የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ተከበረ!!!

00310

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሚገኘው የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ታሪካዊና ዘመናዊ ሕንጻ ቤተክርስቲያን የግንባታ ሥራው በመጠናቀቁ ቅዳሜ ጥቅምት 13 ቀን 2008 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳት ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በቅዱስነታቸው መሪነት ታቦተ ሕጉ ከነባሩ መቃኞ ተነስቶ በአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን መቅደስ በክብር ገብቷል፡፡
በዚሁ ዕለት በሊቃውንቱ ተቀደሲ ወንስኢ ኃይለ ኦ ቤተ እግዚአብሔር እስመናሁ ፓትርያርክ ማትያስ በጽሐ ደብረ ምጥማቅ የሚለውን ግሥ በወረብ አሰምተዋል፡፡
በመቀጠልም በሰንበት ት/ቤቱ መዘምራን “ ሐነጸ ጽርሐ መቅደሱ በአርያም ” የሚል ዝማሬ ቀርቧል፡፡
ከዚያም የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ፈቃደ ሥላሴ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት እንዳስተላለፉ የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዳርሰማ ታደሰ ባሰሙት ሪፓርት የደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን በ1991 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡ በ1993 ዓ.ም የአዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ግንባታ ተጀመረ ÷ የግንባታ መነሻ ካፒታል ብር66,351 ሲሆን ሕንጻው ሲጠናቀቅ ብር14,992,467.99  ፈጅቶል፡፡ ሕንጻው ያረፈበት 1500 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ነው ፡፡ የግንባታ ሥራው አስራ አራት ዓመት ፈጅቷል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ “አንተ እለት ነህ÷በአንተ አለትነት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ” /ማቴ 16÷16/ ይህንን ታላቅ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ሠርታችሁ ለውጤት ያበቃችሁ ምዕመናንና ምዕመናት እንኳን ደስ አላችሁ? ይህ ቤተክርስቲያን ታሪኩ ብዙነው፤ የሥራችሁን ዋጋ እግዚአብሔር ይከፍሏችኋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ መሠረቱ የፀና ነው ፤ ሥራውም የማረ ነው ፤በጣም ሰፊ ቤተክርስቲያን ነው ፤ለልጆቻችሁ እና ለልጅ ልጆቻችሁ የሚተላለፍ ቅርስ ነው፤ የምትጠመቁበት፣ ልጆቻችሁን ክርስትና የምታስነሱበት፣ የምትድሩበት ስለሆነ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ!!
ዛሬ ይህ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ጸሎትና በቅዱስ ቅባት ተባርኮ ተቀድሷል፡፡ ከተራ ሕንጻ ወደ ቅዱሰነት ተለውጧል፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ሆኖአል ÷በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁና በዕውቀታችሁ የሠራችሁት ቤተክርስቲያን እጅግ ድንቅ ነው ÷ ሠሪውም ልዩ አርቴክት ነው፡፡ ብዙ ብትደክሙም ሥራው ግን ድካማችሁን የሚአስረሳ ነው ÷ ከዛሬ ጀምሮ ቤተክርስቲያኑን ካቴድራል ብለን ሰይመነዋል በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት አስተላልፈው መርሐ ግብሩን በጸሎትና በቃለ ምዕዳን አጠናቅቀዋል፡፡

{flike}{plusone}