የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ባስመዘገበው የዕንግዳ አቀባበል የሥራ ጥራት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የማበረታቻ ምስጋና ደብዳቤ ተቀበለ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ2008 ዓ.ም የተከበረውንና በዩኒስኮ የቅርስ መዝገብ የተመዘገበውን የመስቀል ደመራ በዓል አስመልክቶ የጉብኝት ተግባር ለማከናወን ወደ ሀገራችን በዕንግድነት የመጡት የአሌክሳንደርያ ፖፕና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ ታዎድሮስ ሁለተኛ፣ በተጨማሪም ቅዱስነታቸውን አጅበው የመጡት ሊቃነ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የልዑካን ቡድን ባደረጉት ሀገር አቀፍ ጉብኝት ላይ ሀገረ ስብከቱ ለጉብኝቱ መሳካት የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጉ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  ፊርማቸውን በማሳረፍ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የማበረታቻና የምስጋና ደብዳቤ ተላልፉል፡፡
የቅዱስነታቸው  ፊርማና  ያረፈበት ይህ የማበረታቻ ምስጋና ደብዳቤ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ታዎድሮስ ከአዲስ አበባ አድባራትና ገደማት ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች ያከናወኑትን የጉብኝት ሥራና በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ወቅታዊና ሁለንተናዊ የጋራ ግንኙነት ለማሳደግ ከመንግሥታችንና ከቅዱስ ሲኖዶሳችን ጋር የተደረገው የጋራ ምክክር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ሀገረ ስብከቱ ከልብ የተረዳው መሆኑን አበክሮ ይጠቁማል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ታዎድሮስን ሀገረ አቀፍ ጉብኝት የተሳካ ለማድረግ ሀገረ ስብከቱ ባበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ ለብፁዕ ወቅዱስ አባታችንና ለሀገረ ስብከቱ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ማጠናቀቂያ የገዛቸውን አራት ዘመናውያን አዳዲስ ሞዴል መኪኖች የታርጋ ቁጥራቸውና ሕጋዊነታቸው በአስቸኳይ እንዲረጋገጥ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡
ሀገረ ሰብከቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የክብር ዕንግዳ የሆኑትን የፖፕ ታዎድሮስን ጉብኝት የተሳካ ማድረጉ የመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወኪል ሆኖ የዕንግዳ አቀባበል ኃላፊነቱን በመወጣቱ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን የማበረታቻ ምስጋና ደብዳቤ ለማግኘት በቅቷል፡፡