ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በአዲግራት አድባራትና ገዳማት ሲያከናውኑ የቆዩት የአምስት ተከታታይ ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ተጠናቀቀ!!

0082

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ከሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎችና ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪች ጋር በመሆን ከጥቅምት 25 ቀን እስከ ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ለአምስት ተከታታይ  ቀናት ያህል በአዲግራት ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ  አድባራትና ገዳማት ሲያከናውኑ የቆዩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀቀው ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም ወደ መንበረ ፕትርክናቸው ተመልሰዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉዞአቸው ከጎበኙዋአቸው አድባራትና ገዳማት መካከል ወቀሮ ደ/ፀ/ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን፣ አጽብሒ /ደ/ገ/ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፣ አሲራ መቲራ ቅድስት ሥላሴ ገዳም፣ ውቅሮ ደ/ሰ/ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም፣ አብርሀ ወአፅብሐ ገዳም፣ ውቅሮ አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን፣ ዕዳጋ ሐሙስ ደ/ፀ/ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን፣ አዲግራት መድኃኔዓለም ካቴድራል፣ አዲግራት ዩኒቨርስቲ፣ አዲግራት ደ/ጎልጎታ መድኃኔዓለም ካቴድራል፣ ውልዋሎ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን፣ ሰውነ ደብረሲና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን፣ ሐውዜን ደብረ ሐዋዝ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ይገኙበታል፡፡ በቅደስነታቸው ከተጎበኙት አስራ አምስት አድባራትና ገዳማት ለአስራ አንድ አድባራትና ገዳማት ከብር ሶስት መቶ ሃያ ሺህ ያላነሰ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ለሁለት አድባራት ሙሉ የአምስት ቀዳስያን ልብሰ ተክህኖ ተበርክቷል፡፡ ውልዋሎ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን እና ሰውነ ደብረሲና ቅድስት ማርያም የቅዱስነታቸው መካነ ልደት ሲሆኑ ውልዋሎ ቅዱስ ቂርቆስ የቅዱስነታቸው የተወለዱበት ቦታና በጥምቀት ስመ ክርስትና የተቀበሉበት ነው፡፡
በዚህ ቤተክርስቲያን ቅርብ ርቀት የወላጅ አባታቸው ልዩ የመኖሪያ ቦታ የሚገኝ ሲሆን የሰውነ ደብረሲና ቅድስት ማርያም የቅዱስነታቸው ወላጅ እናት ቦታ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
በብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ከተጎበኙት በርካታ አድባራትና ገዳማት መካከል የአዲግራት መድኃኔዓለም ሕንፃ ቤተክርስቲያን የግንባታ ሥራው በመጠናቀቁ በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተባርኮ  የቅዳሴ ቤቱ በዓል ተከብሯል፡፡ የሕንፃው ታሪካዊነትና ዘመናዊት የካቴድራል ደረጃን የሚወክል በመሆኑ የአዲግራት መድኃኔዓለም ካቴድራል ተብሎ በቅዱስነታቸው ተሰይሟል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በጎበኙአቸው አድባራትና ገዳማት ሰፊ ትምህርት የሰጡ ሲሆን የትምህርታቸው የሐሳብ አቅጣጫ፣ የጥንታውያን ገዳማትና አድባራት ቅርሶች አጠባበቅ፣ ስለደን ልማትና ጥበቃ፣ ስለ እምነተ ዕቅበት፣ ጊዜ ስላመጣው የድርቅ ሁኔታ በዋነኛነት ያተኩራል፡፡
በጉብኝቱ መጠናቀቂያ ወቅት ጥቅምት 29 ቀን በጨካኙ የደርግ መንግሥት በቦንብ የተጨፈጨፉ የ2500 የሐውዜን ሕዝብ  የሰማዕነት መታሰቢያ ሐውልትን በመጎብኘት የሕሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
በ28/02/2008 ዓ.ም በማታው መርሐ ግብርም በሐውዜን ደብረ ሐዋዝ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ለተሰበሰበው በርካታ ምዕመናን በአሰቃቂ በቦንብ ሕይወታቸውን ያጡትን የሐውዜን ሰማዕታት አስመልክተው የደርግ መንግሥት የፈጠረውን አሰቃቂና ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ምዕመናን አፅናንተዋል፡፡

{flike}{plusone}