የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ጉዞ እንደቀጠለ ነው
ቅዱስ ፓትርያርኩ የአብርሃ ወአጽብሐ ገዳምን ጎበኙ
ቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ ተገኝተው አባታዊ ምክር ሲሰጡ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጥቅምት 26 ቀን 2008 ዓ.ም በውቅሮ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የደብረ ነገስት አብርሃ ወአጽብሐ ገዳምን ጎብኝተዋል፡፡ገዳሙን ለመጎብኘት ከብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ከጠቅላይ ቤተ-ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች ፤ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስከያጅና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ጋር በደብረ ነገስት አብርሃ ወአጽብሐ ገዳም የተገኙት ቅዱስነታቸው በገዳሙ የሚገኘውን የጥንታዊ ቅርሶች ማስቀመጫ ሙዝዬምን ተዛውረው ጎብኝተዋል፡፡በገዳሙ አውደ ምህረትም የገዳሙ አገልጋይ ካህናት፤የአካባቢው ሕዝበ-ክርስቲያን፤የዘመናዊ ት/ቤት ተማሪዎች ለቅዱስነታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን ሦስት የገዳሙ ሊቃውንትም ቅኔ አበርክተዋል እንዲሁም በተመሳሳይ የገዳሙ ሊቃውንት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪም የገዳሙን አመሠራረትና ታሪክ በማስመልከት ገለፃ አድርገዋል፡፡
ገዳሙ የሚገኝበትን አካባቢ የሚያስተዳድሩት አቶ ገ/ሚካኤል(አባ ሓዊ )የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድርገዋል በንግግራቸውም የቅዱስ ፓትርያርኩ ጉብኝት ለአካባቢው ብሎም ለወረዳቸውና ለክልል ትግራይ ትልቅ በረከት መሆኑን ገልፀው በተለይም በአሁኑ ወቅት በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች በኤልኒኖ ዓለም አቀፋዊ የአየር ተጽዕኖ ምክንያት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን በመጎብኘታቸውና በመባረካቸው ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህ በበረሃማነቱ የሚታወቀው ቦታ በህዝቡ ብርቱ ጥረት ልምላሜን እንዲላበስ በመደረጉ ዓለም አቀፍ ትኩረት ማግኘት ችሏል ያሉት አባ ሓዊ ቀደምት አባቶቻችን አብርሃ ወአጽብሐ በዘመናቸው ሀገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተዋወቁበትን ታሪክ በዘመናችን ለማስተዋወቅና በዓለም መድረክ በአዲስ መልክ የመገናኛ ብዙሃን ርዕስ ማድረግ በመቻላችን ከፍተኛ ደስታ ይማናል ብለዋል፡፡
የደብረ ነገስት አብርሃ ወአጽብሐ ገዳም
በማያያዝም በድርቅ የከረመው ዘመናችን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጉብኝት ተከትሎ ከፍተኛ ዝናብ በማግኘታችን ቦታው መልሶ የማገገም ዕድል ገጥሞታልና እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራና የበረከት መሆኑን በማረጋገጣችን ከፍ ያለ ደስታ ይሰማናል በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለተሰበሰበው ሕዝበ ክርስቲያን አባታዊ መመሪያና ትምህርት ሰጥተዋል ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው እንደገለፁት የአብርሃ ወአጽብሐ ገዳም ጥንታዊና ታሪካዊ መሆኑን ገልፀው የሁለቱ ወንድማማች ነገስታት ታሪክ በመላው ኢትዮጵያ የሚታወቅና የሚደነቅ ሲሆን በዘመናቸው ሁለቱ ነገሥታት በመላው ኢትዮጵያ ታላላቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና ሕንፃዎችን በማነጽ የሚከበርና የሚደነቅ ሥራ ሠርተው አልፈዋል ብለዋል፡፡
እነዚህ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን ያነፁ ነገስታት የሠሯቸው ሥራዎች በመላው ዓለም የሚደነቁ ሲሆን ታሪካቸውም እስከ ምድር ፍፃሜ ድረስ ሲዘከር ይኖራል ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህ ደጋግ ነገሥታት የሠሯቸውን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና ትተዋቸው የሄዱትን ቅርስ ተንከባክባችሁ እና ጠብቃችሁ የምትኖሩ እናተ ወገኖቻችን የታሪክ ባለቤትና ጠባቂ በመሆናችሁ ልትደሰቱ ይገባችኋል ብለዋል፡፡
ዛሬ በዚሁ ገዳም በተገኘንበት ጊዜ የተደረገልን አቀባበል አስደሳችና የሚያስመሰግን ነው ያሉት ቅዱስነታችው አካባቢያችሁን ለመለወጥና አረንጓዴ ለማልበስ የምታደርጉት ጥረት የሚደነቅ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀትል ይገባዋል ካሉ በኋላ ዛፎች የምድር ደም ስሮች ናቸው አንድ ሰው የደም ስሩ ከተቆረጠ ዋጋ እንደሌለው ሁሉ ዛፎችም ከተቆረጡ መሬት ስሯ ስለሚቆረጥ ዋጋ የላትም ስለሆነም የምድርን ልምላሜ ለመመለስ የከፈላችሁት መስዋዕትነት ለልጆቻችሁና ለልጅ-ልጆቻችሁ ኑሮ መሻሻል የጀመራችሁትን የልማት ሥራ አጠንክራችሁ ቀጥሉ ብለዋል፡፡
ይህንን በማጠናከርም በዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የተከሰተውን ድርቅ መከላከል እንደሚቻል የጠቆሙት ቅዱስነታቸው በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረውን የድርቅ ችግር ከመንግስት ጋር በመሆን ለመከላከል ጥረቱ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመው ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን የድርቅ ችግር እንዲወገድ ጠንክራ ትፀልያለች ብለዋል፡፡ለገዳሙ ካህናትም 30,000 ብር ድጎማ ያደረጉ ሲሆን የብር መስቀላቸውም በገዳሙ በቅርስነት ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ለገዳሙ አስተዳዳሪ አስረክበዋል፡፡
የጨለቆት ሥላሴ ካህናት ለቅዱስነታቸው አቀባበል ሲያደርጉ የሚሳይ ፎቶ በከፊል(ፎቶ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ)
(በእስክንድር ገ/ክርስቶስ)
{flike}{plusone}