የጥቅምት 2008 ዓ.ም.የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአጋእዝት ጌታ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከተለያዩ የዓለም አህጉርና ከሀገራችን አህጉረ ስብከት አሰባስቦና አንድ ላይ አገናኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ስለተሰጠን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለመወያየት ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን ፡፡
‹‹ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት፤ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናትን አስመልክቶ ምን አለ?›› (ራዕ. 2፡7) ፡፡በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተችው ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ሐምሣ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አመራርና ጥበቃ ሥር እንዳለች ይታወቃል፡፡
ቅዱስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዓለም በማያየውና በማያውቀው ረቂቅ ጥበቡ በሃይማኖት አማካይነት በልበ ምእመናን አድሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲመራ ይኖራል ፡፡
ከዚህም ሌላ በሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ቅዱስ ቃሉንና ቅዱሳት ምሥጢራቱን ለምእመናን ያድላል ፡፡
በመሆኑም ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የሚለውንና የሚናገረውን በትክክል አዳምጠውና ተረድተው ምግብናቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ለሰባቱ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ዘእስያ የተነገረው ቃለ ተግሣጽ ወምዕዳን በግልጽ ያስተምረናል ፡፡
ለተጠቀሱት የቤተ ክርስቲያን ሥዩማን የተላለፈው መልእክት በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ቃል እንደሆነ ለማመልከት ‹‹ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት›› በሚልና ‹‹ዘቦ ዕዝን ሰሚዐ ለይስማዕ›› በሚል ኃይለ ቃል ሲዘጋ እናያለን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ለሰብዑ አብያተ ክርስቲያናት ዘእስያና ለአለቆቻቸው የተነገረው ሁሉ ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያንና አለቆቿን ጭምር በቀጥታ የሚመለከት እንደሆነ ጥርጥር የለውም ፡፡
ከአለቆቹ መካከል የተመሰገኑም፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙም፣ እንደዚሁም ጠንከር ያለ ተግሣጽ የደረሰባቸው እንዳሉ እንገነዘባለን ፡፡
ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሥራ ኃላፊነት የምንገኝ ሥዩማንም በዚያን ጊዜ በነበረችው ፈታኝ ዓለም ውስጥ የምንገኝ እንደመሆናችን መጠን፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ኩነቶች ሁሉ አሁንም አይኖሩም ማለት አይቻልም ፡፡
በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ቦታ፣ ክፍተት አይፈጠርም ብሎ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት መውሰድ የሚችል ይገኛል ተብሎም አይጠበቅም ፡፡
ነገር ግን የከፋና የባሰ ክፍተት እንዳይፈጠር የተጠናከረ ሥራ በመሥራት መከላከል የሚችሉ በየጊዜው ሁሉ የተነሡ ታላላቅ አበው እንዳሉ እናስተውላለን ፡፡
በዚህ ዘመን የምንገኝ ኖሎትም ምንም ቢሆን ከዚህ እውነታ ውጭ መሆን አንችልም፤ መሠረታዊ ችግር ሊሆን የሚችለው ክፍተት ለምን ተፈጠረ የሚለው ሳይሆን ክፍተት መኖሩ እየታወቀ ዝም ብሎ መኖሩ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ይህ ዓቢይ ጉባኤ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ በቤተ ክርስቲያናችን መሠራት የነበረባቸው፤ ሆኖም ግን እስካሁን በአጥጋቢ ሁኔታ ያልተሠራባቸው የሥራ መስኮች እንዳሉ ባይካድም ጥሩ ውጤት ያስመዘገብንባቸው ነገሮች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም፤
በተለይም ሕዝበ ክርስቲያኑ ባለው ዓቅም ሁሉ ቤተ ክርስቲያኑን ለመደገፍና ለማልማት የሚያደርገው ቀና ትብብር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ይታያል፣
አንዳንድ አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሚያስደንቅ ሁኔታ የራስ አገዝ ልማት እያካሄዱ ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ የሚሆን ትልቅ ዓቅም እየፈጠሩ ይገኛሉ ፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማስፋፋት በዓለም ዙሪያ የተደረገው እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም ክፍለ ዓለማት ማለትም ከምዕራብ አሜሪካ እስከ ጃፓን፣ ከአየርላንድ እስከ አውስትራሊያ ቤተ ክርስቲያናችን ክንፎቿዋን የዘረጋችበት ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ተገኝቶአል ማለት እንችላለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንም ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ወደ መሆን አድጋለች ማለት ይቻላል ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ሥራ ሰፊና ዘርፈ ብዙ በመሆኑ አሁንም ቢሆን ትኩረት ተሰጥቶአቸው በቅድሚያ ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ ማስታወሱ ተገቢ ነው፤ በመሆኑም፤
- ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ጥበብ ተከትላ ሀብትዋና ንብረትዋን መጠበቅ የሚያስችሏትን አሠራሮች መቀየስ፤
- በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ሊዘጋጁ የሚገቡ ልዩ ልዩ ደንቦች፣ ፖሊሲዎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሥራዎች ሁሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤
- ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረውንና እስካሁን በይደር የቆየውን የመሪ ዕቅድና የሚድያ ጥናት በዚህ ዓመት በጀት ተይዞለት በአፋጣኝ ሥራ ላይ ማዋል፤
- የምእመናንን ፍልሰት ለማስቆም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር፣
- በውጪ ሀገራት የሚገኙ አድባራት ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ትስስር ማጠናከር፤
- በሁሉም አቅጣጫ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያናችንን በኢኮኖሚ የበለፀገች ማድረግ፤
- የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሆኑ ሕጻናትና ወጣቶች በሰንበት ት/ቤት በስፋት እየተደራጁ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ተገንብተው እንዲያድጉ ማድረግ፤
- ለአብነት ት/ቤቶችና ለገዳማት የሚደረገውን ድጋፍ በማሳደግ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግና በመሳሰሉት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራባቸው ሥራዎች ሊሆኑ ይገባል ፡፡
- በሌላ በኩል በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ድርቅ እንደተከሠተና የምግብ እጥረትም እንዳጋጠመ፣ በሠላሳ ዐራተኛው የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረቡ የየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርቶች ለመገንዘብ ተችሎአል ፡፡
- በመሆኑም ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በተለመደው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ባህላችን መሠረት፣ ሕዝቡ ካለው እየከፈለ የተጎዱ ወገኖችን እንዲረዳ ከማስተማርና ከማስተባበር በተጨማሪ፣ የሕዝብ እናት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ዓቅሟ የሚችለውን ሁሉ ታደርግ ዘንድ፣ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ መነጋገር አለበት፡፡
በመጨረሻም
ይህ ሐዋርያዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓቢይ ጉባኤ ሐዋርያዊት፣ ህልውተ ኵሉ፣ አንዲትና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም አቅጣጫ የተሟላ፤ የተስተካከለና ከክርስቶሳዊ አስተምህሮዋ ጋር የሚጣጣም አሠራር እንዲኖራት ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንሥቶ በመወያየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ዘንድ በማሳሰብ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 164 በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የ2008 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ባርከን ከፍተናል ፡፡
እግዚአብሔር ጉባኤችንን ይባርክ፤ ይቀድስ
አሜን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
{flike}{plusone}