የአዲስ አበባ ገደማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎችና ሰባክያነ ወንጌል በማኅበረ ቅዱሳን ኢመዋቅራዊ አደረጃጀትና የሥራ ግድፈቶች ላይ ባለ 19 ነጥብ የአቋም መግለጫ አወጣ

m0005

ብዛቱ እስከ 2000 የሚገመተው ይህ ጉባኤ የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ በመገኘት ማህበረ ቅዱሳን በመዋቅር የለሽ አሠራሩ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ  በርካታ ችግሮችን እየፈጠረ መሆኑን በማስመልከት አስፈላጊው ርምጃ ይደረግበት ዘንድ ጉባኤው በስፋት ከተወያየ በኋላ ባለ 19 ነጥብ  የአቋም  መግለጫ አውጥቷል፡፡
የስብሰባውን ቃለ ጉባኤ እና አቋም መግለጫ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
በጉባዔው መጀመሪያ የጉባዔው ሰብሳቢ እና የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ የቤተክርስቲያንን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታዩ ሁኔታዎችን በማስመልከት የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡
በንግግራቸውም ላይ ቤተክርስቲያን የሰላም ቤት መሆኗን፣ ሰላምን ለራሷ ብቻ ሳይን ለሀገር እና ለመላው ዓለም የምትለምን እና የምትማልድ መሆኗን፣ ሰላም በሌለበት ዓለም ዋና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ሰላም መሆኑን እንደምታስተምር፣ ነገር ግን አሁን በራሷ ሰላም ያጣችበት ሁኔታ መፈጠሩን ለጉባዔው አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም በተለይም የቤተክርስቲያንን ሉአላዊነት የሚጻረሩ ሲኖዶሳዊት ፓትርያርካዊት መሆኗን የሚፈታተኑ የፖሊቲካ ባሕርይ ያላቸው ንቅናቄዎች እንደሚስተዋሉ በዚህም ምክንያት ከሕገ ቤተክርስቲያን ውጪ ሕዝብን በማነሳሳት መዋቅር የለሽ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚሞክሩ የተለያዩ ሙከራዎች እንዳሉ፣ በዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን የሾመቻቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ ወኪሎች በአመጽ እና በሁከት ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶች ለቤተክርስቲያን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግሮች እየሆኑ እንደመጡ ገልጸዋል፡፡
የቤተክርስቲያንን ሥርዓት በመከተል ሰማያዊ ዋጋ ይገኛል ብላ የምታስተምረውን ቤተክርስቲያንን በመጋፋት፣ ቤተክርስቲያን የምታንቀሳቀሰው ገንዘብ ምዕመናን የሚሰጡት ምጽዋት ስለሆነ ገንዘቡን የሚያወጣው ምዕመናን ፍላጎት ትመራ፣ የሚል የመንፈስ ቅዱስ እንደራሴ የሆነውን የቅዱስ ሲኖዶስን ስልጣን የሚቀናቀን ግልጽ ያልወጣ የኑፋቄ ትምህርት የሚያስፋፋ እና በዚህም ምክንያት ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር እስከ መገዳደር የደረሱ አደረጃጀቶችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያፈጠጡ መጥተዋል፡፡
እንዲሁም በሀገረ አቀፍ ደረጃ የሚታዩ የፖለቲካ  ትኩሳቶችን እየተከተሉ የሀገር ትኩረት ወደ ሌላ አቅጣጫ መሆኑን በመጠቀም የራሳቸውም ዓለማ በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን የሚሯሯጡ እየበዙ እንደመጡም ይስታወላል፡፡
ከግዜ ወደ ግዜ በተለያዩ አካላት የሚፈጸሙ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ያልጠበቁ ክንውኖች፣ በቅንነት የተፈጸሙ ተራ ስህተቶች ተደርገው እየተወሰዱ ባለመታረማቸው፣ ይህንኑ በመጠቀም  የቅድስት ቤተክርስቲያንን ቀኖናዊ አሠራር እና መዋቅራዊ ሉአላዊነትን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየበዙ እና እየተለመዱ መምጣታቸውን በመግለጽ እነዚህ ሁኔታዎች ጎልምሰው ቅዱስ ፓተርያርኩ ለሚሰጡት መመሪያ የተቃውሞና የድፍረት የጽሑፍም ምላሽ እስከ መስጠት መደረሱን በማብራራት በቀጣይ ይህን መሰል ድርጊቶች ካልታረሙ፣ ለቤተክርስቲያን የሰላም ጠንቆች እንደሚሆኑ በማብራራት ጉባዔው በዚህ አቢይ አጀንዳ ላይ ውይይት በማድረግ ለቤተክርስቲያን አንድነት እና ሰላም፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሉአላዊነት ለመዋቅር መጠበቅ፣ ለምዕመናን ሕብረት እና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የሚበጅ፣ ቀኖና ቤተክርስቲያንን የጠበቀ የጋራ ውሳኔ ማሳለፍ  እንደሚገባ በማብራራት ውይይቱን ለጉባዔው ክፍት አድርገዋል፡፡
ጉባዔው በቀረበው አጀንዳ ላይ የግማሽ ቀን ውይይት ያደረገ ሲሆን በርካታ ችግሮች እና ማሳያዎች እየተነሱ ሐሳቦች ተሰጥተዋል፡፡ በተለይም የቅዱስ ሲኖዶስን ሉአላዊነት የሚዳፈሩ የሃይማኖት ነክ ውሳኔዎች በቤተክርስቲያን አቋም ያልተወሰደባቸው ያልተረጋገጡ እና ሕዘበ  ክርስቲያኑን ወደፍርሀት የሚከቱ ትምህርቶች መስፋፋት በቤተክርስቲያን ስም ከሕዝበ ክርስቲያኑ ገንዘብ የሚያሰባስቡ ማህበራት እና ግለሰቦች መብዛት፣ በጉባዔ ሊቃውንት ያልተረጋገጡ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ያልተወሰኑ የውግዘት ውሳኔዎች መስፋፋት በዝምታ በመታለፉ ሊቃውንትን ለቤተክርስቲያን በማፍራት ወሳኝ ሚና ያላቸውን የትምህርት ተቋማት ጭምር በደፈናው ስም እስከ ማጥፋት መደረሱ በሰፊው ተነስቷል፡፡
በተለይም የሃይማኖት ችግር ያለበት ሰው ቢገኝ እንኳን በሊቃውንት ጉባዔ ተመርምሮ እና ተረጋግጦ ለንስሐና ለቀኖና የሚሆን ዕድል ተሰጥቶት አልመለስ ያለውን መናፍቅ መሆኑን የሚወስነው እና በውግዘት የሚለየው ቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ ሳለ እራሳቸውን የቤተክርስቲያኒቱ ብቸኛ ጠበቃ አድርገው የሚቆጥሩ አካላት ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስ ስልጣን ለራሳቸው በመውሰድ የፈለጉትን ሲያጸድቁ ያልፈለጉትን ደግሞ በራሳቸው መገናኛ ዘዴ ጭምር እንዲሁም የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት በመጠቀም የሚያሰራጩት ትምህርት እና ያለስልጣናቸው የሚያስተላለፉት ውሳኔ ሊወገዝ የሚገባው በቤተክርስቲያን ሊቀውንት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ በጉባዔው ላይ ተወስቶአል፡፡
ማንኛውም ክርስቲያናዊ ማህበር ወይም ግለሰብ በምክረ ካህን በቤተክርስቲያን መዋቅር ታቅፎ መኖር ግዴታው ቢሆንም፣ በሰበካ ጉባዔ አባልነት ሳይታቀፉ የማሕበራት አባላት በመሆን  በክርስትና ስም ተሸፍነው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፣ ቤተክርስያን ላይ ሁከት በመፍጠር ሕዝበ  ክርስቲያኑን በቡድን በመክፈል ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ እና የሰላም ጠንቅ እየሆኑ ስለሆነ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ከነዚህ ቀሳጢዎች ለመጠበቅ ሰፊ ትምህርት ቢሰጥ እና ስብከተ ወንጌል መጠናከር እንዳለበት፣ በተለይም በቤተክርስቲያን ሥርዓት ማን ምን እንደሚሰራ እንዲያውቅና ለአጽራራ ቤተክርስቲያን ከለላ የሚሆን ነገር እንዳይፈጠር የማሳወቅ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ በተለይም በተለያየ ስም በቡድን የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ኔትወርክ በመፍጠር በቤተክርስቲያናችን የአስተዳደር ወማቅር ላይ ጥቃት በማድረስ አንድነቷን ለማናጋት ዝግጅት ያላቸው  እና አጥቢያ  ቤተክርስቲያንን በመገንጠል  በቦርድ ለመምራት የሚደረጉ  ሙከራዎች በሃይማኖት ሽፋን የሚፈጸሙ የአጽራራ ቤተክርስቲያን ተግባራት  እና የግል ጥቅመኞች እኩይ ሥራዎች ስለሆኑ በንቃት በከታተል የቤተክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ በጉባዔው ላይ በአጽንኦት ተገልጾአል፡፡
የስህተቶች መደጋገም ስህተቶችን ልምድ፣ ልምዶችን ደግሞ ሥርዓት፣ ስለሚያስመስል በስህተቶች ድግግሞሽ በመቀጠል፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ሳይቀር እስከ መገዳደር ድረስ የቅዱስ ሲኖዶን አንድነት ለመለያየት የሚሄዱበት አግባብ ጸረ ቤተክርስቲያን በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው የሚሉ በርካታ ሀሳቦች ቀርበው በሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ የጉባዔው ተሳታፊዎች  የሚከተለውን ነጥቦች የያዘ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
የጋራ የአቋም መግለጫ
1.ሐዋርያዊት እና ሲኖዶሳዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን  ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከቅዱስ ፓትርያርክ  ውጪ በምድር ላይ ሌላ መሪ ስለሌላት ፓትርያርካዊትና ሲኖዶሳዊት እንዳትሆን የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት እንቃወማለን፡፡
2.ቤተክርስቲያናችን በመንፈስ ቅዱስ በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ብቻ የምትኖር  መሆኗን ለካህናት ለምዕመናን እንዲሁም ለሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እናስተምራለን፡፡
3.በቤተክርስቲያን ዕድሳት፣ በአብነት ትምህርት ቤቶች እና በገዳማት ስም፣ ገንዘብ እየሰበሰቡ ኦዲት የማይደረጉ ማሕበራት የሚሰበስቡት ገንዘብ በጠቅላይ ቤተ ክሕነት በየዓመቱ ኦዲት እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡
በተለይም ማህበረ ቅዱሳን ከአባላት የሚሰበስበው መዋጮ በአብነት መምህራንና ትምህርት ቤቶች፣ በገዳማት ልማት በስብከተ ወንጌል ማስፋፋፊያ፣ በፕሮጀክትና በመሳሰሉት ስም ከምዕመናን የሚቀበለውን ማንኛውንም ገንዘብ እና የዓይነት ስጦታ በቤተክርስቲያኒቱ ሞዴል ሞዴሎች እንዲቀበል እና በቤተክርስቲያናችን የሒሳብ አጣሪዎች በየዓመቱ እንዲመረመር እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡
4.ማህበረ ቅዱሳን በስሩ ያሉትን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እና ሕንጻዎች ወደ ግል አክሲዮን እየቀየረ በማሸሽ ላይ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱትን ሐብትና ንብረቶች ክትትል ተደርጎ በቤተክርስቲያኒቱ የሐብት መዝገብ  እንዲስመዘግብ አብክረን እንጠይቃለን፡፡
5.ማሐበሩ የቅዱስ ሲኖዶስን ስልጣን በመጋፋት በሌለው ስልጣን ግለሰቦችን በማውገዝ የሚፈጸመው ተግባር ባለመታረሙ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ የትምህርት ተቋማትን በጅምላ ወደ ማውገዝ ተሸጋግሯል፡፡ ይህ አይነቱ ድርጊት ከሥርዓተ ቤክርስቲያን ውጪ በመሆኑ ከስህተቱ እንዲታረም ጥሪ እናቀርባለን፡፡
6.ማህበረ ቅዱሳን በሠራው ስህተት ወደፊት እንዳይቀጥል ብፁዕወቅዱስ አቡነ ማትያስ  ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቃጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ  ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የወሰዱትን አቋም እንደግፋለን፡፡ ለተግባራዊነቱም በቅዱስነታቸው አባታዊ አመራር ሥር የሚጠበቅብንን እንወጣለን፡፡
7.ማሕበሩ እንደ አበው ሥርዓት የቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓተርያርክ የሰጡትን ምክር እና ተግሳጽ መቀበል እና መጸጸት ሲገባው ለቅዱስ ፓተርያርኩ የከሰሳና ወቀሳ መልስ በጽሑፍ መስጠቱ ፍፁም የተሳሳተ እና ከመስመር የወጣ በመሆኑ የማህበሩ መሪዎች ለፈጸሙት የሕገ ቤተክርስቲያን ጥሰት ይቅርታ እንዲጠይቁ እንጠይቃለን፡፡
8.ማህበረ ቅዱሳን ከመጋቢት 15 እስከ 21 2008 በተከታታይ ለ7 ቀናት በአዲስ አበባ እግዚብሽን ማዕከል ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ ፓተርያርኩ ሳያውቁት በቤተክርስቲያን ስም ያዘጋጀው አውደ ርዕይ  እንዲታገድ ስንል እንጠይቃለን፡፡
9.ማህበረ ቅዱሳን በርካታ በጎምግባር ያላቸው እራሳቸውን ለምክረ ካህን ለፈቃደ ቤተክርስቲያን ያሰገዙ አባላት ያሉት በመሆኑ ጥቂት አባላት በሚፈጽሙት ተግባር መንፈሳዊ አገልግሎቱ እንዳይደናቀፍ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና የቤተክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት የአበውን ተግሳጽና መመሪያ እንዲከተሉ ለማሕበረ ቅዱሳን አባላት ጥሪ እናቀርባለን፡፡
10.በቀላል ቋንቋ የሚገለጹ፣ ነግር ግን የቅዱስ ሲኖዶስን አንድነት የሚፈታተኑ፣ መግለጫዎችን አስተያየቶችን እና ትምህርቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን፡፡
11.ቤተክርስቲያን ልትፈረስ አደጋ ላይ እንዳለች በማስመሰል ለሕዝበ ክርስቲያን በተለይም ለወጣቶች በተለያዩ ሆቴሎች እና አዳራሾች የሚሰጡ ትምህርቶች ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በክርስቶስ ደም የተመሰረተች የማትፈርስ የማትሸነፍ የቃል ኪዳን  ቤተክርስያን መሆኗን  የሚያቃልል የኑፋቄ  ትምህርት በመሆኑ እናወግዘዋለን፡፡
12.ወጣቶች ቤተክርስቲያናቸውን በደማቸው እንዲጠብቁ፣ ማህበራትን በሕይወታቸው እንዲታደጉ፣ በመቅስቀስ እና በማነሳሳት የሌለ እና ሊሆን የማይችል አስጨናቂ ሁኔታ  በመፍጠር ግጭት ለመቀስቀስ የሚጥሩ አካላት እና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ወጣቶችም የሚደርሳቸው መልዕክት እና የሚማሩት ትምህርት በቤተክርስቲያን የታመነበት በሊቃውንት ጉባዔ የተመረመረ እና ቤተክርስቲያን ያጸደቀችው መሆኑን ለማረጋገጥ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
13.የመንግሥት አካላት ከቤተክርስቲያናችን ጋር በሰላም እና በልማት መስኮች አብረው የሚያደርጉት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የቤተክርስቲያንን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
14.በወጣቶቻችን ያለውን ዕምቅ አቅም ለቤተክርስቲያናችን ጥቅም ለማዋል ሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር እና ወጣቶችን የሚያሳትፉ ተግባራትን በስፋት ለማከናወን ጥረት እናደርጋለን፡፡
15.ሀገረ ስብከታችን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ሀገረ ስብከት በመሆኑ በቅዱስነታቸው እና በክቡር ዋና ሥራ አስኪያጃችን በሀገረ ስብከታችን የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ሙስናን ለማስወገድ የተጀመሩ ሥራዎችን እንደግፋለን ተጠናክረው እንዲቀጥሉም እንጠይቃለን፡፡
16.በቤተክርስቲያናችን መዋቅር ተሰግስገው የቤተክርስተቲያን ላልሆነ የግል ጥቅም እና ቡድናዊ ፍላጎትን ለማሳካት በተለያዩ ዕለታዊ ችግሮች ተከልለው ለመኖር የሚጥሩ አካላትን አንድነታችንን አጠናክረን እናጋልጣቸዋለን ድርጊታቸውንም እናወግዘዋለን፡፡
17.በቤተክርስቲያን ሥር ተደራጅተው ነገር ግን የአባሎቻቸው ማንነት የማይታወቁ ማህበራት የአባሎቻቸውን ማንነት የመኖሪያ አካባቢ እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ለየሚኖሩበት ሀገረ ስብከት እና ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲያሳውቁ አስገዳጅ ሕግ እንዲወጣ ብፁዕወቅዱስ አባታችንንና ቅዱስ ሲኖዶስን እንጠይቃለን፡፡
18.ዘመን የወለዳቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የቤተክርስቲያናችንን ስም እና ቋንቋ፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት የሚሸረሽሩ፣ የብፁዐን አበውን ክብር የሚነኩ፣ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሕዝበ ክርስቲያኑ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ሀሰተኛ ትምህርት የሚያስፋፉ፣ አጽራረ ቤተክርስቲያን መነሳታቸውን ከሚያሰራጩት መረጃ እና ከድርጊታቸው ማወቅ ይቻላል ስለሆነም ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ከነዚህ የአጽራረ  ቤተክርስቲያን ተልእኮ ፈጻሚ ብሎጎች የስህተት መረጃ እንዲጠበቅ እና የእናት ቤተክርስቲያንን ድምጽ የካህናትን ምክር ብቻ እንዲሰማ እናሳስባለን፡፡
19.በቅዱስ ሲኖዶስ ያልተፈቀደላቸው ሰባክያንን እና ራሳቸውን መምህር ያደረጉ ሐሰተኛ መምህራንን ለመከላከል ያወጣቸው ተደጋጋሚ ውሳኔዎች እና መመሪያዎች በመላው ኢትዮጵያ እንዲተገበሩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በያለንበት ሁሉ ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚነት ተግተን የምንሠራ መሆናችንን እናረጋግጣለን፡፡
በተጨማሪም ይህ የአቋም መግለጫችን ለብፁዕወቅዱስ ፓትርያርክ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለሁሉም አህጉረ ስብከት እና ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሁሉ እንዲደርስ በመወሰን ስብሰባችንን በጸሎት ፈጽመናል፡፡
የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ

{flike}{plusone}