የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከቀረጥ ክፍያ ነጻ የገዛቸውን 4 ዘመናውያን አዳዲስ ሞዴል መኪኖች የርክክብ ሥርዓት አከናወነ!!

አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀደም ሲል ከቀረጥ ክፍያ ነጻ የገዛቸውን 4 መኪኖችን አስመልክቶ የሕጋዊነታቸውን የማረጋገጫ ሰነድ አሟልቶ ካጠናቀቀ በኋላ መስከረም 13 ቀን 2008 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ቁጥራቸው 1,000 በሚደርስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመመሪያ ኃላፊዎች ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አድባራት እና ገዳማት ተወካዮች በተገኙበት 4ቱንም መኪኖች በይፋ በማሳየት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎት እና ቡራኬ የተዘጋጀው ሪቫን ተቆርጧል፡፡
በመቀጠልም የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ለታዳሚው ባቀረቡት ሪፖርት ቅዱስ አባታችን ባላቸው ቋሚ ሦስት ዕቅዶች መሠረት ማለትም ሙስና እንዲወገድ ፣ መልካም አስተዳደር እንዲስፋፋ ፣ ፍትህ እንዲሰፍን ሀገረ ስብከታችን ሰላም እና መረጋጋትን በማስፈን፣ የታገዱ ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ ሥራ ላላገኙት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሥራ ዕድል በመፍጠር ፣ ሙስና እንዲወገድ በማድረግ ፣ የገንዘብ ቆጠራ በባንክ እንዲሆን ፣ የንብረት አያያዝ እና አቆጣጠር ሥልጠና በመስጠት ፣ የደመወዝ አከፋፈል በባንክ ሆኖ ሠራተኛው የቁጠባ ደብተር እንዲኖረው በማድረግ ፣ የተሻለ የፐርሰንት ክፍያ በመሰብሰብ ሀገረ ስብከቱ የላቀ የሥራ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡
አስተዳዳሪዎችም የሚነሳባቸውን እሳት ተቋቁመው ከዚህ ደረጃ በመድረሳቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ የዘወትር አለቆቼ ስለሆናችሁ እጅግ በጣም እኮራባችኋለሁ! በሥራችን ላይ ተስፋ እንድንቆርጥ ፣ ለውጥ አይቻልም እንድንል ፣ ጫና የሚፈጥሩ ክፍሎች የተለየ ስያሜ በመስጠት እሳቱ እየተቀጣጠለ ስለሆነ መቆሚያ የለውም በማለት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አሳውቀው ግፊት እና ጫና የፈጠሩብንን ክፍሎች መቋቋም የመጀመሪያ እና ተቀዳሚ ሥራችን ነበር፡፡ በየደብሩ ሁከት እና ብጥብጥ ሲፈጥሩ፣ በውጭ እና በከፊል የውስጥም ግፊቶች የለውጥ ፍጥነታችን እንዲዘገይ ቢያደርጉም ቀላል የማይባል ሥራ አከናውነናል፡፡
ቀደም ሲል ለ9 ወራት የተሰበሰበው የፐርሰንት ገንዘብ ዝቅተኛ ነበር አሁን ግን ከ101 ሚሊዮን በላይ ፐርሰንት ሰብስበናል፣ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በማስደረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገናል፣ የቤተ ክርስቲያን የሀብት ምንጭ የሆነው አስራት በኩራት በሌሎቹ የተወሰደ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የገቢ ምንጫችን ሙዳዬ ምጽዋት ላይ ብቻ ነው የተንጠለጠለው በአድባራት እና ገዳማት ውስጥ በዓመት 507 ሚሊዮን ብር ገቢ የተገኘ በመሆኑ የላቀ ታሪክ አስመዝግበናል፡፡
98 አድባራት እና ገዳማት የ2007 ዓ.ም ፐርሰንት ክፍያ አጠናቀዋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ስሪታቸው የ2015 ሞዴል የሆኑ 4 ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነጻ በሆነ ከውጭ ሀገር ገዝተን ማስገባት ችለናል፡፡ ቅዱስነታቸው ለሐዋርያዊ ጉዞ የሚጠቀሙበት ተሽከርካሪ የቆየ እና የአረጀ በመሆኑ ከነዚህ 4  ተሽከርካሪዎች ሀገረ ስብከቱ አንድ አዲስ ተሽከርካሪ አበርክቷል፡፡
ተሽከርካሪው ካሜራ ፣ የቪዲዮ ስክሪንና ማቀዝቀዣ እንዲገጠሙለት ተደርጓል፣ 3ቱ ተሽከርካሪዎች ለሀገረ ስብከቱ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ተሽከርካሪዎቹ ሙሉ ኢንሹራንስ ተገብቶላቸዋል ፤ የሰሌዳ ቁጥርም ተሰጥቷቸዋል፡፡ በብቃታቸው የቅድመ አገልግሎት ፍተሻ ተደርጎላቸዋል፡፡ መኪኖቹ የተገዙበት ከነሥራ ማስኬጃቸው ከ3 ሚሊዮን 600 ሺህ ብር ያልበለጠ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ቢገዙ ኑሮ ከብር 12 ሚሊዮን እስከ 14 ሚሊዮን ወጪ ይደረግ ነበር፡፡
ስለዚህ ከብር 9 ሚሊዮን እስከ 12 ሚሊዮን አትርፈናል፡፡ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ጉዳዩን በየደረጃው በማሳሰብ እስከ ፕሮፎርማ ድረስ ያለውን ሥራ በመሥራታቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች የሆኑት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ እና ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሙቀት መጠኑ ከ42 ዲ/ሴ በነበረበት ወቅት በዱባይ ከተማ ተገኝተው ያንን ሙቀት ተቋቁመው የመኪና ግዥ አከናውነው ቤተ  ክርስቲያናችንን ተጠቃሚ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት ለፍላጎታችን እና ለሥራችን መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላበረከተ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ በሀገረ ስብከታችን ዘመናዊ ማንዋል ተዘጋጅቶ የሰለጠኑ የሂሳብ ባለሙያዎች ለምረቃ በቅተዋል፡፡ ዘመናዊ ሞዴላ ሞዴሎችን ለማሳተም ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልን ለውጤት በቅተናል፡፡
ይህ የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን አቀርባለሁ በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥልቅ የሆነ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በማያያዝ ሀገረ ስብከቱ የሒሳብ እና በጀት የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ለሰጣቸው የሒሳብ ባለሙያዎች የምስክር ወረቀት ፣ የፐርሰንት ክፍያ ላጠናቀቁ አድባራት እና ገዳማት የምስጋና የምስክር ወረቀት ፣ ዱባይ ድረስ በመሄድ የመኪና ግዢ ላከናወኑ የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች ለሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ እና ለሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ሽልማት ከተደረገላቸው በኋላ የዚህ ሁሉ ሥራ የበላይ ተቆጣጣሪ ለሆኑት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በተጨማሪም ሀገረ ስብከቱ የመኪናውን ቁልፍ ለቅዱስነታቸው አስረክቧል፡፡ ከዚያም በማያያዝ የሲዳሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሀገረ ስብከቱን የልማት እንቅስቃሴ በማድነቅ ሙስና ከቤተ ክርስቲያን እንዲወገድ እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ምኞታቸውን በመግለጽ “አሰስል ለነ ፅዕለተነ” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ጠቅሰው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት ሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር ተግባር እና ሙስናን የማስወገድ ጅምሩ ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ ችግሮቹ በየጊዜው እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ስለሠራችሁ ለመሸለም በቅታችኋል ፤ ስለዚህ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ የፐርሰንት ክፍያ አጠቃላችሁ የከፈላችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! ፐርሰንት የቤተ ክርስቲያን የደም ሥር በመሆኑ ሊከፈል ይገባዋል፡፡ በቃለ ዓዋዲ በታዘዘው መሠረት ሥራችሁን ስለሠራችሁ ቤተ ክርስቲያን ታመሰግናችኋለች ፤ ሥራችሁን ያላስተካከላችሁ እንድታስተካክሉ እና እንድትሸለሙ አደራ እላለሁ፡፡ የአስራት ክፍያውን ሌሎች ወስደውታል ፤ ሒሳቡም ዘመናዊ እንዲሆን ሀገረ ስብከቱ እያደረገ ያለው ሂደት በጣም ያስመሰግናል፡፡ ሙስናን አጥብቀን ልናወግዝ እና ልንጸየፍ ይገባናል በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት እና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ሀገረ ስብከቱ ያዘጋጀውን የምሳ መርሃ ግብር ተካሄዶ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል ፡፡

{flike}{plusone}