የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የ2008 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቀረበ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትጋር  በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው መርሐ ግብሩን በጸሎት ከጀመሩ በኋላ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፣
አንሰ አፋቀርኩ ጵጵስናከ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣
ትክበር ነፍስየ በቅድመኰሎሙ ሊቃነ ጳጳሳት ወካህናት ትብል ደብረ ጽጌ፡፡
የሚለውን መንፈሳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመቀጠል የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሳሙኤል ደምሴ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመልካም ምኞት ንግግር ካደረጉ በኋላ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እና በችግሮች ላይ የተወሰዱ መፍትሔዎችንም ጭምር በሪፖርታቸው አክትው አቅርበዋል፡፡
ከዚያም በግማሽ ዓመቱ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ መልካም ሥነ ምግባር ላሳዩ ለክፍለ ከተማው ቤተ ክርህነት ጽ/ቤት እና ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የሥራ ኃላፊዎች  በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በመቀጠል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ይህን መርሐግብር ያዘጋጀነው ለመካሰስ ሳይሆን በሠራነው ሥራ ስኬታማ ያደረገንን እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፡፡
ከዛሬ ዓመት በፊት በቦሌ ክፍለ ከተማ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እንደዚህ አይነት ሰላም አልነበረም፡፡ በአንፃሩ በየእስር ቤቱ የሚመላለሱ የደብር አለቆች፣ በሰላማዊ ሰልፍ የሚመጡ ምእመናን ከሀገረ ስብከት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ ብሎም እስከ ቅዱስነትዎ ልዩ ጽ/ቤት ድረስ በመምጣት እሮሮ የሚያሰሙ ብዙዎቹ ከዚህ ክፍለ ከተማ የሚመጡ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነበር፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለዚህ ስኬት በመብቃታችን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
አሁን የሁከት ድምፅ የሚሰማበት ሳይሆኝ ሁሉም በየ አጥቢያው ከመንፈሳዊው አገልግሎት ጐን ለጐን በልማት ላይ ተሰማርቶ የሚገኘበት ወቅት ነው፡፡
በተጨማሪም የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እስካሁን ተከራይቶ ከሚሠራበት ቢሮ ወጥቶ የራሱ ቢሮ ለመግዛት በንቀሳቀስ ላይ ነው የሚገኘው፤ ቢሮ ብቻ አይደለም፤ ክፍለ ከተማው ሰፊ በመሆኑ ሁሉም ቦታ ለመድረስና ሥራን ለማፋጠን ይረዳ ዘንድ ተሽከርካሪዎችንም ለመግዛት በዝግጅት ላይ ነው፡፡
ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ በቦሌ ክፍለ ከተማ ስብከተ ወንጌል በስፋት መሰጠት ከመጀመሩም በላይ ከቤተክርስቲያኗ መዋቅር ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሰባክያነ ወንጌልን መቆጣጠር ተችሏል፡፡
በሰንበት ት/ቤት በኩልም መልካም ጅምር ነው እየታየ ያለው፡፡ በመንፈሳዊው የአገልግሎት ዘርፍም ቢሆን የቦሌ ክፍለ ከተማ የታደለ ክፍለ ከተማ ነው ነው፡፡ ሊቃውንቱ በማሕሌት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርት ዘርፍ ጉባኤ ዘርግተው በማስተማር ላይ ነው ያሉት ታዲያ በዓመት ውስጥ ይህ ሁሉ ስኬት ያለ እግዚአብሔር አጋዥነት ሊሆን አይችልም፡፡
ለዚህ ያበቃን እግዚአብሔርን ምርኩዝ በማድረግ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ላገለገሉ  አባቶች እና ወንድሞች እውቅና ለመስጠት እንጂ ለመካሰስ ያልተሰበሰብን በመሆናችን ከሰይጣን ወገን ያልሆነ ሁሉ ይደሰትብናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በማለት ክቡር ከሥራ አስኪያጁ ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ  ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክረሃይማኖት የዕለቱን መርሐ ግብር አስመልክተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በሰጡበት ወቅት 
ወለእለሰ ሠናየ ተልዕኩ ምክዕቢተ ክብር ይደልዎሙ፡፡ በቅንነት ለሚያገለግሉ እጽፍ ድርብ ክብር ይግባቸዋል እንዲል ለሚሠሩ ሰዎች የሚደረገው ሽልማት የሰውን ሞራል ስለሚያነሣሣ ይቀጥል የሚል እምነት ነው ያለኝ ለደከሙ ሰዎች የድካም ዋጋቸውን በሰው ፊት መመስከር ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በዘፈቀደ ሳይሆን እንዲህ በሕግ ማገልገል ተገቢ ነው፡፡ ሕገ ወጥነት ለግለሰብም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን አይበጅም፡፡ ሁሉም በሕግ መኖር ነው ያለበት፡፡ ነገር ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሕግ ውጪ የሚሆኑ ይኖራሉ፡፡ እነሱንም ቢሆን መምከር እና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡
ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ በተለይ በዚህ በጾም ወቅት በሚገባ ሕዝቡን ማገልገልና ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ሰባክያነ ወንጌልን በሁሉም ቦታ ማሰማራት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከአገር ውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ ያላመነችበት ሰባኪ ማስተማር የለበትም፡፡
ስለ መልካም አስተዳደርም ይሁን ስለ ፐርሰንት አሰባሰብ በሕግና በቃለ ዓዋዲው መሠረት ከተሠራ መጣላትና መከሰስ ቀርቶ በአንጻሩ የመልካም ሥራ ውጤቱ እንዲህ መመሰጋገንና መመሸላለም ነው የሚሆነው፡፡
መልካም ሥራ ሠርታችሁ የማበረታቻ ሽልማት ያገኛችሁ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የሥራ መመሪያ እና አያያዘውም ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ በመስጠት የዕለቱን ፕሮግራም በጸሎት ዘግተዋል፡፡

{flike}{plusone}