አሥሩ ማዕረጋት

በመጋቢ አእላፍ ቀሲስ ፋሲል ታደሰ የቀበና ም/ፀሐይ መድኃኒዓለም ቤ/ክ/ስ/ወ/ኃላፊ
ማዕረግ ማለት ክብር፣ ሥልጣን ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን በገድልና በትሩፋት ብዛት የሚያገኟቸውን ዐሥር ማዕረጋትና ከዐሥር ቁጥር ጋር ያላቸውን ተያያዥነት እንመለከታለን፡፡
ቁጥር ምንድን ነው?
በዕብራይስጥ ብዛትን ሲገልጥ ቁጥር በፊደል እንጂ በአኃዝ ምልክት ብዙ ጊዜ አልተጻፈም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቁጥር አጠቃቀም ሌላ ነገር አለ፤ ይኸውም ቁጥሮች አንዳንድ ጊዜ የነገር፣ የሰውን ወይም የዘመንን ሁኔታ እንጂ ብዛትን አያመለክትም፡፡ ይህም በተለየ በዮሐንስ ራእይ ይታያል፡፡ ሆኖም ስለ ቁጥር አተረጓጎም የሊቃውንቱ ሀሳብ ብዙና የተለያየ ነው፡፡
ዐሥር ቁጥር
ዐሥር የሙላት ቁጥር ነው፡፡ አንድን ሙሉ የሆነ ነገር የሚያሳይ ተምሳሌት ነው፡፡ ይህንንም አባባል በመጽሐፍ ቅዱስ ካሉ ታሪኮች ጋር በማዛመድ እንደሚከተለው ማብራራት ይቻላል፡፡
ከጥፋት ውኃ በፊት ዐሥር ሰዎች /ዘፍ. 5/
በግብጻውያን ላይ የተከሰቱ ዐሥሩ መቅሰፍቶች
እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ዐሥርቱ ትእዛዛት
ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚከለክሉ ዐሥር ኃጢአቶች፤ /1ኛቆሮ 6፥9-10/፡፡
ከእግዚአብሔር ሊያርቁን የሚችሉ ዐሥር ኃይላት፤ (ሮሜ 8፥38-39/፡፡
ዐሥሩ ደናግል
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 15፥31 ላይ “በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያል” በማለት እንደተናገረ በመልካም ሥራቸው ለዘለዓለም እንደ ከዋክብት ደምቀው የሚኖሩ ቅዱሳን በሠሩት ገድልና ትሩፋት መጠን የአንዳቸው ክብርና ሥልጣን ከሌላው ይለያል፡፡ /ዳን 12፥3፤ ራእ12፥1-4/፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የገበሬና የዘር ምሳሌ ላይ “ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ወደቀ አንዱም መቶ፣ አንዱም ስድሳ፣ አንዱም ሰላሳ ፍሬ ሰጠ” ብሏል፡፡ /ማቴ 13፥8/ ዘር የተባለው ቃለ እግዚአብሔር ሲሆን መልካም መሬት የተባሉት ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ፍሬ ሃይማኖትና ፍሬ ምግብር የሚያፈሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ 3፥9 እነርሱም እንደሥራቸው መጠን 30፣ 60፣ 100/ /ሠላሣ፣ ስልሣ፣ መቶ/ ፍሬ ያፈራሉ ወይም የተለያየ ክብርና ሥልጣን ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ የቅዱሳን ማዕረጋት የሚወሰኑት በሕይወት ዘመናቸው በፈጸሙት ገድልና ትሩፋት መጠን ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍትም እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን እንደሚከፍለው በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ /መዝ 51፥12፤ ምሳ 14፥12፤ ማቴ 16፥17፤ ሮሜ 2፥6፤ ራእ 10፥12/፡፡
ቅዱሳን የደረሱበት ማዕረጋት ዐሥር እንደሆኑ በመጻሕፍተ መነኮሳት ተገልጧል፡፡
ዐሥሩ ማዕረጋት የሚባሉትም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.ጽማዌ 2.ልባዌ 3.ጣዕመ ዝማሬ 4.አንብዕ(አንብዐ ንስሐ)5.ኩነኔ 6.ፍቅር 7.ሑሰት 8.ንጻሬ መላእክት 9.ተሰጥሞ 10.ከዊነ እሳት እነዚህ ቅዱሳን የደረሱበት ዐሥሩ ማዕረጋት የንጽሐ ሥጋ፣ የንጽሐ ነፍስ፣ የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት በመባል በሦስት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ተሰ 5፥12-14 ላይ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ (ልቦናችሁም) መንፈሳችሁም፣ ነፍሳችሁም፣ ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” ማለቱ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ልቡና፣ ንጽሐ ነፍስ ይኑራችሁ፣ ከኃጢአት ከነቀፋ የተጠበቃችሁ ሁኑ ማለት ነው፡፡
በቀጣይ ጊዜያት በሦስት ክፍል የተከፈሉ የቅዱሳን ደረጃዎችን በጥልቀት ለማየት እንሞክራለን፡፡ ንጽሐ ሥጋ ማዕረጋት ሦስት ናቸው እነሱም ጽማዌ፣ ልባዌ፣ ጣዕመ ዝማሬ ሲሆኑ፤ እነዚህ ማዕረጋት ላይ የደረሱ ቅዱሳን 30 (ሠላሣ) ፍሬ በሚያፈራው ዘር የተመሰሉት ናቸው፡፡
ጽማዌ
ጽማዌ ማለት ድንቁርና ማለት ነው፡፡ እንደ ሰው ጆሮው ቢደነቁር በዓለም ያለውን ማንኛውንም ድምፅ አይሰማም የልቡን ሐሳብ ብቻ ያዳምጣል፡፡ በጽማዌ ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን በዓለም ላይ እያሉ የዓለምን ማንኛውንም ነገር ለመስማት አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን በሕሊናቸው ነገረ እግዚአብሔርን ያስባሉ፣ በአፍንጫቸው መዓዛ ገነትን ያሸታሉ፡፡ እዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ በዐይናቸው ሥውራን ዓለማችን፣ ግሩማን አራዊትን፣ ከሥጋዋ የተለየች ነፍስን፣ አጋንንትን ለመለየት ይችላሉ፡፡ እንዲሁም በዚህ ዓለም ለተልእኮ የሚመላለሱ መላእክትን የማየት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ነገር ግን የተገለጡላቸው መላእክት የሚሠሩትን፣ የሚናገሩትን እንዲሁም እነማን እንደሆኑ ስማቸውን ለይተው ስለማያውቁ ጽሙም ተብለዋል፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ጽሙም የተባሉበት ምክንያት ጆሮዋቸው በተፈጥሮ ችግር ምክንያት መስማት ተስኖት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
እዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ አባቶች በመንፈስ ቅዱስ መግቦት ይኖራሉ እንጂ፤ ራሳቸው ጥረው ግረው አይመገቡም፡፡ እናነባለን፤ እንዘምራለን፤ ከሰው ጋር እንነጋገራለን አይሉም፡፡ ዓለምን ከማሰብ ይለያሉ፡፡ ቀንና ሌሊት ምንም ሳይበሉና ሳይጠጡ መጾማና መጸለይ ይችላሉ፡፡ ለዚህም አብነት የምናደርገው ሊቀ ነቢያት ሙሴን ነው፡፡ ሙሴ ቀንና ሌሊት ምግብ ሳይመገብ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ቆይቶ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ተቀብሏል፡፡ /ዘጸ 9፥9¿¿፤ “4፥17-18፤ 1ዮሐ 2፥15-17/፡፡
ልባዌ
ልባዌ ማለት ልብ ማድረግ፣ ማስተዋል፣ ዕውቀት፣ የልብ አስተያየት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ማዕረግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን የሕሊና ጾር በተነሣባቸው ጊዜ (ክፋ ምኞት ሲታሰብባቸው) መስቀል ተክለው ይሰግዳሉ፤ ጌታ ሆይ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሲገንዙህ ሲቀብሩህ እንዲህ ተንከባለልህ እያሉ በማዘንና በማልቀስ ይንከባለላሉ፡፡ ሥጋዊ ነገርን በማሰብ ጸጋቸው እንዳይነሣቸው ሕሊናቸው ነገረ መስቀልን ከማሰብ እንዲለይ አይፈልጉም፡፡ በባዐታቸው ጸንተው ቢኖሩም የሚፈልጉትን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ፈጥኖ ይሰጣቸዋል፡፡ እንዲሁም ነፍስ ከሥጋ ተለይቶ ወዴት እንደምትሔድ ያያሉ፤ መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ፣ ተልእኳቸውንና እነማን እንደሆኑም ጭምር ስማቸውን ለይተው ያውቃሉ፡፡ አጋንንትንም የማየትና ለምን እንደተላኩ የማወቅ ጸጋ ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ከሚሰውራቸው አንዳንድ ነገሮች በስተቀር ከጠፈር በታች ያለውን ማቸውንም ነገር ሳይጠይቁ ይረዳሉ፡፡ /ዳን 9፥11-13፤ 2ኛ ቆሮ 12፥1-7፤ገላ 6፥4/፡፡
ጣዕመ ዝማሬ
አባቶች እዚህ ማዕረግ ላይ ሲደርሱ የሚጸልዩትን ጸሎት አንድ በአንድ ምስጢሩን ያውቃሉ፡፡ የአቡነ ዘበሰማያት ምስጢር አላልቅ ብሏቸው ለ30ዓመት የሚቆዩ አሉ፡፡ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ቁመት አይሰለቻቸውም ሲዘምሩ ድምፃቸው እንደ መላእክት ይሆናል፤ ቀንና ሌሊት ያለ ዕረፍት ያመሰግናሉ፡፡ የራሳቸውም ድምፅ እንደ መላእክት ዝማሬ አይሰለቻቸውም፡፡ ክብራቸውን ለመሰወር ካልሆነ ካልፈለጉ በስተቀር ሥጋዊ ምግብ አይመገቡም፤ አያንቀላፉም፡፡ እዚህ ማዕረግ ላይ በደረሱ አባቶች ሰይጣናት ከዚህ ዋሻ ውስጥ እንደሽኮኮ ተሸጉጠህ ትኖራለህን ከተማ ገብተህ ቀድሰህ፣ ዘምረህ፣ አስተምረህ አትኖርምን የሚል የኅሊና ፈተና ያመጡባቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ ልቡናቸው ከውዳሴ ከንቱ ተለይቶ በአጽንዖ በዐት የቆየ እንደሆነ የንጽሐ ነፍስ ማዕረጋት ይሰጣቸዋል፡፡
የነፍስ ንጽሕና (ማዕከላውያን)
የንጽሐ ነፍስ ማዕርግ ሥጋ የሚረሳበት፣ የነፍስ ኃጢያት የሌለበት ጊዜ ነው፡፡ በንጽሐ ነፍስ ጊዜ በተባሕትዎ ጸንቶ በኖረ ሰው ጸጋ እግዚአብሔር ያድርበታል፡፡ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች በዐይነ ሥጋ ለማየት የማይችሉትን የልዑል ብርሃንንና ምስጢርን ያያል፡፡ ነገር ግን ልዩ ጾር (ፈተና) ይታዘዝበታል፡፡ ትሩፋትን መተው፣ ተስፋ መቁረጥ፣ በዐቴን ጥዬ ልውጣ ማለት መጠራጠር፣ አይምረኝም፣ አያድነኝም የማለት ሐሳብ ይመጣበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ከጾሩ ብዛት የተነሣ ከጽናቱ ሳይናወጽ፣ እግዚአብሔር ያድነኛል በማለት በሃይማኖት ከጸና ክብሩ (ጸጋው) አይለየውም፡፡ በንጽሐ ነፍስ ማዕርግ ላይ ያሉት 60 (ስልሣ) ፍሬ ባፈራው ዘር የተመሰሉ ናቸው፡፡ የንጽሐ ነፍስ ማዕርጋት የሚባሉት እንብዕ (አንብዐ ንስሐ)፣ ኩነኔ፣ ፍቅር፣ ሑሰት ናቸው፡፡
አንብዕ
እዚህ ማዕርግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን የዕንባ ሀብት ይሰጣቸዋል፡፡ ሳያቋርጡ ያነባሉ (አንብዐ ንስሐ)፤ ዐይናቸው ግን አይጠፋም፤ ዕንባቸው ሌሊትና ቀን አያቋርጥም፤ አንብዐ ንስሐ ማዕርግ ላይ የሚደርሱ ቅዱሳን አብዛኛውን ጊዜ የሚጸልዩት በሕሊና እንጂ፤ በድካም አይደለም፡፡ ይኽም በሕሊናቸው የሚመላለስ ረቂቅ ጸጋ ስለኾነ ኃጢአትን ያስወግድላቸዋል፡፡ እርጥብ እንጨትን በእሳት ላይ ቢጥሉት እየነደደ ውኃ እንደሚወጣው ሁሉ በሀብት አንብዕ ደረጃ ላይ ያሉ ቅዱሳንም ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን፣ ምረረ ገሃነመ እሳትን እያሰቡ በልቦናቸው ከሚቀጣጠለው መንፈሳዊ ጸጋ እሳት የተነሣ የጸጋን ዕንባ ያነባሉ (ያፈሳሉ)፡፡ /ማቴ 5፥4፤ ሉቃ 6፥11፤ የሐዋ 10፥1፤ ሮሜ 12፥11/፡፡
ኩነኔ
ኩነኔ ማለት አገዛዝ፣ ግዛት ማለት ነው፡፡ እዚህ ማዕርግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን የነፍስ ፈቃዳቸው የሥጋ ፈቃዳቸውን ይገዛል፤ ያሸንፋል፡፡ በሰው ሕይወት የሥጋና የነፍስ ፈቃዳት ሁልጊዜ ይቃረናሉ፡፡ /ገላ 5፥16-17/፡፡ የነፍስ ፈቃድ እያሸነፈ ሔዶ ሥጋን በቁጥጥር ሥር የሚያውልበት፣ ነፍስ የመንፈስ ቅዱስን ፈቃድ ብቻ በመፈጸም የምትጀምርበት ማዕርግ ኩነኔ ነው፡፡ የሥጋቸው ፈቃድ በፈቃደ ነፍሳቸው ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አይኖረውም፡፡ በሐሳብም ከመበደል ይጠበቃሉ፡፡ የሲዖልንና የገሃነመ እሳትን ኩነኔ እያሰቡ ያዝናሉ፡፡ ቅዱሳን አባቶች፣ በዚህ ማዕርግ ላይ የደረሰ ሰው ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን ያስባል፤ መከራ ለመቀበልም ዝግጁ ይሆናል፤ ብለው ያስረዳሉ፡፡ /ሮሜ 7፥15-18፤ 1ቆሮ 9፥17፤ ገላ 5፥14-16፤ ኤፌ 2፥1/፡፡
ፍቅር
እዚህ ማዕርግ ላይ የሚደርሱ አባቶች ሁሉን የመውደድ ሀብት ይሰጣቸዋል፡፡ እነርሱንም ሁሉ ይወዳቸዋል፡፡ በእነዚህ አባቶች ዘንድ ይህ ጌታ ነው፣ ይህ ባሪያ ነው፣ ይህ ግዙር ነው፣ ይህ ቆላፍ ነው፣ ይህ ወንድ ነው፣ ይህች ሴት ናት፣ ይህ ደግ ነው፣ ይህ ክፉ ነው፣ ይህ መልከ ቀና ነው፣ ይህ መልከ ክፉ ነው ማለት የለም፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ክርስቶስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል ብለው ሰውን ሁሉ አስተካክለው ይወዳሉ፤ ለሁሉም ይራራሉ፤ የወጡትን በደኅና አግባቸው፤ የሰው ልጆችን ከክህደት ወደ ሃይማኖት፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሳቸው እያሉ ይጸልያሉ፡፡ አዕዋፍ፣ አዞ፣ ጉማሬ በአጠቃላይ እንስሳትና አራዊት አይጣሏቸውም፡፡ ዓመፀኞች አጋንንት ጭምር ይታዘዙላቸዋል፡፡ /መዝ 90፥13፤ ማቴ 5፥33-38፤ ሉቃ 6፥16-20፤ 10፥17፤ 1ኛ ቆሮ 13፥1-13/፡፡
አባ አክሎግ አንበሳዊው የተባለው ቅዱስ ራሱን ይታመም ነበር፡፡ ውኃ ሸግ አድርጎ ማን በሰጠኝ ሲል አንበሳ ሰማው፡፡ አንበሳውም ነጋዴዎች ብላቴናውንና ውኃውን በብርት (በማንቆርቆሪያ) ጭነው ሲሄዱ አየና ከነሱ ነጥቆ ብላቴናውንና ውኃውን አምጥቶ ከፊቱ አቀረበለት፤ አባ አክሎግም አግዚአብሔር ካመጣህስ በል ሸግ አድርገህ ስጠኝ አለው፡፡ ብላቴናውም ሸግ አድርጎ ሰጠው፡፡ ከዚያም አንበሳውን ብላቴናውን ከነብርቱ ወስደህ ስጥ ባለው ጊዜ ወስዶ ሰጥቷል፡፡
ሑሰት
ሑሰት ማለት እንደ እግር ፀሐይ (የፀሐይ ብርሃን) ካሰቡበት ሁሉ መገኘት፤ በሌላ ቦታ የሚሠራውን ባንድ ቦታ ሆኖ ማየት መቻል ማለት ነው፡፡ ይህ ማዕርግ ለማዕከላውያን የመጨረሻው ማዕርግ ነው፡፡ እዚህ ማዕርግ ላይ የደረሱ ቅዱሳን በዓለም በሚደረገው ሁሉ አይሰወራቸውም፡፡ ሁሉንም አንድ ቦታ ሆነው ማየት ይችላሉ ለምሳሌ በአንድ ተመሳሳይ ሰዓት በመላው ዓለም ቅዳሴ ቢቀደስ እነማን እንደቀደሱ እነማን እንደቆረቡ በቅጽበት ያውቃሉ፡፡ በዚህ ማዕርግ ሳሉ ረቂቅ መንፈስ ቅዱስ ስለሚዋሐዳቸው ረቂቃን ይሆናሉ፡፡ በሥጋ ግዙፋን ቢሆኑም ጠፈር ደፈር ሳይከለክላቸው በመስተዋት ብርሃን እንደሚያልፍ ማለፍ ይችላሉ፡፡ /2ኛነገ 6፥8-13፤ኢሳ30፥17-21፤የሐዋ5፥1-11፤1ቆሮ12፥1-5/፡፡
እነዚህ ቅዱሳን ዓለመ መላእክትን፣ ገነትን፣ ብሔረ ሕያዋንን፣ ብሔረ ብፁዓንን ጎብኝተው መምጣት ይችላሉ፡፡ የብርሃን መንኮራኩር (ሰረገላ) እና ክንፈ ጸጋ ይሰጣቸዋል፡፡
ንጽሕ ልቡና (ፍጹማን)
አንድ ሰው ንጽሐ ልቡና ላይ ሲደርስ ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ ወደ መላእክት ዓለም ትሔዳለች ነገር ግን ዐይኑ እንደማንኛውም ሰው ያያል ሰውነቱም ይሞቃል፤ እንደሞተ ሰው ዐይኑ አይጨፈንም፡፡ ነፍሱ ግን ለተወሰነ ጊዜ ከመላእክት ጋር እግዚአብሔርን እያመሰገነች በጣዕመ ዝማሬ ተመስጣና ተደስታ ከቆየች በኋላ ትመለሳለች፡፡ መላእክት ግን ይህቺ ነፍስ ከእነርሱ እንድትለይ አይፈልጉም፡፡ እነዚህም 100 (መቶ) ፍሬ በሚያፈራው ዘር የተመሰሉ ናቸው፡፡ የንጽሐ ልቡና ማዕርጋት የሚባሉት ንጻሬ መላእክት፣ ተሰጥሞ እና ከዊነ እሳት ናቸው፡፡
ንጻሬ መላእክት
ንጻሬ ማየት ማለት ነው፡፡ ንጻሬ መላእክት ማለት መላእክትን ማየት ማለት ነው፡፡ ወጣንያንስ መላእክትን ያዩ የለምን; የልባዌ ማዕርግ ላይ የደረሱስ መላእክትን እያዩ እነማን እንደሆኑ ለምን እንደመጡ ያውቁ የለምን? ቢሉ እነዚያ መላእክትን የሚያዩት በዚህ ዓለም ሆነው ነው፡፡ ንጻሬ መላእክት ላይ የደረሱ ግን መላእክትን በዓለማቸው እየገቡ፣ በዚህም ዓለም ሆነው በተመስጦ እላይ የመላእክት ዓለም እየገቡ ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ነፍሳቸው ብቻ ወይም ከሥጋቸው ወደ መላእክት ዓለም ሂደው እያንዳንዱን ከተማ ይጎበኛሉ፤ ዜማቸውንም ይሰማሉ፤ ምስጋናቸውም ከመላእክት ጋር አንድ ሆኖ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ እያሉ አብረው ያመሰግናሉ፡፡ ረቂቃን የሆኑት መላእክት አካል ገዝተው ዳመና ዳመና አክለው ይታዩዋቸዋል፡፡ ከመላእክት ማዕርግ ላይ ይደርሳሉ፤ የመላእክትን መኖሪያና ክብር እያዩ ያደንቃሉ በመላእክት ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ /11ኛ ቆሮ 6፥3፤ ራእ 12፥8-9፤ 1ኛ ቆሮ 13፥1/፡፡
ከዚህ ማዕርግ በታች ያሉ ወጣንያን እንኳን በጸጋ በመላእክት ቋንቋ መናገር ይችሉ የለምን? ቢሉ ልዩነቱ ወጣንያን ከፍቅር ማዕርግ ላይ ሳይደርሱ ነው፡፡ ኅሊና ግን ከፍቅር ማዕርግ ደርሰው ነው፡፡ ይህ ማዕርግ ከሑሰት ይበልጣል፡፡ እዚህ ማዕርግ ላይ የሚደርሱ አባቶች ከጠላቶቻቸው ከአጋንንት ይሰወራሉ፤ የመንግሥተ ሰማይትን ምስጢር ያውቃሉ፡፡
ተሰጥሞ
ዓሣ በባሕር ውስጥ ተሰጥሞ እንደሚኖር፤ እዚህ ማዕርግ ላይ የሚደርሱ አባቶች ኅሊናቸው ጸጥ ይላል፤ ልዑል፣ ስፉሕ፣ ረቂቅ በሚሆን ብርሃን ይሰጥማሉ (ይዋኛሉ)፤ ሕይወታቸው ብሩህ ይሆናል፤ ሙሉ በሙሉ ደስተኞች ይሆናሉ፡፡ /2ኛ ቆሮ 6፥10፤ ፊልጵ 3፥1/ አሞራዎችና ንስሮች በአየር ባሕር ውስጥ እንደሚበሩ፣ ዓሣዎች በባሕር ውስጥ እንደሚዋኙ ተሰጥሞ ማዕርግ ላይ የደረሱ ቅዱሳንም በላይ ባለ የብርሃን ውቅያኖስ ውስጥ ይዋኛሉ፤ ይንሳፈፋሉ፡፡ ይሄም የብርሃን ውቅያኖስ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ በዚያ ብርሃን ልቦናቸው ይታጠባል፤ ፍጹም ሆነው የልብ ንጽሕና ላይ ይደርሳሉ፡፡ /ኤፌ 5፥13-14፤ ራእይ 11፥12-17፤ 12፥1-5/፡፡
ከዊነ እሳት (ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ)
ከዊነ እሳት ማለት እሳትን መሆን ማለት ነው፡፡ ይህ የመጨረሻው የብቃት ደረጃ ነው፡፡ ቅዱሳን ከከዊነ እሳት ማዕርግ ሲደርሱ እንደ እሳት ይሆናሉ ሰውነታቸው በብርሃን ይከበባል፤ ከእግር እስከ ራሳቸው ድረስ እሳት ይመስላሉ /ዮሐ 5፥5/፡፡ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ከከዊነ እሳት ማዕርግ ላይ ደርሶ ስለነበር ተሐዋስያን /ነፍሳት/ እላዩ ላይ ሲያርፉ ይቃጠሉ /ይሞቱ/ ነበር፡፡ በዚህ ማዕርግ ያሉ ቅዱሳን የራሳቸውን አኗኗር ይዘነጋሉ፡፡ ነፍሳቸውም በተመስጦ ለብዙ ቀኖች መቆየት ትችላለች፡፡ ኅሊና አባቶች ንጽሐ ልቡና ስለተሰጣቸው እግዚአብሔር (ቅድስት ሥላሴን) በተለያየ አርአያና ምሳሌ የማየት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ጌታችን፣ ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና፣ እንዳለ /ማቴ 5፥8/፡፡ ፈጣሪን ከማየት የበለጠ ምን ክብር፣ ምን ዕውቀት አለ፤ እግዚአብሔር ሊረዱት በሚችሉበት መጠን ይገልጽላቸዋል፡፡ ይኸውም በዘፈቀደ ይገለጻል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በባሕርዩ ማየት የሚቻለው የለም፡፡ /ዮሐ 1፥18/ በዘፈቀደ ግን ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ዮሐንስ እግዚአብሔርን በንጉሥ አምሳል አይተውታል፡፡ /ኢሳ 6፥1-8፤ ራእ 4፥1-11/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር