ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሥራ ኃላፊዎች የካህናትና ምዕመናን አመዘጋገብን አስመልክቶ ለግማሽ ቀን የቆየ ሥልጠና ተሰጣቸው

0110

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በተዘጋጀ የምዕመናን አመዘጋገብና የቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት አመዘጋገብ ጥናታዊ ዝግጅት የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ቁጥራቸው 1000 ለሚደርሱ የገዳማትና አድባራት ተወካዮች ለግማሽ ቀን የቆየ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ባደረጉት የመክፈቻ ገለፃ ይህ ሥልጠና መሠረታዊና አስፈላጊ ነው ÷የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና  ምዕመናንን የምንመዘግብበት ዘመናዊ አሠራር ተዘርግቷል÷ ይህ የዛሬው ሥልጠናም ይህንኑ የሚያሳይ ሥልጠና ስለሆነ ሥልጠናውን በንቁ ተሳትፎ ልንከታተል ይገባናል በማለት አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም መጋቤ ሐዲስ ሐዋዘ ብርሃን ጫኔ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ም/ኃላፊ በአሁኑ ጊዜ የምዕመናን ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃው ለ28 ጊዜ ሥልጠና የሰጠ ቢሆንም የተገኘ ውጤት አለመኖሩን ገልፀው ይህ ችግር የተፈጠረው የአስልጣኝ አለመኖር ነው፤ ችግሩም መፈታት ያለበት በአህጉረ ስብከት በኩል ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም  የምዕመናን ምዝገባ ስለሚደረግ በግምት የምንጠራውን አሀዝ በተጨባጭ ማወቅ ይገባናል፡፡ የቃለ ዓዋዲውን ድንጋጌ መከተል ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ገንዘብም ሆነ ንብረት ወደ ቤተክርስቲያን ሲገባና ሲወጣ እንዴት መውጣት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡የምዝገባው ዓላማ የአብነት ት/ቤት መምህራንንና ምዕመናንን ለማወቅና ፖሊሲ ለማውጣት ይረዳናል ብለዋል፡፡
በመቀጠልም ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ አያይዘው እንደገለፁት የሕዝብ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በሰባት ፐርሰንት ቀንሶአል አሁን ባለው የቁጥር መቀነስ እየጨመረ ከሄደ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በኋላ ሥጋት ይኖራል በአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ተጨባጭ መረጃ ሊኖረን ይገባል÷ የአገልጋዮች ኘሮፋይል ሊኖረን ይገባል፡፡

p0100

መረጃ መሰብሰብ የምንችለው ማብራሪያ መስጠት የሚችል የመረጃ ሰብሳቢ ሰው ያስፈልጋል፡፡  የምዕመናን ምዝገባ ጠቀሜታ መንፈሳዊ ጥቅም፣ ፣ማኀበራዊ ጥቅም ፣ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ፣አስተዳዳራዊ ጥቅም አለው፡፡
ካህናት የሚሠሩት ሥራ ከፍተኛ ድካም ያለበት በመሆኑ ተመጣጣኝ ደመወዝ የሚገኙበትን መንገድ ማፈላለግ ይገባል፣ ምዕመናንን መመዝገብ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ማለት ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን አንድነትና አስተዳደር ለማጠናከር፣ የቤተክርስቲያንን ችግር ለይቶ ለማወቅ መረጃው ጉልህ የሆነ ጠቀሜታ አለው ምዝገባው ሁሉንም መሸፈን ካልቻለ መረጃው ሊዛባብን ይችላል በሁሉም የቤተክርስቲያን መዋቅር የሚገኙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መረጃ የመሰብሰብ ሥራ መሥራት አለባቸው በማለት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊው ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በመያያዝም ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በሰጡት የማጠናከሪያ ሃሳብ ሥራው ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በእጅጉ ያስፈልጋል÷ በካህናትና ምዕመናን ምዝገባ ጊዜ ለገጠሪቱ ኢትዮጵያ ካህናትና ምዕመናን መመዝገቢያ ሁሉም ተሳታፊ በግሉም ሆነ በቤተክርስቲያን የወረቀት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ዋና ሥራ አስኪያጁ በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ በሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ለሕዝቡ መጥፋት ተጠያቂዎቹ ኃላፊች ናቸው በቃለ ዓዋዲው በተደነገገው መሠረት መሥራት ይኖርብናል፡፡ የእኛ ሥራ ሕግ ማስፈጸም ነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚያስገባው የፐርሰንት ክፍያ በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስበከት ከሚያስገቡት የፐርሰን ክፍያ ይበልጣል፡፡በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተሹመው የፐርሰንት ክፍያ ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ አስተዳዳሪዎች አሉ፡፡ የአሠራር ችግር ላለባቸው ክፍሎች ዕዳ እንዳለባቸው ይቆጠራል፡፡ በቅፅ ላይ የተመዘገበ የፐርሰንት ክፍያ መከፈል አለበት÷ ቅፅ በሚሞላበት ጊዜ በጥንቃቄ ሊሞላ ይገባል÷ በእኛ  የሒሳብ አሠራር ጉድለት ቤተክርስቲያንን ልናስወቅስ አይገባንም÷ አንድ አንድ ገዳማትና አድባራት የሒሳብ መዝገብ ያልያዙ አሉ÷ በሀገረ ስብከቱ የሥልጠና ማዕከል ሥልጠና የወሰዱ የሒሳብ ሠራተኞች በሰለጠኑት መሠረት ወደ ሥራ ሊገቡ ይገባቸዋል፡፡ የገዳማትና አድባራት የቁጥጥር ሠራተኞች በፔሮል ላይ ፈርመው ደመወዝ ከተቀበሉ በኋላ በሞዴል ስድስት ላይ አንፈርምም ማለት አይገባቸውም÷ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከሒሳብና በጀት ኃላፊው መልዕክት በመጨመር የማጠቃለያ መልእክት ያስተላለፉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ አስራት በኩራት አልሰበሰብንም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሙዳየ ምፅዋት ብቻ ነው ያለችው÷ ገንዘብ እየሰበሰቡ ገንዘብ አትሰብስቡ የሚሉ ክፍሎች አሉ÷ እነሱን ልንሰማቸው አይገባንም፡፡ ወገኖቻችን በሌላው ዓለም እየሄዱ የሚታረዱት ለገንዘብ ብለው ነው÷ ገንዘብ ኑሮን ለወገኖቻችን የሥራ ዕድል ብንፈጥርላቸው ለመታረድ ወደ ሌላ ሀገር አይሄዱም ነበር፡፡ የፐርሰንት ክፍያ አሰባሰብ በጣም ትልቅ አገልግሎት ስለሆነ ሁላችንም ተግተን ልንሠራ ይገባናል፤ የዘንድሮ የፐርሰንት ክፍያ በጣመ የተሻለ ነው በአደርባይነት የምንሠራ ክፍሎች  ወደትክክለኛ ኃላፊነት ልንመለስ ይገባናል፡፡ የሒሳብ መዛግብትና የሒሳብ ማቴርያሎች እንዲኖረን ወደተሻለ የሥራ ዕድገት መሸጋገር አለብን÷ ገምጋሚዎቻችን ትኩረታቸው በሥራ ላይ ሳይሆን በሰው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ / በዘር፣ በፓሊቲካ/ በሕግ ያልተፈቀደላቸው ሰባክያን በአውደ መሕረቱ ላይ ቆመው የቤተክርስቲያንን መሪዎች ሲሰድቡ ርምጃ ሊወስድ ያልቻለ አስተዳዳሪ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም አስተዳዳሪው የቤተ ክርስቲያንዋ የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ነው÷ ሀገረ ስብከቱ የቅዱስ ሲኖዶስን እና የቅዱስ ፓትርያርኩን መመሪያ ተቀብሎ ርምጃ እየወሰደ ነው÷ በየቀኑ በመድረክ የሚሰብኩ ሰባክያንን የማወቅ ኃላፊነት አለብን÷ በከተማው ዳር አካባቢ ያለ ሀገረ ስበከቱ ፈቃድ ሠራተኛ የቀጠሩ አሉ የቀጠሩትን ሠራተኞች ሊያሰናብቱ ይገባቸዋል፤ በፎርጅድ የተቀጠሩ ሠራተኞች እንዳሉም ደርሰንበታል፡፡
ስለዚህ ከሀገረ ስብከቱ የቅጥር ደብዳቤ ይዘው የሚመጡትን ሠራተኞች የማጣራት ሥራ መሥራት አለባችሁ በማለት ለተሰብሳቢዎቹ አስተዳደራዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

{flike}{plusone}