የተቀፀል ፅጌ በዓል በድምቀት ተከበረ!!

0043

በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን ሲከበር የቆየው የተቀፀል ፅጌ በዓል በዘንድሮውም በ2008 ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጰሳት ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የአድባራትና ገዳማት ተወካዮች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡
በተረኛው በቅዱስ ቂርቆስ ደብር ሊቃውንት ፣ ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል፡፡ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያንዋ ሊቃውንት ቅኔያት ተበርክተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚከተለውን ትምህርታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
“ዘይፈቅድ ይትልወኒ ይፅልአ ለነፍሱ”
በዚህ አውደ ምህረት ተሰብስበን ስናደርሰው የነበረው ስብሐተ እግዚአብሔር ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን ዕፀ መስቀል የሚያስታውስ ነው፡፡ የተቀፀል ፅጌና የአዲሱን ዘመን በዓል ስናከብር ሁሉ ነገር አዲስ ይሆናል፤ አእምሮአችን ይታደሳል ፤ ምድር ትታደሳለች ፤ ዛፎች ይለመልማሉ ፣ አበቦች አበብው ይታያሉ፡፡
አበቦቹ እግዚአብሔር በሰጣቸው የተለያየ ሕብረ ቀለማት አሸብርቀው ይታያሉ፡፡ ይህ ስጦታ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ ከጨለማው ክረምት የወጣው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል፡፡
የተቀፀል ፅጌ በዓል መከበር የጀመረው በአፄ ገብረ መስቀልና በቅዱስ ያሬድ በ6ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በወቅቱ በዓሉ ይከበር የነበረው መስከረም 25 ቀን ነበር፡፡ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በዓሉ በቤተ መንግሥት ሲከበር ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ ከዚህ ወቅት ጀምሮ እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ በዓሉ ሳይከበር የቆየ ቢሆንም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከ1987ዓመ.ም ወዲህ ሲከበረው ቆይቶአል፡፡ በዓሉ መስከረም አስር እንዲከበር የተደረገበት ምክንያት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገባበት ወቅት ስለሆነ ነው፡፡ በዓሉም አፄ መስቀል ተብሎ ተሰይሟል፡፡ በማለት ቅዱስነታቸው የተቀፀል ፅጌን በዓል ጥንተ ምሥጢር በማብራራት ትምህርታዊ መልእክት ካስተላለፉና የመዝጊያ ጸሎት ካደረጉ በኋላ በዓሉን ለማብሰር ታስቦ የቀረበውን የተፈጥሮ አደይ አበባ ባርከው ከብፁዓን አባቶች ጀምረው በየደረጃው ላሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አድለዋቸዋል፡፡

{flike}{plusone}