ቅዱስ ፓትርያርኩ ተወልደው ያደጉበትን አካባቢ እና የሐውዜን ከተማን ተዛውረው ጎበኙ

t0011
ቅዱስነታቸው ክርስትና የተነሱበት ደብር

የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ጉብኝታቸው ሊጠናቀቀ አምስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተወለዱበትን፣ የተማሩበትን እና በደርግ ዘመነ መንግሥት ከ2,500 በላይ ወገኖችና ከ20,000.00 በላይ እንስሳት በቦንብ ተደብድበው መሥዋዕት የሆኑበትን የሐውዜን ከተማን ተዘዋውረው ተመልክተዋል አባታዊ ቡራኬና ቃለምዕዳንም ሰጥተዋል፡፡
ጥቅምት 28 ቀን 2008 ዓ.ም ከብፁአን አባው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና የደብር አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን በወልዋሎ ቁሽት ደብረ ብርሃን ቅዱስ ቂርቆስ በሚባል ጥንታዊ ገዳም የተገኙት ቅዱስነታቸው ተወልደው ባደጉበት መንደርና ክርስትና በተነሡበት ገዳም ተሠብስበው ለጠበቋቸው በርካታ ምእመናንና አገልጋይ ካህናት ከባረኩ በኋላ አባታዊ ቃለምዕዳንና ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
ሀይማኖታችሁን፣ ታሪካችሁን፣ ባህላችሁን ጠብቃችሁ የደረሰባችሁን መከራና ችግር ተቋቁማችሁ በመቆየታችሁ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ በዚህ ቤተክርስቲያን የሚገኘውን ቅርስ በሚገባ በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በመቻላችሁም ልትደሰቱ ይገባችኋል ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ እናንተ ከአባትና አያቶቻችሁ የተረከባችሁትን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ እንዳቆያችሁት ሁሉ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁም ሃይማኖታቸውን፣ ታሪክና ባህላቸውን ጠብቀው መኖር ይችሉ ዘንድ በሚገባ ልታስተምሯቸውና ለትመክሯቸው ይገባል ብለዋል፡፡

t0010
ቅዱስነታቸው ያገለገሉበት ገዳም

ከረጅም ዘመን በኋላ ወደ ተወለዱበትና ወደ አደጉበት ሀገር መመለሳቸውን ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ ከዘመናት በኋላ ለመገናኘት በመብቃታችን እንኳን ደስ ያላችሁ ካሉ በኋላ በልጅነታቸው ላገለገሉበት ቤተክርስቲያን ለአምስት ልዑካን ለመቀደሻ ልበስ እና አንድ የእጅ የብር መስቀላቸውን ለግሰዋል፡፡ በወደዋሎ አካባቢ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለእያንዳንዳቸው አሥር ሺ ብር ለግሰዋል፡፡
የቅዱስነታቸው የሁለተኛ ቀን ጎብኝት ለመጀመሪያ ጊዜ የተማሩበትን የማርያም ሰውን ገዳም መጎብኘት ነበር፡፡ በገዳሙ ሲደርሱ የገዳሙ አበምኔት ካህናት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ትምህርት የሠጡት የልዩ ጽ/ቤት ኃላፊው ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ ችግር፣ ርሃብ፣ ጦርነት፣ ቸነፈር የማይፋታው የትግራይ ህዝብ ይህን በመሠለ በረሃማ አካባ በማልማትና መሬቱ መልሶ እንዲገደብ በማድረግ ከፍተኛ የልማት ሥራ እየሠራ መሆኑን ስንመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በአጠቃላይ ከቅዱስነታቸው ጋር የመጣን በሙሉ በታሪክ ሠሪነታቸው በልማት አርበኝነታችሁና በቅርስ ጠባቂነታችሁ ኮርተናል ብለዋል፡፡
አካባቢን ማልማት ልማትን ማፋጠን ቅርስን መጠበቅ፣ በሀይማኖት መጽናትን ከወላጆቻችሁ ታምራችሁ ለልጅ ልጆቻችሁ ለማውረስ እያደረጋችሁት ያለው እንቅስቃሴ ሁሉ የሚያስደስት እና የሚያኮራ ነው ያሉት ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በመጽሐፍ ቅዱስ ምድርን አልማት ተብሎ በልዑል እግዚአብሔር የተሰጠንን አምላካዊ ትዕዛዝ እንዲሁም በላብህ ጥረህ ግረህ ብላ የሚለውን አምላካዊ ቃል በተግባር የፈፀማችሁና በመፈፀም ላይ ያላችሁ በመሆናችሁ ተደስተናል ብለዋል፡፡ ልማትን ማጠናከር፤ መሥራት፣ መለወጠና አካባቢን በመጠበቅ ሀገራችንን ማልማት ይጠበቅብናል በማለት ስለ አካባቢ ልማት ብሎም ስለሀገር ልማትና በውጤቱም ህዝብ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠንካራ መልዕክት ያስተላለፉት ክቡር ንቡረዕድ በትግራይ አንዳንድ አካባቢ የሚታየው በዓለም አቀፍ የኤልኒኖ ተጽዕኖ የተፈጠረውን የምግብ እጥረት ከዚህ በፊት ደርግን ታግላችሁ በመጣል አሁን ደግሞ ድህነትን ለመጣል ያደረጋችሁትን ተጋድሎና ያስመዘገባችሁትን ውጤት በማጠናከርና በጽናት የድርቁን አደጋ በመቋቋም ክፏውን ቀን እንድታላልፉት ነው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አደራ በማለት ሠፊ ትምህርት ሠጥተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ለገዳሙ የብር መስቀልና ለአምስቱ ልዑካን መቀዳሻ የሚሆን አልባሳትን እንዲሁም 10,000.00 ብር ለገዳሙ ለግሰዋል፡፡
በዚሁ እለት ለሦስተኛ ጊዜ በቅዱስነታቸው የተጎበኘው የሐውዜን ከተማ ሕዝብ ሲሆን ቅዱስነታቸው ሐውዜን ከተማ ከመድረሳቸው 10 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ሚሊሻዎች በአጠቃላይ የከተማዋ ነዋሪዎች በአውቶቡስ፣ በሚኒባስ፣ በሞተር ሳይክልና በእግር በማጀብ ከፍተኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በሐዋዜን ደብረ ሃዋዝ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ለተሠበሠበው ሕዝብ ትምህርትና ቃለምዕዳን የሰጡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በድህነት ላይ የሚኖርን፣ የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ ላይታች የሚል ሕዝብን በገበያ ውስጥ የዕለት ጉርሱን ለመሸመትና ለመሸጥ ለመለወጥ የሚሯሯጥን ሕዝብ በሚግ አውሮፕላን በመታገዝ በቦንብ መፍጀት የግፍ ግፍ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ያኔ የነበረውን ጊዜ ያየ ዛሬ በመላ ሀገሪቱ በስውዓቱ መስዋዕትነት እየተመዘገበ ያለውን ልማትና ውጤቱን ሲያይ ደስተኛ ነው፡፡ ይህን በመስዋዕትነት የተገኘን ሰላም ጠብቀን ልማታችንን በማፋጠን ከመንግሥት ጎን በመሆን ሀገራችንን ማልማት እንደሚጠበቅብን የተገኘዘበው የሐውዜን ከተማ ሕዝብ አካባቢውን ለማልማትና ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
በቤተክርስቲያኑ ለሚሠራው ሕንፃ ቤተክርስቲያን የ30,000 ብር ድጋፍ ያደረጉት ቅዱስነታቸው ሕዝቡ ሀይማኖቱን፣ ባህሉን፣ ቅርሱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲጠብቅ አደራ ብለዋል፡፡ በማግስቱ ጠዋትም የሐውዜን ሰማዕታት መታሰቢያ በመጎብኘት የምሥራቅ ትግራይ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጎብኝት አጠናቅቆ ሰኞ 29/2008 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

በዚህ በዓይነቱ ልዩ የሆነው ሐዋርያዊ ጉብኚትን አስመልክቶ ከቦታው ያለማቋረጥ ሙሉ ዝግጅቱን ሲልኩልን ለሰነበቱ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ለእስክንድር ገ/ክርስቶስ በጠ/ቤ/ክ/የልማትና ዕቅድ መምሪያ ዋና ኃላፊ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን፡፡

{flike}{plusone}