ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ያለን የሃይማኖት ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገር ልማት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

t006
ብፁዕ አቡነ ተሥፋ ሥላሴ የወርቅ ፅዋ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ሲያበረክቱ

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የምሥራቅ ትግራይ ዞን ሐዋሪያዊ ጉዞን በማስመልከት የትግራይ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ፤ካህናት፣ ምዕመናንና በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሚማሩ ተማሪዎች  ከአዲግራት ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አቀባበል አድረገውላቸዋል፡፡
የአዲግራት ከተማ ሕዝበ ክርስቲያን የአቀባበል ሥነ ሥርዓትን በመቀላቀል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎችና ምዕመናን የብፁዕ ወቅዱስ  ፓትርያርኩን ፎቶግራፍ በመኪናዎቻቸው ላይ በመለጠፍና ተማሪዎቻቸውም  በሠልፍ ሥነ ሥርዓት  ቅዱስነታቸውን እንዲቀበሉ  በማድረግ  በቅዱስነታቸው  ሐዋርያዊ ጉብኝት  የተሰማቸውን ደስታ  ገልፀዋል፡፡
ብፁዕ  አቡነ ተስፋ ሥላሴና የካቶሊክ  ቤተክርስቲያን ካህናትም  በአዲግራት ደብረ መድሃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የቅዱሴ ቤት ማክበር ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት በህንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታና የምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሰማቸውን ደስታና በቤተክርስቲያናችን ያላቸውን አጋርነት አረጋግጠዋል፡፡
ማምሻውን ለብፁዕ ወቅዱስ  ፓትርያርኩና ለብፁአን አበው ሊቃነ  ጳጳሳት ክብር የምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ባዘጋጀው  የዕራት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል  ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ  ብፁዕ አቡነ ተሥፋ ሥላሴ በቅዱስነታቸው ሐዋርያት ጉዞ የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ በራሳቸው በኢትዮጵያ  ካቶሊካዊት  ቤተክርስቲያንና  በዕምንቱ ተከታይ  ምዕመናን ስም ገልጸው ከኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ቤተ ክርስቲያን ጋር በልማት ሥራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዕምነቱ ፣ በማንነቱ ፣ በባህሉ እና በታሪኩ  ኩሩ  ሆኖ መኖር እንዲችል  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ያበረከታቸው አስተዋጽኦ በቀላሉ  የሚገመት እንዳልሆነ የተናገሩት  ብፁዕነታቸው በዛሬው ዕለት በቅዱስነትዎ የአቀባል ሥነ ሥርዓት  ላይ በመታደም የቅዱስነተዎን በረከት በማግኘታችን ከፍተኛ  ደስታ ይሰማናል ካሉ በኋላ ለቅዱስነታቸውና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያለንን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽ ያዘጋጀነውን ሥጦታ እንዲቀበሉን በማክበር እንጠይቃለን በማለት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል  የወርቅ  ፅዋ   ለቅዱስ  ፓትርያርኩ አበርክተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ  ፓትርያርኩም ሥጦታውን ከተቀበሉ በኋላ ባሰሙት አባታዊ ንግግር ለተደረገላቸው አቀባበልና  ሥጦታ በማመስገን ከካቶሊክ  ቤተ ክርስቲያን ጋር  ያለንን  የሃይማኖት ልዩነት ጠብቀን በዜግነታችን እና በክርስቶስ ልጅነታችን በዋና ዋና የልማት ሥራዎች ዙሪያ በጋራ በመሥራት ለክርስቶስም ለሰው ልጅም ደስታን የሚሰጥ አገልግሎት ማበርከት  ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ብፁዕ  አቡነ ተስፋ ሥላሴ  ከአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ጀምሮ  በሕንፃ  ቤተክርስቲያኑ  ቡራኬ ላይም ሆነ በዚህ የዕራት መርሐ ግብር ላይ ከእኛ ጋር በመሣተፍ የቤተክርስቲያናችን አጋርነትዎን በማሣየትዎ በተለይም ከአዲግራት ወጣ ብሎ  በተደረገው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ እርስዎ እና ተከታይ ካህናቶችዎ፣ ምዕመናንና ተማሪዎቻችሁ ላደረጉልን አቀባበል እና  ለተሠጠን ስጦታ ምስጋናችን ላቅ  ያለ መሆኑን እንገልጻለን ብለዋል፡፡
በአጠቀላይ  በምሥራቅ  ትግራይ ዞን ቆይታቸው እጅጉን ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በሕዝበ ክርስቲያኑ የሚታየውን መነቃቃት በመጠቀም ለልማት ማትጋትና የበለጠ ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው በተለይም ድህነት፣ ድንቁርናና ረሃብን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ  ረገድ  ህዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቅበትን ሁሉ በጽናት መወጣት ይችል ዘንድ ጠንክሮ ማስተማር ይገባል በማለት በአንዳንድ  የትግራይ ወረዳዎች የተከሠተውን ወቅታዊ የድርቅ አደጋ ለመከላከልና ለመቋቋም ከፀሎተ ምህላ ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ በመፈጸም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል በማለት መልእክታቸውን አጠናቀዋል፡፡

                                                                                     (በእስክንድር ገ/ክርስቶስ)

{flike}{plusone}