“ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ”
በመምህር ሣህሉ አድማሱ
በዐቢይ ጾም ሳምንታት ከሚታሰቡት ሳምንታዊ በዓላት መካከል ጾሙ በገባ በአምስተኛው ሳምንት የሚታሰበው ሳምንታዊ በዓል ደብረ ዘይት በመባል ይታወቃል፡፡
ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ከታላቁ ቤተ መቅደስ/የሰለሞን ቤተ መቅደስ) አደባባይ ሰባ አምስ ሜትር ገዳማ ከፍ ይላል፡፡ ዳዊት ከአቤሲሎም በሺሽ ጊዜ ወደ ደብረ ዘይት አቀበት ወጣ (2ሳሙ 15÷30) ቤተ ፋጌና ቢታንያ ከደብረ ዘይት ተራራ ግርጌ ናቸው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለም ፍጻሜ በደብረ ዘይት ይወርዳል የሚል ትንቢት ተነግሯል (ዘካ 14÷4) ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ ትምህርት አስተማረ (ማቴ 24÷1-49) በዐቢይ ጾም ወቅት ማለትም በደብረዘይት ዕለት ቅዳሜ ለሑድ አጥቢያ የሚዘመረው ያሬዳዊ ቃለ እግዚአብሔር “እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት…” የሚል ሲሆን በጧቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ በዲያቆናትና በቀሳውስት፣ በምንባብና በዜማ የሚቀርበቡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክቶች፣ መዝሙርና ወንጌል (1ተሰ 4÷13-ፍ) 2ጴጥ 3÷6-14) (የሐዋ 24÷14-25) (መዝ 49÷3) (ማቴ 24÷1-49) ሲሆኑ በዳዊት መዝሙርና በማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡ “እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፣ ወአምላክነሂ ኢያረምም፣ እሳት ይነድድ ቅጽሜሁ፡፡” (መዝ. 49÷3) እግዚአብሔር ይመጣል፤ ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነዳል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በሐዲስ ኪዳን ዘመን የሰውን ሥጋ ለብሶ በመጣበት ጊዜ ሰዎች የሚሠሩትን ኃጢአት አይቶ እንዳላየ ሲታገሳቸው የነበረ ሲሆን በዚህ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ግን ሰዎች በሚሠሩት ኃጢአት ልክ ቅጣት /ፍርድ/ ይሰጣል፡፡ በዚህ የፍርድ ቀን የእግዚአብሔር መገለጥ በመብረቅና በነጎድጓድ ክስተቶች የታጀበ ነው፡፡ ከላይ የተመለከትነው በዳዊት መዝሙር የተጻፈውን ነገረ ምፅአተ ክርስቶስን ሲሆን በማቴዎስ ወንጌል (24÷1-49) ድረስ ያለው እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡
“ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ፡፡ እርሱ ግን መልሶ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው፡፡
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላቸሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፡፡ ራብም፣ ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡
በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ እረስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙችንም ያስታሉ ከዓመጻም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፤ ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል፡፡
እንዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል፡፡ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ፤ በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው፤ ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና፡፡ እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ፡፡
በዚያን ጊዜ ማንም እነሆ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድነቅ ያሳያሉ፡፡ እነሆ አስቀድሜ ነገርኋችሁ፡፡ እንግዲህ እነሆ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ አትውጡ፤ እነሆ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ አትመኑ፤ መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤ በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ፡፡
ከዚያችወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ የወድቃሉ፤ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ፤ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላል፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር ከሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤ መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ፡፡
ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቊጥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ፡፡ እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፡፡ ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም፡፡
ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ልጅም ቢሆን ሚያውቅ የለም፡፡ የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡ በዚች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡም፣ እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፣ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች፡፡ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ፡፡ ያን ግን እወቁ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ ቤቱም ሲቈፈር ባልተወም ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና”
ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ፍርድ የሚሰጥበትን ቀንና ሰዓት ማንም የሚውቅ የለም፡፡ (ማቴ 24÷36) ስለዚህ መቼ እንደሚመጣ ትንቢት መናገር ከንቱ ነው፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የሰው ክፋት በጣም ታላቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በዚህ አዝኖ ሰዎችንና ፍጥረታትን ሁሉ በምድር ላይ ታላቅ የንፍር ውሀ ጎርፍ በመላክ ለማጥፋት በወሰነ ጊዜ ኖህ የተባለ አንድ ጻዲቅ ሰው ስላገኘ ትልቅ መርከብ ሰርቶ ከጥፋት ውሀ እንዲአመልጥ ነገረው፡፡
ኖህም በሠራው መርከብ ውስጥ ገብቶ እርሱና ቤተሰቡ ከጥፋት ውሀ ዳኑ፡፡ ሌሎቹ ኃጢአተኞች ግን በንፍር ውሀ ጎርፍ ጠፉ (ዘፍ 6÷5)
በዓለም መጨረሻ ላይ የሰው ልጅ ወይም የክርስቶስ መምጣትም ልክ እንደ ንፍር ውሀ ጎርፍ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ሆነው ያልተቆጠሩት ሁሉ በገሀነማዊ የዘለዓለም ቅጣት ይቀጣሉ፡፡ (ማቴ 24÷40) የሰው ልጅ ወይም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ ፍርድ ይሆናል፡፡ መላእክቱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ (ማር 13÷27) ያልተመረጡት ርኩሳንና እምነት የሌላቸው ሁሉ ይጠፋሉ፡፡ በእርሻ ላይ ካሉ ሁለት ሰዎች አንዱ ወደ መንግሥተ ሰማይ ይወሰዳል (1ተሰ4÷16) ሌላው ግን በገሀነማዊ እሳት ለመቀጣት ይቀራል፡፡ ከሁለት የሚፈጩ ሴቶች አንዷ ወደ መንግሥተ ሰማያት ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ግን በገሀነማዊ እሳት ለመቀጣት ትቀራለች፡፡
ስለዚህ በእግዚአብሔር ፊት ሁል ጊዜ ታዛዥና ንጹሐን ሆነን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ ከመጣ በኋላ ግን ለኃጢአተኞች የንሰሐ ዕድል አይኖራቸውም፡፡ ለዚህ ነው ሰዎች ያለምንም መዘግየት ንስሐ መግባትና እምነታቸውን በክርስቶስ ላይ ማድረግ ያለባቸው፡፡ የድኅነት ቀን አሁን ነው (2ቆሮ6÷2) ከዓለም ጋር እንዳይፈረድብን ሁላችንም በቅድስና እና በመንፈሳዊነት ልንኖር ይገባናል፡፡ ይህ አሮጌ ዓለም ያልፋል፡፡ እኛ ግን ጻድቃን ወደ ሚኖሩበት ዐዲስ ሰማይና ዐዲስ ምድር እንገባለን፡፡