ሥርዓተ ጸሎት በኢ.ኦ.ተ.ቤተ ክርስቲያን
ሥርዓተ ጸሎት
ጸሎት፡-ቃሉ ግእዝ ነው ጸለየ ለመነ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ጸሎት፡- ማለት ልመና ነው፡ጸሎት ምስጋናም ነው ‹‹ይትቀደስ ስምከ›› (ስምህ ይቀደስ) ስንል ምስጋና ነው ‹‹ሲሳየነ ዘለለእለትነ ሀበነ ዮም›› (የእለት ምግባችንን ስጠን ዛሬ) ስንል ደግሞ ልመና ነው፡፡ እንዲሁም ጸሎት፡- ሰው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገርበት ነው፡፡ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14)
በምን አይነት መንገድ መጸለይ እንዳለብን ከዚህ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
1.በፍጹም እምነት መጸለይ ይገባል፡፡በፍጹም እምነት የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሔር ይቀበለዋል እየተጠራጠርን የምንጸልየውን ጸሎት ግን እግዚአብሔር አይቀበለውም፡፡ ጥርጥር ትልቅ የሰው ባለጋራ (ጠላት) ነው ጥርጥርን ማስወገድ ያስፈልጋል‹‹ አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ›› /ማቴ. 21÷22/
2.በቅን ልቡና፣በንጹሕ ልብ መጸለይ ይገባል፡፡በቅን ልቡና፣በንጹሕ ልብ የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሔር ይቀበለዋል ልባችንን የቂም በቀልና የክፋ ምሽግ አድርገን የምንጸልየውን ጸሎት እግዚአብሔር አይቀበለውም፡፡‹‹ጸሎቱ ለመስተቀይም ከመዘርዕ ዘወድቀ ማእከለ አሥዋክ›› (የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መካከል እንደ ወደቀ ዘርዕ ነው) /መጽሐፈ መነኮሳት/
3.ሀሳባችንን ሰብስበን አንድ ልብ በመሆን መጸለይ ይገባል፡፡ቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት የጰራቅሊጦስ እለት አንድ ልብ ሆነው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ /የሐ. ሥራ 2÷1/
4.በመፍራት፣ በመንቀጥቀጥ ሆኖ መጸለይ ይገባል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14/
5.በጸሎት ጊዜ ቀጥ ብሎ መቆም እንደሚያስፈልግ ሥርዓት ተሠርቷል፡፡‹‹በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ ላንተ እታይሀለሁም›› /መዝ.5÷3/
6. ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መጸለይ ይገባል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ጊዜ ይገለጽ ዘንድ የተነገረለት ነውና ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መጸለይ ይገባል፡፡/ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14/
7.በጸሎት ጊዜ መስገድ ይገባል፡፡ይኸውም ጸሎቱን ስንጀምርና ስንጨርስ እንዲሁም በጸሎት ጊዜ ስግደትን ከሚያነሳ አንቀጽ ስንደርስ መስገድ ይገባል፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14/
8.ጸሎት ስንጀምር በትእምርተ መስቀል (በመስቀል ምልክት) እናማትባለን ስናማትብም ከላይ ወደታች ከግራ ወደ ቀኝ ነው፡፡ ይህም ምሳሌ አለው ከላይ ወደታች የምናማትብበት ምክንያት የሰላም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት የመውረዱ ምሳሌ ነው፡፡ ከግራ ወደቀኝ የምናማትብበት ምክንያት ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተስቅሎ፣ሞቶ ነፍሳትን ከሲኦል ወደገነት የመመለሱ ምሳሌ ነው፡፡ በቀኝ ገነት፣በግራ ሲኦል ይመሰላልና፡፡/ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 14/
በመስቀል አምሳል የምናማትብባቸው ጊዜያቶችም ጸሎት ሲጀመርና መስቀሉን ከሚያነሳ አንቀጽ ሲደረስ ነው፡፡ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 14/
9.ዓይኖችን ወደላይ አቅንቶ መጸለይ ይገባል፡፡አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ባስነሳው ጊዜ ዓይኖቹን ወደላይ አቅንቶ እንደጸለየ ሁሉ የሚጸልይ ሰው ዓይኖቹን ወደ ላይ ማንሳት እንዲገባ ነው /ዮሐ 11÷41/
ከዚህ ቀጥሎ የጸሎት ጊዜያትን እናያለን
ስብዐ ለእለትየ እሴብሐከ(በቀን ሰባት ጊዜ አመሰግንሀለሁ) /መዝ118÷164/ ሲል ነቢዩ ዳዊት በተናገረው መሠረት በቀን ሰባት ጊዜ መጸለይ እንደሚገባ ታዟል፡፡
ይህም እንደሚከተለው ተገልጿል፡-
ሰው ከእንቅልፍ ነቅቶ ከመኝታው ተነስቶ ገና ሥራ ሳይጀምር የሚጸልየው ጸሎት(በነግህ)፤በ3ሰዓት፤በ6ሰዓት፤በ9 ሰዓት፤በ11 ሰዓት (በሠርክ)፤በመኝታ ጊዜ፤በመንፈቀ ሌሊት (ከሌሊቱ በ6 ሰዓት)7ቱ የጸሎት ጊዜያት ከላይ የተገለጹት ሲሆኑ በተለይ የጧትና የሠርክ ጸሎት በቤተክርስቲያን መሆን እንዲገባው ታዟል፡፡
የሦስት ሰዓትና የሌሎች ጊዜያት ጸሎት ግን በቤትም ቢሆን በሌላ ቦታ ቢጸለይ አይከለከልም፡፡
ከነዚህ ጊዜያቶች የአንዱ የመጸለያ ጊዜ ቢደርስና የሚጸልየው ሰው ለመጸለይ ከማይችልበት ቦታ ቢሆን በልቡ የሕሊና ጸሎት ማድረስ እንዲገባው ታዟል፡፡
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ሀሳበ ልቡናችንን እንዲፈጽምልንና እንዲሁም ከልዩ ልዩ ፈተናና መከራ እንዲያድነን ሁልጊዜ መጸለይ ይገባል፡፡ ሰው ፈተና፣መከራ ሲገጥመው ይጨነቃል እንቅልፍ ያጣል እንቅልፉ ጭንቀት ይሆናል፡፡ ነገር ግን በጭንቀት ምንም የሚገኝ ነገር የለም ይህንንም ጌታችን በቅዱስ ወንጌል ‹‹ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው›› /ማቴ6÷27/ ሲል ተናሯል፡፡ፈተና፣መከራ ሲገጥመን ተግተን መጸለይ እንጂ መጨነቅ አይገባም ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› /ፊልጵ 4÷6/ ሲል ተናግሯል፡፡ይህ ዓለም የፈተና፣የመከራ ዓለም ነው፡፡ እንደውም በዚህ ዓለም ስንኖር ከደስታው ይልቅ የሚያመዝነው ፈተናው፣መከራው ነው፡፡ ይህንን ደግሞ የምንቋቋመው በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር ነው፡፡
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተግተን በመጸለይ ከፈተና እንደምንድን እንዲህሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት›› (ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ) /ማቴ 26÷41/በዚህ መሠረት አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ከፈተና፣ከመከራ እንዲያድነን ተግተን እንጸልይ፡፡ንስሐ ገብተን ቅዱስ ስጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንዲሁም በቅዱሳን አማላጅነት ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ልዑል እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ቸርነቱ ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
(ላዕከ ወንጌል በእደ ማርያም ይትባረክ (ቀሲስ) የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ትምህርት ስርጭት ኃላፊ)
{flike}{plusone}