የቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአስተዳደር ምክትል ዲን የነበሩት መምህር ጎይተኦም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ!!

00159

ቀደም ሲል በመቀሌ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅና በሰዋሰወ ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመድበው ሲሠሩ የነበሩና በኋላም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአስተዳደር ምክትል ዲን በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት መምህር ጎይተኦም ያይኑ ከመጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በመዛወርና የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን እንዲሠሩ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የተፈቀደላቸው በመሆኑ መጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው የአቀባበል ሥርዓት ወቅት በተነበበው የሹመት ደብዳቤ ተረጋግጧል፡፡
ለመምህር ጎይተኦም ያይኑ በአድራሻ በተጻፈላቸው የሹሙት ደብዳቤ ያላቸውን ዘመናዊና መንፈሳዊ እውቀት ከግምት በማስገባትና ይህንኑ ዘመናዊና መንፈሳዊ እውቀታቸውን ተጠቅመው የበለጠ የሥራ ውጤት ያሳያሉ ተብሎ የታመነባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ሕግንና ሥርዓትን መሠረት አድርገው በመሥራት፣ በሀገረ ስብከቱ መልካም አስተዳደር እንዲሠፍን ጥረት እንዲያደርጉ በግልጽ ተብራርቷል፡፡
የሹመት ደብዳቤው በተሰማበት በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገደማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራን፣ ሠራተኞችና ደቀ መዛሙርት በተገኙበት የአቀባበል ሥርዓት ተደርጓል፡፡
ከዋና ሥራ አስኪያጁ በተጨማሪ መጋቤ ጥበብ ናሁ ሠናይ በለጠ የሀገረ ስብከቱ የሰው ኃይል ዋና ክፍል ኃላፊ፣ አቶ ገብረሕይወት አሰገዶም የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሆነው የተመደቡ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ተነቧል፡፡
የአቀባበሉን ሥርዓት የመሩትና ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፈውን የሹመት ደብዳቤ ለታዳሚው ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ እንደአብራሩት የአቀባበሉ ሥርዓት በሌላ ጊዜ ከዚህ በተሻለ ደማቅ ሥርዓት ይፈጸም ዘንድ መርሐ ግብር እንደሚያዝ አስታውቀዋል፡፡