“የቤትህ ቅናት አቃጠለኝ”
በመምህር ሣህሉ አድማሱ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አስተምሕሮ መሠረት በጾመ ኢየሱስ (ዐቢይ ጾም) ከሚከበሩት የሳምንታት በዓላት መካከል ሦስተኛው ሳምንት “ምኩራብ” በመባል ይታወቃል፡፡
የበዓሉ መታሰቢያ የሚታሰበው በዋናነት በዕለተ እሁድ ሲሆን በዚህ ዕለት በሌሊቱ ማሕሌታዊ ሥርዓት ወቅት “ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ…” የሚል የቅዱስ ያሬድ ድርሰት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዜማ ይቀርባል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴው ወቅት ደግሞ ቆላ. 2÷16-ፍ፣ ያዕ. 1÷14፣ የሐዋ. 10÷1-9፣ መዝ. 68÷9፣ ዮሐ2 2÷12 በዲያቆናትና በቀሳውስት በዜማና በንባብ ይቀርባል፡፡
በመዝሙረ ዳዊትና በወንጌሉ የተጻፈው እንደሚከተለው ተብራርቷል፡፡ “እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልአኒ፤ ትእይርቶሙ ለእለ ይትኤየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፣ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ” የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና፡፡ ነፍሴን በጾም አስመረርኳት፣ (መዝ. 68÷9)
በደራሲው በቅዱስ ዳዊት ያደረበት መንፈሳዊ ቅንዓት የዳዊት ልጅ ተብሎ በተጠራው በመሲሕ ክርስቶስም ተገልጾአል (ዮሐ. 2÷17) እግዚአብሔርን የሚሰድቡ የእግዚአብሔርን አገልጋይም ይሰድባሉ (መዝ. 89÷50) በምድራዊ ሕገ መንግሥት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ድንጋጌ ላይ ስድብና ማዋረድ ወንጀል ነው ተብሎ ተመዝግቧል፡፡ በሰማያዊ በእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ደግሞ ሰውን መሳደብ ኃጢአት መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ “… ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጐ ፍርድ ይገባዋል፣ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል፡፡” በማርቆስ ወንጌል 7÷22 ላይ መድኃኒት ክርስቶስ ሲያስተምር የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት ከሚአረክሱት የኃጢአት ሥራዎች መካከል ስድብ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ምእመናን ባስተላለፈው ሐዋርያዊ መልእክት የስድብን ኃጢአት እንዲአስወግዱ መክሯቸዋል፡፡ (ኤፌ. 4÷31) የእግዚአብሔር የሆነ ግን አይሳደብም “እንግዲህ እነዚህ ሰዎች እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ፡፡ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገጽፅህ አለው እንጂ የስድብ ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ፡፡
ወዮላቸው! በቃየል መንገድ ሂደዋልና ስለደመወዝም ለበለዓም ስህተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል፡፡ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፡፡ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፡፡ በነፋስ የተወሰዱ፣ ውሀ የሌላቸው ደመናዎች፣ ፍሬ የማያፈሩ፣ ሁለት ጊዜ የሞቱ፣ ከነሥራቸው የተነቀሉ፣ በበጋ የደረቁ ዛፎች፣ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባህር ማዕበል፣ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም የተበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው፡፡” (ያዕ. 8-13) እነዚህ ወገኖች ከእግዚአብሔር ተቀበልነው የሚሉት የረከሰ ህልም ነበራቸው፡፡ ርኩሰታቸውንም ትክክል ለማድረግ በእነዚህ ህልሞቻቸው በመጠቀም ታላላቅ ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሥልጣን ይንቃሉ፡፡ መንፈሳዊ አእምሮ የላቸውም፡፡
ስለዚህ ለገዛ ኃጢአታቸው አሳልፎ ይሰጣቸዋል (ሮሜ 1÷28) ወንድሙን እንደገደለው እንደ ቃኤል (ዘፍ. 4÷1) ገንዘብ ወዳድ እንደሆነ እንደበለዓም (2ጴ. 2÷15) ናቸው፡፡ ምንም ዝናብ እንደማይሰጥ ደመና ናቸው፡፡ የፀሐይን ብርሃን ከመጋረድ በቀር ለምንም አይጠቅሙም፡፡
መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ኃጢአቱ አይሰረይለትም፡፡ (ማቴ. 12÷31) ሰው ወደዚህ ሁኔታ የሚደርሰው እንደፃፎች የእግዚአብሔርን ሥራ ለሰይጣን ሰጥቶ የሰይጣንን ሐሳብ ሲከተል ነው (ማር. 3÷22) ሰው መንፈስ ቅዱስን ከመንቀፍ ደረጃ ሲደርስ ልቡ ይደነድናል፡፡ የእግዚአብሔርንም ነገር አይፈልግም፣ ንስሐም አይገባም፣ ይቅርታም አይጠይቅም (ዕብ. 6÷4)
ከዚህ በላይ የተብራራው ታሪክ በደራሲው በቅዱስ ዳዊት የተነገረው ቃል መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በዮሐንስ ወንጌ ምዕራፍ 2÷17 ላይ የተጻፈውን ዝርዝር ሐሳብ እንደሚተለው አንመለከታለን፡፡ “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በመቅደስም በሬዎችንና በጐችን፣ ርግቦችንም የሚሸጡትን፣ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኙ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ በጐችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ሻጮችንም ይህን ከዚህ ወሰዱ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም “የቤትህ ቅናት አቃጠለኝ ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡”
ይህ ታሪክ በተፈጸመበት ወቅት በየዓመቱ በርካታ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዳሉ (ሉቃ 2÷4) መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ በዓመቱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ በደረሰ ጊዜ ነጋዴዎች ለመስዋዕት የሚቀርቡ እንስሳትን በቤተመቅደስ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲሸጡ አየ፡፡
ለአምልኮ ወደ ቤተ መቅደስ የሚሄዱ ሰዎች ለቤተመቅደስ የሚሰጡትን ገንዘብ በዚያው በቤተ መቅደስ ውስጥ ይለውጡ (ይመነዝሩ) ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ነጋዴዎች በቤተመቅደሱ ውስጥ ሲነግዱና ትርፍ ሲአጋብሱ አይቶ እጅግ በመቆጣት በገመድ ጅራፍ እየገረፈ አባረራቸው፡፡
ስለዚህ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ከለዋጮች አጽድቷል፡፡ ክርስቶስ ገንዘብ ለዋጮችን ከቤተ መቅደስ ሲአስወጣ በመዝሙር 69÷9 ላይ “የቤትህ ቅንዓት እንደ እሳት አቃጠለኝ” ተብሎ የተጻፈው ቃል ተፈጸመ፡፡
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የገበያ ስፍራ፣ መሸጭና መለወጫ ማድረግ እግዚአብሔርን አለማክበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት የአምልኮና የጸሎት ቤት እንጂ የገንዘብ መለወጫ (ምንዛሬ) ቤት አይደለም፡፡