የጣሊያን ሪፐፕሊክ ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ማታሬላ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አደረጉ

0062

የተከበሩ ሚስተር ሰርጊዮ ማታሬላ የጣሊያን ሪፐፕሊክ ፕሬዝዳንት ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ተገኝተው ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጋር በአካባቢ ጥበቃ፣ በስደተኞች ጉዳይ እና በጋራ መልካም ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በ20ዎቹ ዓመታት ውስጥ የተደረገው የሁለቱ አገራት ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ እና በስደተኞች ጉዳይ የምታደርገውን እንቅስቃሴ መንግሥታቸው እንደሚደግፍ አብራርተዋል፡፡
የጣሊያን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት  ሲያደርግ የነበረው በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ቤተክርስቲያን በኩል መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝደንት ሰርጊዮ ማታሬላ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ውይይቱን ባካሄዱበት ወቅት የጣሊያን ሪፐፕሊክ የትምህርት ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በበኩላቸው ለፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር የአክሱም አውልት ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ መደረጉ የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሳዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው ፕሬዝደንቱ ከመንበረ ፓትርያርክ ድረስ በመምጣት ላደረጉት ጉብኝትና የጋራ ውይይት ላቅ ያለ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለፕሬዝደንት ሰርጊዮ ማታሬላ መንፈሳዊ ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡ በተመሳሳይም ፕሬዝደንት ሰርጊዮ ማታሬላ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጣሊያንን ቤተ መንግሥት የሚያሳይ ዲዛይን ያለው ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡