የአዲግራት ደብረ መድኃኔት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተከበረ
ቅዱስ ፓትርያርኩ በደብሩ ተገኝተው አባታዊ ምክር ሲሰጡ
በአዲግራት ከተማ በምሥራቃዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የአዲግራት ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህ ሕንፃ ከተራ ቤትነት ወደ ተቀደሰ ቤተ ክርስቲያንነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ቀኖና መሠረት ተለውጧል፡፡ስለሆነም የአከባቢው ህዝበ ክርስቲያን በገንዘቡ ፤በእውቀቱና በጉልበቱ ባሳነፀው ቤተ ክርስቲያን ሥጋ ወደሙ ክርስትና በመነሳትና አስፈላጊውን መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉ በማግኘት ሊጠቀምበት ይችላል በማለት የቤተ ክርስቲያኑን መመረቅ በይፋ አብስረዋል፡፡
የእግዚአብሔር ቤት የሚሠራው እግዚአብሔር እራሱ በመረጠው ቦታና ጊዜ እንደመሆኑ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን መሥራት የሚችሉም ባለቤቱ የመረጣቸውና የፈቀደላቸው ብቻ ናቸው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለዚህ የተመረጣችሁና የተባረካችሁ ልጆቻችን እናንተም መድኃኔ ዓለም ፈቅዶላችሁ ይህን የመሠለ ቤተ ክርስቲያን ሠርታችሁ ለምርቃን አብቅታችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
አሁን ባስመረቅነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሳንዘነጋ ወደፊት ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ገቢ መስገኛ ህንጻዎች እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ሊኖሩ እንደሚገባ ግልፅ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ታታሪውና ሥራ ወዳዱ የአዲግራት ሕዝበ ክርስቲያን እንደወትሮው ሁሉ በአንድነት ተባብሮ ሌላ ተአምር ሊሠራ እንደሚችል የፀና እምነት አለን በማለት በቀጣይነት ሊሠሩ የሚገባቸውን የልማት ሥራዎች ጠቁመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማናቸውም ልማታዊ ሥራዎቻችሁ ሁሉ ከጎናችሁ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ የምታደርግ መሆኗን እናረጋግጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀደም ብሎው ባደረጉት ንግግር በአዲግራት ሕዝበ ክርስቲያን መዋጮ የተገነባውን የደብረ መድኃኔት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ቤተ ክርስቲያኑ የመጀመሪያው የክርስትና ታሪክ ባለቤት በሆነው በክልል ትግራይ መሥራቃዊ ዞን በአዲግራት ከተማ ጥንታዊ የሆነ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ የተሠራ በመሆኑ ከቤተ ፀሎትነቱ ባሻገር ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ የሀገረ ቅርስ (የትውልድ ቋሚ መታሰቢያ) ሆኖ የሚኖር ነው ብለዋል፡፡
ይህንን የመሰለ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በገንዘብ፤ በእውቀታችሁና በጉልበታችሁ የገነባችሁ የከተማችን ነዋሪዎች ሁሉ መሥጋና ይገባችኋል ያሉት ብፁእነታቸው ይህን ታሪክ በዘመናችን በመሥራታችሁ የሃማኖታችሁ ፍሬና የመልካም ሥራችሁ ማረጋገጫ ማኅተም ከሆነው ከዚህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ጋር ባለውና በሚመጣው ትውልድ ስትታሰቡ ትኖራላችሁ ካሉ በኋላ በዚህ የኪነ ጥበብ እድገታችን ጎልቶ በታየበት የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ለበረከት በመረጣችሁና የእግዚአብሔር ፈቃድ በአደረባችሁ ልዩ ጥረት ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ለማክበር በመብቃታችን በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልን በሥራው ሁሉ የረዳን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን በጎ ሥራችሁንና ለስሙ ያላችሁን ፍቅር የማይረሳ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን ዋጋችሁን ይክፈላችሁ በበረከቱ ይባርካችሁ በማለት ምልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልል ትግራይ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የአዲግራት ከተማና የአካባቢውን ምእመናን የተገኙ ሲሆን የሕንፃ ግንባታውን ከፍፃሜ ለማድረስ 5,000,000.00 ብር ያህል ገንዘብ ወጪ መደረጉንና የአዲግራት ሕዝብ በዘመቻ ምልክ በየመንደሩ በመደራጀት ከፍተኛ የጉልበት እና የግንባታ ማቴሪያል አቅርቦት አስተዋፅኦ መበርከቱን በምረቃ በዓሉ ላይ ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የሕንፃ ኮሚቴ ሰብሳቢው ገልፀዋል፡፡በዚህ ዕለትም የቤተ ክርስቲያኑ የሰ/ት/ቤት ለሚያሠራው አዳራሻ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
(በእስክንድር ገ/ክርስቶስ)
{flike}{plusone}