ቅዱስ ፓትርያርክ የአዲግራት ዩኒቨርስቲን ጎበኙ

t009
የአዲግራት ዩኒቨርስቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል

ብፁዕ ወቅዱ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዩጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት የጉበኝታቸው አንዱ አካል የሆነውን  የአዲግራት ዩኒቨርስቲን ጥቅምት 27 ቀን 2008 ዓ.ም  ምሽት ላይ ጎበኝተዋል፡፡
የዩኒቨርስቲውን አጠቃላይ ይዞታ ፣የማሪዎችን ዶርምተርና የመመገቢያ ቦታዎችን በመኪና በመዘዋወር የተመለከቱት  ቅዱስነታቸው ዩኒቨርስቲ የሚጠቀምበትን የዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል እና ማዕከሉ የሚጠውን ሣይንሣዊ ጥቅም  ተመልክተዋል፡፡ በባለሙያዎችም ማብራሪያ  ተሠጥቷቸዋል፡፡
የአዲግራት ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዓለም በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት የቅዱስ ፓትርያርኩና የብፅአን አበው ሊቃነጳጳስት ጉብኝት ለዩኒቨርስቲው ማሕበረሰብ ማነቃቃትን የሚፈጠር በመሆኑ በታላቅ አክብሮትና ደስታ የሚመለከቱት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከኤርትራና ከሱማሊያ ለተፈናቀሉ ሰዎች የመማር እድልን በመፍጠር ሀገራቸው ሰላም በሚሆንበት ወቅት ለሀገራቸው እድገት የበኩላቸውን የሚወጡበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመው ዩንቨርስቲውም ከሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚለይባቸውንና ውጤታማ እየሆነባቸው ያለውን የትምህርት ዘርፍና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመዘርዘር ለቅዱስ ፓትርያርኩ ገልፀዋል፡፡
ቅዱስነታቸውም የአዲግራት ዩንቨርስቲን ተዛውረው በመመልከታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም የዩንቨርስቲው ዲን ለቅዱስ ፓትርያርኩና ለብፁአን አበው ሊቃ ጳጳሳት ያደረጉትን የክብር አቀባበል በአድናቆት እንደሚመለከቱትና ከፍ ያለ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
የአዲግራት ዩንቨርስቲ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደራጀና የተሟላ የትምህርት ተቋም በመሆኑ ለመማር ማስተማር ሥራው ከፍተኛ ጠቀሜታን ይሠጣል ያሉት ቅዱስነታቸው በተለይም ለሁለቱ ጎረቤት ሀገራት ስደተኞች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ የጎረቤትነት ግዴታችንን መወጣታችሁ የሚያስመሰግንና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ይህ ትውልድ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን በተደራጀና የዓለም የሥልጣኔ መገለጫ በሆኑ የትምህርት ግብዐቶች በተሟላ መልኩ እውቀት እንዲጨብጥ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህ እድል የተሰጠው ወጣቱ ትውልድ የተፈጠረለትን በጎ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀምና ለውጤት መብቃት አለብት ብለዋል፡፡
ከአዲግራት ዩንቨርስቲ የጎብኝት መርሐ ግብር በመቀጠል በአዲግራት ደብረ ፀሐይ ቅ/ሥላሴ ቤተክርስቲያን በዩንቨርስቲው ተማሪ ለሆኑ ወጣቶች ቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለበረከትና ቡራኬ ሠጥተዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት በተሟላና በዘመናዊ እንዲሁም በሠፊ ት/ቤት በመማራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ከእናንተ በፊት ትምህርት ይማሩ የኘበሩ ወገኖቻችሁ ባልተሟላና ባልተደራጀ የትምህርት ማዕከል ውስጥ በብዙ ድካም ከገቢ በኋላ በተለያዩ ችግሮች ትምህርታቸውን መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረስ ችግር ላይ ይወድቁ ነበር እናንተ ግን ዘመናችሁ የተባረከ በመሆኑ በዘመናዊ ግብዕት በተሟላ የትምህርት ማዕከላት የመማር እድል ስለገጠማችሁ ፈጣሪያችሁን በማመስገን ትምህርታችሁን በአግባቡ መከታተልና ለሀገራችን ለቤተክርስቲያናችሁ ልማት የምትሠሩ  እንድትሆኑ አደራ እላለሁ በማለት ለተማሪዎቹ መክረዋል፡፡
ዛሬ በዩኒቨርስቲያችሁም ሆነ በመንገድ ማካፈያው ግራና ቀኝ ተሠልፋችሁ የእኛን መምጣት ስትጠባበቁ የነበራችሁና የክብር አቀባበል ያደረጋችሁን ሁሉ የሀይማኖታችሁን ፅናት በተግባር ያሳያችሁን በመሆናችሁ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ አኛም የእናንተን  ሀይማኖት ጠንካራነት ባየን ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ልዑል እግዚአብሔር ፀጋ እና በረከቱ ያድለችሁ ተምራችሁ ለቤተክርስትያናችሁ እድገት የምትተጉ ያድርጋችሁ በማለት መርቀዋቸዋል፡፡
የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን  መፈራት እንደሆነ የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በፈሪሐ እግዚአብሔር የታነፃችሁና በእውቀት የበለፀጋችሁ በመሆን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ የምትሠሩ መሆን ትችሉ ዘንድ ትምህርታችሁን በአግባቡና በሥነ ሥርዓት መማር ይገባችኋል፡፡ በማለት አባታዊ መልዕክትቸውን አጠናቀዋል፡፡
ተማሪዎቹም የቅዱስነታቸውን አባታዊ መመሪያ በሆታና በእልልታ የተቀበሉ ሲሆን ለቅዱነታቸው  ክብር ርችት ተኩሰዋል፡፡
የብፁዕ ወቅሱስ ፓትርያርኩ የአዲግራት ሐዋሪያዊ አገልግሎት በዚሁ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀሪው መርሀ ግብር መሰረት የቅዱስነታታቸው የትውልድ ቦታና የሐውዜን ከተማ ጉብኝት መርሐ ግብር በቀጣዩቹ ሁለት ቀናት ይከናወናል፡፡
በውቅሮ፣ በአፅቢ ወንበርታ፣ በአሲራ መቲራ፣በአብርሀ፣ወአድብሐ፣ በእዳጋ ሐሙስ፣ በአዲግራት ከተማና በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የአቀባበል መርሐ ግብር በሠልፍ የወጣው የህዝብ ክርስቲያን ቁጥር  በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ከተደረገው ደማቅ አቀባበል ጋር የማይወዳደርና ደማቅና  የቅዱስነታቸውን ሐዋሪያዊ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ብፁዕ  ወቅዱ ፓትርያርኩና ብፁአን አበው ሊቃነጳጳሳትን እንዲሁም ቅዱስነታቸውን ተከትለው በምሥራቅ ትግራይ ዞን የተጓዙ የልዑካን ቡድንን ያስደመመና ያስደሰተ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት መሆኑን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሲገለፅ የቆየ የቅዱስነታቸው የሐዋሪያዊ ጉዞ ልዩ ትዝታ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

{flike}{plusone}