ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመምህር ጎይተኦም ያይኔ ለሁለተኛ ጊዜ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
ከመጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለተሾሙት ለመምህር ጎይተኦም ያይኔ፣ ለመጋቤ ጥበብ ናሁሠናይ በለጠ የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል ዋና ክፍል ኃላፊና ለአቶ ገ/ሕይወት አስገዶም የሀገረ ስበከቱ ሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ዕንጦንስ የአውሮፖ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የካህናት አገልግሎት መምሪያ ዋና ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች ፣የሰባቱም ክፍላተ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ ቁጥራቸው 1000 የሚደርስ የአዲስ አበባ ከተማ አድባራትና ገዳማት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን፣ሠራተኞችና ደቀመዛሙርት በተገኙበት ሚያዚያ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ደማቅ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡
የ3ቱም የሥራ ኃላፊዎች የሹመት ደብዳቤ ከተነበበበ በኋላ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ወቅት አቶ ገ/ሕይወት አስገዶም ለጉባኤው ባስተላለፉት መልእክት ይህ የተሰጠን ኃላፊነት ብዙ የሚያስመካ፣ ብዙ የሚያስደስት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የተሰጠን ኃላፊነት ተጠያቂነትም አለበት፡፡ የአድባራቱና ገዳማቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ዕገዛ ካልተደረገበት አንድም ስንዝር መራመድ እንደማይቻል አምናለሁ፡፡
ስለዚህ የብፁዕ ወቅዱስ አባታችን መመሪያ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሁላችሁም ጸሎትና ዕገዛ እንዳይለየን አደራ እላለሁ በማለት አጭርና ግልጽ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ መጋቤ ጥበብ ናሁሠናይ በለጠ በበኩላቸው ባስተላለፉት በጽሑፍ የተደገፈ መልእክት የብፁዕ ወቅዱስ አባታችንን መመሪያ ተቀብለን ለመሥራት እንተጋለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ቤተሠሪ በከንቱ ይደክማል …… በማለት የተናገረውን ቃልም በንግግራቸው አብራርተውታል፡፤ የክትትልና የቁቁጥጥር ሥራ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሰላም፣ፍቅርና ታማኝነት ከእኛ ይፈለጋል፡፡ አለመታመን ያስወቅሳል፣ ያስቀጣል፣ ያስገድላልም በማለት መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ በማስከተል መምህር ጎይተኦም ያይኔ ባስተላለፉት መልእክት በመጀመሪያ ለዚህ ታላቅ ጥሪ የመረጠኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን ስለአስተማረችኝ ብዙ የሚአስገኝ ነገር አይኖርም፡፡ ንግግራችንን ለወደፊቱ በሥራ ላይ እንገልጸዋለን፡፡ ይህ ታላቅ ሰልፍ የእግዚአብሔር ሰልፍ ነው፡፡ ሁላችንም እየተመካከርን በአንድ ላይ መሥራት አለብን፡፡ ጠቃሚ ምክር ለሚለግሰኝ ሥራውን በአግባቡ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ የ2000 ዕድሜ ያላትን ታላቅ ቤተክርስቲያን ለመምራት መታደላችን በእጅጉ ያስደስታል፡፡ በየመድረኮቹ እየተገናኘን ጠቃሚ ውይይቶችን እንወያያለን፡፡ ቤተክርስቲያን የእኛ ናት፡፡ እናንተ ሁላችሁም አዋቂዎች ናችሁ፡፡ እየተመካከርን ቤተክርስቲያናችንን ወደተሻለ ዕድገት ማምጣት አለብን፡፡ ከሙዳዬምጽዋት ጥገኝነት ለመላቀቅ ተግተን የልማት ሥራ መሥራት አለብን በማለት መልእክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ እንጦስ ለተሰብሳቢው ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ አዳራሽ አልነበረውም፡፡ ይህን የተንጣለለ አዳራሽ ያሠሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መሆናቸውን እናስታውሳለን፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኃላፊዎች ሥልጣን ዘመን ከአንድ ዓመት የማያልፍ ሆኖ ይታያል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ብዙ አገልጋይና ምዕመናን ያሉበት በመሆኑ ከብዛት የተነሳ የአሠራሩ ሲስተም እየጎደለ ነው፡፡
በኃላፊነት እንቆያለን የሚሉ ኃላፊዎችም ቀኑ እያጠረባቸው ነው፡ መኖርም መሥራትም የምንችለው እግዚአብሔር የፈቀደልንን ነው፡፡ ዛሬ በመካከላችሁ የተገኘሁት መምህር ጎይተኦምንና እናንተን ለማስተዋወቅ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ተልኬ ነው፡፡ መምህር ጎይተኦም ያይኔ ሁለት ድግሪና ማስተርስ ያላቸው ምሁር ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያንም ብቃት ያለው ትምህርት አላቸው፡፡
ስለዚህ የተሻለ ሥራ ይሥራሉ ተብሎ በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ተመረጠዋል፡፡ ሥጋትና ፍርሃት በሐቅና በዕምነት ይወገዳሉ፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሁሉም አህጉረ ስብከት ሞዴል የሚሆን ነው፡፡ በሕዝብ ብዛትና በፋይናንስም የተሻለ ነው፡፡ ይህንን ሀገረ ስብከት በጥበብ መምራት ያስፈልጋል፡፡ በተሰበረ ልብና በተዋረደ መንፈስ ማገልገል ያስፈልጋል፡፡ ሥራችን ሁሉ ቅልጥፍና ሊኖረው ይገባል፡፡ ወደ ሥራ ቦታችን በሰዓት መግባትና በሰዓት መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ተወደደም ተጠላም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የቅዱስነታቸው ልዩ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ለሀገረ ስበከቱ ከረዳት ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ ማንኛውንም ኃላፊ መልምለው መስቀመጥ የሚችሉት ቅዱስነታቸው ናቸው፡፡
ረዳት ሊቀ ጳጳሱም ሆነ ሥራ አስኪያጁ ከፓትርያርኩ መመሪያ እየተቀበሉ መሥራት አለባቸው በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ አባታዊ መልእክት አስተላልፈው እንደጨረሱ የትውውቁን መርሐ ግብር በጸሎት ዘግተዋል፡፡