የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰባክያነ ወንጌል ፈተና ሰጠ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከተ በስሩ ላሉት ገዳማትና አድባራት ሰባክያነ ወንጌል ለመመደብ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈተና ሰጠ፡፡ ሀገረ ስብከቱ የመግቢያ ፈተናውን ያዘጋጀው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤና ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በተውጣጡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡
ለፈተናው ከተመዘገቡት አመልካቾች መካከልም በትምህርት ማስረጃቸው የተመረጡ 64 እጩዎች ለፈተና ተቀምጠዋል፡፡ በፈተናውም በዘመናዊ ትምህርት እስከ ማስተርስ ዲግሪ በመንፈሳዊም የአብነት ትምህርት ምሥክር የሆኑ ሊቃውንት ተሳትፈዋል፡፡ የፈተናውም ሂደት በጽሑፍ የተሰጠ ሲሆን ፈተናውን ያወጡት ሊቃውንት እዚያው በመሰብሰቢያ አዳራሽ ተመካክረው ለኩረጃ በማይመች መልኩ ስላወጡት ከሐሜትና ከአሉባልታ የፀዳ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰው ኃይል ቅጥርን በፈተናና በእውቀት ላይ የተመሠረተ አድርጐ በመሥራቱ ከተለያዩ ሊቃውንት፣ ካህናት እና ምእመናን ምስጋና እየተቸረው ከመሆኑም በላይ ሀገረ ስብከቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ ቀደም በርካታ ሊቃውንት በፈተና በገዳማትና አድባራት መቀጠራቸውና መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማሻሻል መቻሉ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና ሀገረ ስብከቱ በወሰደው ቁርጥ አቋም በርካታ ሊቃውንት ማለትም የድጓ፣ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የመጽሐፍ፣ የዝማሬ መዋስዕት እና የቅዳሴ መምህራን በፈተና በመመደባቸው በሀገረ ስብከቱ ሥር ባሉ አድባራት ገዳማትና ካቴድራሎች በያዝነው ዓመት በዓቢይ ጾም ሙሉ ጾም ምዕራፍ እና ድጓ እንዲቆም ለገዳማት፣ አድባራትና ካቴድራሎች መመሪያ የሰጠ ሲሆን ገዳማትና አድባራቱም ተግባራዊ ማድረጋቸውን እና በሁሉም ቦታ ሙሉ ጾም ምዕራፍ እንዲሁም ሰዓታት እየተቆመ ከመሆኑም ባሻገር ከቀኑ 5፡30 ጀምሮ ሥርዓተ ቅዳሴው እስከሚጀመር ድረስ የወንጌል አገልግሎት በስፋት እየተሰጠ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡