከተው የሮም መንግሥት ነበር፡፡
ኒቆዲሞስ በጣም የተማረና መምህርም የሆነ ሰው ነው፡፡ (ዮሐ 3÷10) ኒቆዲሞስ በአይሁድ ዘንድ እንደ መምህር ወደ ማይቆጠረው ወደ ኢየሱስ በሌሊት እየሄደ ያነጋግረው ነበር፡፡
በሌሊት የሚሄደውም ማንም ሰው ወደ ኢየሱስ መሄዱን እንዳያውቅበት ነበር፡፡
ኒቆዲሞስ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ታምራት አይቷል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ የተለየ መምህር (ረቢ) መሆኑን ያውቅ ስለነበር ከእርሱ ብዙ ለመማር ይመኝ ነበር፡፡ ሌሎቹ ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ይቃወሙት ነበር፡፡ እንዲያውም የኋላ ኋላ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ከኢየሱስ ጎን ቆሞአል፡፡ (ዮሐ 5÷50)
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲወጣ ሌሎቹ ደቀ መዝሙርት  መከራውን ተሳቀው ጥለውት ሲሄዱ ኒቆዲሞስ ግን የክርስቶስን ሥጋ ከመስቀሉ ላይ አውርዶ እንዲቀበር አድርጎል፡፡ (ዮሐ 19÷39)
ኒቆዲሞስ በመጀመሪያ ላይ ድንጉጥና ፈሪ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይልቅ ለክርስቶስ ታማኝ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ኒቆዲሞስ የዘለዓለም የሚገኘው ሕግን በመጠበቅ ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህ ሰው ከልቡ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ወደ መንግሥተ ሰማይ ለመግባት ፍላጎት እንዳለው ክርስቶስ ያውቃል፡፡
ስለዚህ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ማወቅ የሚገባውን ነገር ፈጥኖ ነገረው፡፡ ይህም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት የሚአስችለው ዳግም ሲወለድ ብቻ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የሚአስፈልገው አዲስ ሕግ ሳይሆን  ዐዲስ ልብ ነው፡፡ ዳግም የተወለደ ሰው ከቶ አይሞትም፡፡ ይህ ሐሳብ ለኒቆዲሞስ የማይታሰብ ነገር ስለሆነበት አንድ ሰው ከተወለደ በኋላ ወደ እናቱ ማህፀን  ገብቶ እንዴት ይችላል አለው፡፡  ክርስቶስም ሰው ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ  በስተቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት  መግባት እንደማይችል ነገረው፡፡