ቅዱስ ፓትርያርኩ የውቅሮ የአጽቢ ወንበርታንና የደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ገዳምን ጎበኙ
የደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ገዳም
በውቅሮ ከተማ ደብረ ፀሐይ ቅ/ማርያም ቤተክርስቲያን ለቅዱስ ፓትርያርኩ አቀባበል ለማድረግ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባስተላለፉት አባታዊ መልዕከት በውቅሮ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኙበት በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው ይህንኑ እንግዳ ተቀባይነታቸውንና ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ቀናኢነት አጠናክረው እንዲቀጥሉበት መክረዋል፡፡
አምላኪ እግዚአብሔር የሆነ ሕዝብ ንዑድ ክቡር ነው፣ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሚያምን ህዝብ ንዑድ ክብር ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የውቅሮ ከተማ ሕዝብ በእምነቱ በመጽናት የእግዚአብሔርን ረድኤትና በረከት በማግኘቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
ዛሬ በዚህ ከተማ የተመለከትነው የሃይማኖት ጽናትና የአባቶች አክብሮት እናንተ ከአባቶቻችሁ የወረሳችሁት በመሆኑ ልጆቻችሁም ይህንኑ የእናንተን ጽናት በመውረስ ሃይማኖታቸውን ጠባቂ እና አክባሪ በመሆን መጪው ትውልድ ሃይማኖትን አክባሪ በመሆን ይታነጽ ዘንድ ለልጆቻችሁ ስለ ሃይማኖታችሁ ምንነትና ጽናት በርትታችሁ ማስተማር ይገባችኋል ካሉ በኋላ ካህናት ወጣቱ ትውልድ በሕገ እግዚአብሔር በፍቅርና በአንድነት መኖር ይችል ዘንድ ዘወትር ማስተማር ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡
በዚሁ እለት በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ክልሻ እምኒ በተባለ የገጠር ቀበሌ በመላው ዓለም በኤልኒኖ ተጽዕኖ ከተከሰተው የአየር መዛባት ጋር ተያይዞ የምግብ እጥረት የገጠማቸውን አካባቢ ተዛውረው የተመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሕዝቡ አካባቢውን ሳይለቅ ከመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በጊዜያዊነት የገጠመውን ችግር መቋቋምና በትዕግስት ማለፍ እንደሚገባው ጠቁመው ቤተክርስቲያንም ይህ ወቅታዊ ችግር ይፈታ ዘንድ በፀሎተ ምሕላ ልዑል እግዚአብሔርን ከመለመን በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ለመፈፀም መዘጋጀቷን ገልፀዋል፡፡
የቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ አካባቢው መምጣት የተመለከቱ አጸቢ ወንበርታ ከተማ በርካታ ነዋሪዎችም ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደማቅ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በአጽቢ ወንበርታ ደብረ ገነት ቅ/ሥላሴ ገዳም ለተሰበሰቡ ምዕመናን ትምህርትና ቡራኬ ሠጥተዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ በትምህርታቸውም በገዳሙ የሚገኙ ጥንታዊያን ቅርሶች ለመጠበቅና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲሁም ጥታዊውን ቤተክርስቲያን በዘመናዊ የሕንፃ ጥበብ ለመተካት የአጽቢ ወንበርታ ሕዝብ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው የጀመራችሁትን ሕንፃ ቤተክርስቲያን በማጠናቀቅ ቅርሶቻችሁን በአግባቡና በተገቢው መንገድ በመጠበቅ አደራችሁን በብቃት መወጣት ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ በገዳሙ ለሚሠራው አዲስ ሕንፃ ቤተክርስያን ግንበታም የአንድ መቶ ሺ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የደብረ ዓላማ አሲራ መቲራ ቅ/ማርያም ገዳምን የጎበኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ አባምኔት በአባ ገ/መድህን ገ/ጊዮርጊስ የቀረበውንና የገዳሙን አመሠራረትና ታሪክ የሚገልጽ ሪፖርት አዳምጠዋል፡፡
የገዳሙ አበምኔት አባ ገ/መድህን ገ/ጊዮርጊስም በሪፖርታቸው የገዳሙን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነት እንዲሁም በልማት ራሱን ለመቻል ያደረገውን ጥረትና ያሳካቸውን ስኬቶች በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በገዳሙ በቀጥታ የሚረዱ ከ8000 በላይ ወላጅ አልባ ህፃናትም እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ ገዳሙ ለሚያደርገው ጠንካራ የልማት እንቅስቃሴም ከወረዳ እስከ ፌድራል መስሪያ ቤቶች ተገቢው እውቅናና ሽልማት የተሠጠው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የገዳሙ የራስ አገዝ ልማት ያመጣው ውጤቱ ያላስደሰታቸው አንዳንድ ማኅበራት ነን ባዮች የገዳሙን መልካም ሥራ ለማጠልሸት ሌት ተቀን ሲደክሙ ይውላሉ ያሉት አበምኔቱ እኛ ግን ገዳማዊ ሥራችንን በማከናወን ለውጤት መብቃት መቻላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸውም ሪፖርቱን ካዳመጡ በኋላ ባሠሙት አባታዊ ንግግር ይህንን ታላቅ ገዳም ከአባቶቻችሁ ተረክባችሁና ጠብቃችሁ ለትውልድ ለማስተላለፍ ቅድመ ታሪኩ ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲሁም በልማት ሥራው የተዋጣለት እንዲሆን ለማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት የሚደነቅና የሚመሠገን ነው ብለዋል፡፡
ይህ ገዳም ችግረኛ ሕጻናትን ለማሳደግና ለመረዳት ያደረገው ጥረትና እያደረገ ያለው ሥራ የሚመሠገንና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህን አይነት የተቀደሰ ተግባር ማከናወን ደግሞ ከገዳማውያን መነኮሳትና መነኮሳያት የሚጠበቅ ነው በዚህ ልትቀጥሉበት ይገባል ብለዋል፡፡
የዚህ ታላቅ ገዳም አበምኔት አባ ገ/መድህንም ይህን ገዳም በማስፋፋት፣ በማጠናከርና የውጤታማው የልማት ሥራዎች ባለቤት እንዲሆን በማስቻል ረገድ ያከናወኗቸው ሥራዎች ሁሉ የሚመሰገኑና ተገቢው እውቅና ሊሠጣቸው የሚገባ ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሥራ የሚሠራ ሰው መፈተኑ ስለማይቀር በሥራዎቻችሁ መካከል የሚገጥሟችሁን አሉባልታዎች በመራቅ እና ለአሉባልተኞች በመተው ጠንክራችሁ መሥራትና አሉባልታ ከሥራ እንደማይበልጥ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባችኋል ሲሉ መክረዋል፡፡
{flike}{plusone}