በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 14ቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከግዕዝና ከአማርኛ ቋንቋዎች ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ

0159

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስራአራቱን ቅዳሴያት ከግዕዝና ከአማርኛ ቋንቋዎች ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ በማስተርጎምና በማሳተም ቅዳሜ መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቀድሞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች በተገኙበት በኢሊሊ ሆቴል በይፋ ተመርቋል፡፡
ከአማርኛ እና ከግዕዝ ቋንቋዎች ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ የተረጎመው አስራ አራቱ ቅዳሴያት በተመረቀበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የቀሌም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የደቡብ ምዕራብ ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ የተጻፈውን መነሻ በማድረግ በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የወላይታ ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው በአስተላለፉት መልዕክት ለመወለድ፣ ለመሞት፣ ለመትከል፣ ለመንቀል ጊዜ አለው በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን የተናገረውን ቃል መነሻ አድርገው ቋንቋ የመግባቢያ መሠረት መሆኑን፣ ቋንቋ እንደ መሸጋገሪያ ድልድይ አገልግሎት ያለው መሆኑን፣ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን የተለያዩ ቋንቋዎች የነበሩ መሆናቸውን፣ ለሐዋርያት 72 ቋንቋዎችን መንፈስ ቅዱስ የገለጸላቸው መሆኑን እና ሰፊ ሕዝብ ሰፊ ቋንቋ ሊኖረው የሚገባ መሆኑን፣ አበባ የሚያምረው የተለያዩ ቀለማት ህብር ሲኖረው በመሆኑ፣ የምንለብሳቸው አልባሳት በተለያዩ ቀለማት የተዋቡ መሆናቸውን፣ ንብ የምትቀስመው አበባን ሲሆን በዚሁም ጣፋጭ ማር የምታስገኝ መሆኗን፣ ለአንድ መሠረታዊ ዓላማ ቋንቋ ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ መጻሕፍትን በየቋንቋው እያስተረጎመች የምትገኝ መሆኗን፣ የግዕዝ ቋንቋ የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ቅርስ በመሆኑ ተጠብቆ ሊኖር የሚገባው መሆኑን፣ ዛሬ ለምረቃ የበቃው አስራአራቱ ቅዳሴያት ብዙ ውጣ ውረድ እና ብዙ ድካም ያስከተለ ሲሆን ከዚህ በኋላ ግን ለውጤት የበቃ መሆኑን፣ ለዚሁም ሥራ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በኮሚቴነት ተመድበው ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ መሆናቸውን በማብራራት ሰፋ ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዚህ የምረቃ በአል ላይ የተገኙት የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በሰጡት መግለጫ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአሌክሳንደሪያ ጳጳሳትን እያስመጣች ስትገለገል የቆየች ሲሆን የመጀመሪያውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስን ፓትርያርክ አድርጋ መሾም በጀመረችበት ጊዜ ትልቅ የደስታ ቀን ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በወቅቱ በርስት ጉልት ስትተዳደር ከቆየች በኋላ ሁለተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሰበካ ጉባኤን በማቋቋም እና ቃለ አዋዲ የተባለ መመሪያ በመደንገግ እራሷን እየመራች በመቆየት አሁን ካለንበት ከ6ኛው ፓትርያርክ ደርሳለች፡፡ ይህ ትልቅ የደስታ ትንሳኤ ነው፡፡ በዛሬው ዕለት ከግዕዝና ከአማርኛ ወደ አፋን ኦሮሞ የተተረጎመው መጽሐፈ ቅዳሴ ሁለተኛው የደስታ ትንሳኤዋ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ወደ ላቲን ቋንቋ የተተረጎመው በሳባ እና በግዕዝ ቋንቋ ሊተረጎም የሚገባው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያኗ ለወደፊት ልታስብበት ይገባል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው በአስተላለፉት መልእክት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ለዚህ ታላቅ የአፋን ኦሮሞ ቅዳሴ ምረቃ በአል የበኩልን ድጋፍ ያደረገ መሆኑን በመጠቆም ሀገረ ስብከቱ ለወደፊቱም በመጽሐፉ ስርጭት ወቅት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የአፋን ኦሮሞ መጽሐፈ ቅዳሴ ትርጉም ሥራ ተጠናቆ እና ታትሞ ለምረቃ የቀረበውን ባለ ሦስት ኮለን አስራአራቱን ቅዳሴያት የያዘውን አንድ ጥራዝ መጽሐፍ የተቀመጠበትን መሶብ ወርቅ በመክፈት ባርከው በይፋ መርቀዋል፡፡
የመጽሐፉ ይዘት ባለ ሶስት ኮለን ሲሆን አንዱ ኮለን በሳባ ፊደል አንዱ ኮለን በቁቤ ፊደል አንዱ ኮለን በግዕዝ ፊደል የተከፈለ ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በምረቃው ለተሰበሰበው ታዳሚ የሚከተለውን አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ወተመልኡ ኵሎሙ መንፈሰ ኃይል ወአኃዙ ይንብቡ ዘዘዚአሆሙ በነገረ ኩሉ በሐውርት በከመ ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ ይንብቡ ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስ ቀዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠንም በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ›› (የሐ.ሥራ.2÷4)
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በሐምሳኛው ዕለት ባረገ በዐሥረኛው ቀን፤ በሃይማኖት ፍጹማን፤ በማስተማር ጥቡዓን፤ በዕውቀት ማእምራን የሚያደርግ መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ ለሐዋርያት ወረደላቸው፣ የዓለምን ቋንቋ ሁሉ እንዲናገሩም ዕውቀት ሰጣቸው ፡፡
ሐዋርያት፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሰጣቸው መንፈሳዊ ጥበብና ቋንቋ የዕውቀት ባለቤቶች ሆነው እንዲታዩበት ወይም ለራሳቸው እንዲገለገሉበት ሳይሆን ‹‹ሑሩ ወመሀሩ ውስተ ኵሉ አጽናፈ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ›› ብሎ ባዘዛቸው መሠረት ሁሉንም ኅብረተሰብ በየቋንቋው ማስተማር ይችሉ ዘንድ እንደሆነ እናውቃለን (ማር16÷15) ፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከለኛው ምሥራቅ በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም የመሠረተውን ትምህርተ ክርስትና በሚያስተምርበት ወቅት ከጊዜ በኋላ በመላው ዓለም እንደሚዳረስ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ ገልጾ ነበር፤ (ማቴ. 24÷14)
ከዕርገቱ በኋላም ሐዋርያትና ሰብዐ አርድእት በአንድነት ትምህርተ ወንጌል በመላው ዓለም እንዲሰራጭ አድርገዋል ፡፡ ትምህርታቸውም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀባይነትንና መልካም ፍሬን እያገኘ በመሄዱ በጥቂቶች ሰባክያንና መምህራን የክርስትናው ሃይማኖት መካከለኛውን ምሥራቅ አዳርሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ እስያን፣ አውሮፓንና ምድረ አፍሪካን እንዳዳረሰ በቅዱስ መጽሐፍም በታሪክም ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ትምህርተ ወንጌል በዚህ አኳኋን ደረጃ በደረጃ እየተጓዘ አሁን ላለው የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ደርሶአል ፡፡
ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት መሠረት የሆነው ቅዱስ መጽሐፍ በአሁኑ ዘመን ኅብረተ ሰቡ በቀላሉ ሊረዳ በሚያስችለው አኳኋን በተብራራ መልኩ በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሞና ተባዝቶ በሁሉም የዓለም አቅጣጫ ለሰው ልጅ ሁሉ እንዲዳረስ ተደርጓል ፡፡
የክርስትናው ሃይማኖት መገልገያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስትናው እምነት መስፋፋትና ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ መተኪያ የለውም፤
ቅድመ ልደተ ክርስቶስም ሆነ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ የተነሡት መንፈሳውያን አባቶቻችን በየጊዜው ዘመኑ የፈቀደላቸውን ያህል ታላላቅ ሥራዎችን በመሥራት ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበትን ተግባር እየፈጸሙ አልፈዋል፤ እኛም ቀደምት አባቶታችን ባቆዩልን አሠራር መሠረት የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን ምእመናን ለመጠበቅና ለማስተማር በአባቶቻችን ቦታ ተተክተናል ፡፡
በዚህ በተሰየምንበት ኃላፊነት የቤተ ክርስቲያን ዓላማን ከግብ ለማድረስና ሕዝባችንም የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ እንዲሆን ለማድረግ፣ በቅዱስ መጽሐፍ እንደታዘዘው ምእመናንን በለመለመው የሃይማኖት መስክ ላይ ለማሠማራት፣ ከእግዚአብሔርም ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ፣ ትልቁ ተልእኮአችንን ለመወጣት፣ ጥረት በማድረግ እንገኛለን ፡፡
ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩና የተለያየ ባሕል ያላቸው ልጆች አሏት፤ እነዚህም ልጆቻችን በቋንቋቸው አምላካቸውን ማመስገን ይችሉ ዘንድ ማስተማርና ለእግዚአብሔር መንግሥት ማዘጋጀት ተቀዳሚ የቤተ ክርስቲያን ተግባር ነው ፡፡
በመሆኑም የኦሮሞ ብሔረሰብ ምእመናን ልጆቻችን በአሁኑ ወቅት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አምልኮአቸውን መፈጸም እንዲችሉ፣ በቋንቋቸውም እንዲያስቀድሱና እግዚአብሔርንም እንዲያመሰግኑ ታስቦ በሦስት ዓምድ ተከፋፍሎ የተተረጎመውና በዛሬው ዕለት ለምረቃ የቀረበው ዐሥራ ዐራቱ የአፋን ኦሮሞ መጽሐፈ ቅዳሴ ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉን አቀፍና ሁሉን በእኩል የምታገለግል መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ለብዙ ጊዜ ሲደከምበት ቆይቶ አሁን በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ታትሞ በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው መጽሐፈ ቅዳሴ የክልሉን ምእመናን መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟላ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስኬት ስለሆነ መላው የኦሮሞ ክልል ምእመናን ልጆቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላቸዋለን ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር የመሆኗን ያህል በዚያው መጠን የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩባት የሚታወቅ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያናችን  በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንና ምእመናት እንዳደረገች ሁሉ ለሌሎች ብሔር ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች ምእመናን ልጆቻችንም በተመሳሳይ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣትመጽሐፈ ቅዳሴውን በየብሔረሰቡ ቋንቋ እያስተረጐመችና እያሳተመች አገልግሎት ላይ ማዋል ቋሚ ዓላማዋና ተቀዳሚ ተልእኮዋ ስለሆነ በስፋት ትቀጥልበታለች፤ በመሆኑም ሁሉም የኅብረተ ሰብ ክፍሎች የዕድሉ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑ በዚህ ኣጋጣሚ ልናረጋግጥላቸው እንወዳለን ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግእዝና በአማርኛ ቋንቋ እየታተመ አገልግሎት ሲሰጥ የኖረውና አሁንም እያገለገለ ያለው መጽሐፈ ቅዳሴ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጐመ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ምእመናን አገልግሎት እንዲውል በወሰነው መሠረት እነሆ ዐሥራ ዐራቱን መጽሐፈ ቅዳሴ በአፋን ኦሮሞ አስተርጉሞና አሳትሞ ለአገልግሎት ማብቃት ተችሎአል ፡፡
ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ የማስፋፋትና የማዳረስ አቅም እንደሚያጎለብት የታመነበት ከመሆኑም በላይ ለሌሎች የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ምእመናን ልጆቻችን አርአያ ሆኖ የሚያገለግል ስለሆነ ሌሎች ብሔረሰቦች ሁሉ በዚህ ደስ ሊላቸው ይገባል እንላለን ፡፡
የመጽሐፉ ዝግጅት ከመጽሐፉ አንጻር ረዥም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም ልዩ ልዩ ፈተናዎችን በማለፍ ለሕትመት እንዲበቃ ያደረጉት የክልሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንደዚሁም በዚህ የትርጉም ሥራ ላይ ከኮሚቴነት እስከ ተርጓሚነት ከዚያም እስከ አርትዖት የተሳተፉትንና የደከሙትን ሊቃውንቶቻችንና ምሁራን ልጆቻችን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ሳናመሰግናቸው አናልፍም ፡፡
ከዚህም ጋር ይህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ትልልቅ መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር  ያደረጋችሁ የበዓሉ አዘጋጅ ልጆቻችንም እናመሰግናችኋለን ፡፡
ይህ መጽሐፈ ቅዳሴ በከፍተኛ ድካምና ወጪ ታትሞ የቀረበው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ምእመናን ልጆቻችን ሃይማኖታቸውን እንዲማሩበትና እንዲያውቁበት፣  እንዲቀድሱበትና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩበት ታስቦ ስለሆነ ይህን መሠረታዊ ግንዛቤ በመጨበጥ ከዛሬ ጀምሮ በክልሉ የምትገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ኃላፊዎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት መጽሐፉን ለየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ በማከፋፈልና በማሰራጨት፣ እንደዚሁም የክልሉ አገልጋዮች ሁሉ እንዲያጠኑትና እንዲለማመዱት በማድረግ ሕዝቡ እንዲማርበትና እንዲገለገልበት ታደርጉ ዘንድ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፊ የሆነ አባታዊ መልዕክት አስተላልፈው ጉባኤውን መርሐ ግብሩን በጸሎት ዘግተዋል፡፡