የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት በሥራ እንቅስቃሴያቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አድባራትና ገዳማት የማበረታቻ ሽልማት አበርከተላቸው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስና የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች በተገኙበት በልማት፣በመልካም አስተዳዳርና በፐርሰንት ክፍያ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አድባራትና ገዳማት የዋንጫ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በአደስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሥር ካሉት ሰባት ክፍላተ ከተሞች አንዱ ሲሆን በምዕራብ አዲስ አበባ፣ የኦሮምያ ክልል ልዩ ዞን የቡራዮ አስተዳደርና የሰበታ አስተዳደር የሚያዋስነው የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ነው፡፡
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሃያ ሰባት አድባራትና ገዳማት የሚገኙበት ነው፡፡ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ በሰለጠነ የሰው ኃይል የተገነባ መሆኑን በስብሰባው ወቅት ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ችለናል ÷ በሳምንት አንድ ቀን የሥራና የሠራተኛ ግምገማ እንደሚደረግ ሪፖርቱ አክሎ አብራርቷል ÷ በሪፖርቱ ላይ እንደተዘረዘረው ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ የታገዱ ሠራተኞችም ወደሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡በዝቅተኛና ያለጨረታ የተከራዩ የአብያተ ክርስቲያናት ቦታዎችም የኪራይ ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ሰላምን የሚአደፈርሱና ሁከት የሚፈጥሩ አንድ አንድ ወገኖች ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው ነው፡፡ የምርጫ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የሰበካ ጉባኤ አባላት በአዲስ ተመራጭ እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ የፐርሰንት ክፍያ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ዕውቅና ያልተሰጣቸው ሰባክያን የወንጌል አገልግሎት እንዳይሰጡ የተደረገ ሲሆን ሕጋዊ የሆኑ ሰባክያን ግን የወንጌል ትምህርት እንዲሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ወጣቶች 30 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በሰንበት ት/ቤቱ እየተማሩ እንዲአድጉ በትጋት እየተሠራ ነው፡፡
ከዚህም ጐን የቅርስ ጥበቃ የልዩ ልዩ ልማት እንቅስቃሴ፣እየተከናወነ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት በሩብ ዓመት ውስጥ ብር4,000,000 አራት ሚሊዮን ብር የፐርሰንት ክፍያ ገቢ ተደርጓል ÷ በክፍለ ከተማው ያገጣሙ ችግሮችን በተመለከተ የኮምፒውተር ጸሐፊ፣ መዝገብ ቤት፣ ተላላኪ አለመመደቡ፣ የትራንስፖርትና የቢሮ ቁሳቁስ አለመሟላት፣ በአንድ አንድ አድባራትና ገዳማት የሚገኙ የሰበካ ጉባኤ ሊቃነ መናብርት በዕንቢተኝነት የደመወዝ ፊርማ አለመፈረም፣ አንድ አንድ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የቃለ ዓዋዲውን ሕግ ጠብቀው አለመሥራት አንድ አንድ ማህበራት በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የአስተዳደር ሥርዓቱን ለማወክ የሚደረገው ሴራ ዋና ዋና ችግሮች
ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡
የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነቱ በ2008 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ ለማሳየት ዕቅድ የያዘ መሆኑም በሪፖርቱ ተብራርቶአል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የመርሐ ግብሩን ሂደት አስመልክተው የሚከተለውን ትምህርትዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ዛሬ በጣም ልንደሰት ይገባናል ይህን ያህል ትልቅ አቅም ካለን ብዙ መሥራት እንችላለን ሥራችን ትዕግሥትን ይጠይቃል የሥራችን ውጤት ጥሩ ስሜት ፈጥሮብናል፡፡ በሪፖርቱ የተገለፁትን ተግባራት መፈጸም አለብን፡፡
ሰበካ ጉባኤ የችግር መፍትሔ ነው ÷ የቀደሙት አባቶቻችን ከመሬት ጥገኝነት እንድንወጣ ራዕይ ስለነበራቸው ሰበካ ጉባኤን ፈጥረዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰበካ ጉባኤ ዓላማውን የጠበቀ ነውን ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡
ሰበካ ጉባኤ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር የተጣጣመ ÷ ሥራ መሥራት አለበት ÷ ከምርጫ ጋር በተያያዘ በቃለ ዓዋዲው መሠረት መከናወን አለበት ÷ ቤተክርስቲያናችንን ለማይገባ አካል ልንሰጥ አይገባንም፡፡ የሰበካ ጉባኤ ሦስት ዓመት መሥራት አለበት፡፡ የባቡር መንገድ በሁለት ዓመት ነው ተሠርቶ ያለቀው ካልሠራንበት ዕድሜ ዘልዛላ ሊባል ይችላል፡፡ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስ በሦስት ዓመቱ ነው የክርስትናውን ሥራ ሠርቶ ያጠናቀቀው ÷ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተከማቸና በመማማር ላይ ያለ ኃይል አላቸው ያንን ኃይል ከተጠቀምንበት ኃይል ይሆናል፡፡ ሌላ አካል ከተጠቀመበት ደግሞ የሌላ ኃይል ይሆናል፡፡ ስለነገዋ ቤተክርስቲያን ስናስብ ሰንበት ት/ቤትን ችላ ማለት አንችልም ወጣቱን ለመውሰድ ሌላ ኃይል ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ባዘጋጀችው ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ወጣቱን ማስተማር አለብን፡፡ ቸልተኝነት ችግር ያመጣል ÷ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መላዋን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን በድጐማ እያገለገለ ነው ከሀገር ውጭ ያሉትንም ጭምር እየደጐመ ነው፡፡ ቤተክርስቲያናችን ዓለምን ዙራ ለማስተማር የፐርሰንት ክፍያ መሰብሰብ አለባት፡፡ ወንጌልን በዓለም ሁሉ ላሉ አብያተ ክርስቲያናት ማስተማር አለብን ÷ የማኀበራቱ ቁጥር በብዙ ሺዎች ይገመታል፡፡
ይሁን እንጂ ማን እንዳደራጃቸውና ማን ፈቃድ እንደሰጣቸው አይታወቅም ÷ እነሱ እየሠሩት ያለው ሥራ እኛ ልንሠራው የሚገባንን ነው ማኀበራትን የማቋቋም ኃላፊነት የተሰጠው የማኀበራት ኤጂንሲ ነው ፡፡ እኛ የማኀበራት ሰለባዎች ነን ÷ ማኀበራቱ ከጥፋታቸው ለመታረም ሳይሆን የሚመጡት ለመላተም ነው፡፡ ማኀበራት በማኀበራት ላይ ድንጋይ ይወረውራሉ ÷ ራሳቸውን ሲኖዶስ አድርገው የሚያስቡ ማኀበራት አሉ ÷ በአድባራትና ገዳማት በሚደረገው ምርጫ ከሩቅ አካባቢ እየመጡ ሁከት በመፍጠራቸው የአድራሻ መታወቂያ እስከመጠየቅ ደርሰናል ÷ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ኃይሎች ተፈጥረዋል፡፡ ከሌላ አድራሻ እየመጡ እገሌ ሌባ ነው፣ እገሌ ጰንጤ ነው እያሉ እሳት ለኩሰው ይሠወራሉ ÷ ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኀበራት ዕውቅና እንዳይሰጥ የወሰነው ውሳኔ ደርሶናል ÷ በአቃቂ ቃሊቲና በኮልፌ ቀራንዮ ጠንካራ የሥራ እንቅሥቃሴ አይተናል ÷ እገሌ የእኛ ነው እያልን የምንፎክር ክፍሎች ካለን ተገቢ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለእኛ የሚሰማን የመጨቆንና የማግለል ሰሜት ሌሎችንም ይሰማቸዋል፡፡ ሰላም ከጠፋበትና ከተበጠበጠ ቦታ ላይ ለሰላም መፈጠር መጠራት አለብን፡፡ የአስተሳሰብ ዝንጉነት ሊኖረን አይገባም ÷ መልካም ሥራዎች መጠናከር አለባቸው÷ ሽልማቶች ለጋራ እምነትና ለጋራ ሥራ ቃል ኪዳን መግባትን ያሳያል፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሰንበት ት/ቤት በደንብ እንዲጠናከር ያስፈልጋል ÷ ከአዲስ አበባ ውጭ ስላለችው ቤተክርስቲያን ማሳብ መወያየት አለብን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሁለት ቄሶች ብቻ እየተቀደሰ ነው ያለው÷ አሥራ ሦስት ሆነው ቤተክርስቲያን የሚገነቡ ምዕመናን አሉ ÷ በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሰፊ የሆነውን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
{flike}{plusone}