ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለዩ

2832

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ የኢሊባቡርና የጋንቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ  አቡነ ፊልጶስ ነሐሴ 25/2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩ ሲሆን በዚሁ ዕለት  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በአበባ ሀገረ ስብከት ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎቸንና ሠራተኞች አስከሬናቸው  ካረፉበት ናሽናል ሆስፒታል ከቀኑ በ11፡00 ሰዓት በክብር ታጅቦ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  እርፏል፡፡

የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አጭር የሕይወት ታሪክ
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከአባታቸው ከአቶ ፈለቀ ለውጤ ከእናታቸው ከወ/ሮ አዛልነሽ ሙሉ በ1928 ዓ.ም. በወሎ ክፍለ ሀገር በላስታ ቡግና አውራጃ ሠራብጥ ካህናተ ሰማይ ከሚባል ቤተ ክርስቲያን

አካባቢ ተወለዱ፡፡
ብፁዕነታቸው በተወለዱበት በካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መምሬ ኃይሉ ከሚባሉ መምህር ንባብና ዳዊት ሰዓታትና አምስቱን አእማደ ምሥጢር ተምረዋል ፤ እንዲሁም ወደገነተ ማርያም በመሔድ፤ መሪጌታ ኃይለ ማርያም ከሚባሉ ፀዋትወ ዜማን ተምረዋል፤ በመቀጠልም አርካ አቦ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከአለቃ ኢሳይያስ ጾመ ድጓን በመማር ላይ እንዳሉ ወደግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የዲቁናን ማዕርግ ተቀበሉ፤ በኋላም ወደ ትውልድ ቀበሌያቸው ተመልሰው ጥቂት እንደቆዩ ወደ ደሴ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጽሐፈ መነኰሳትን ተምረዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ብፁዕነታቸው በፍፁም ሀሳባቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የመረጡት መንገድ ምንኵስናን በመሆኑ እንደገና ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ምንኵስናን ተቀበሉ፤ በተከታታይም ማዕርግ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከተሰጣቸው በኋላ ገደሚት ከምትባል ገዳም ገብተው ለጥቂት ጊዜ እንዳገለገሉ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአለቃ በዛብህ ወንድም ጋር ወደ ዞብል በመሔድ ከመምህር ወልደ ሰንበት ሰዋሰወ ቅኔን ተምረዋል ፡፡
ከዚያም ብፁዕነታቸው በአዲስ አበባ የወንጌል ትምህርት በማስተማር ሰፊ አገልግሎት ከመስጠታቸውም በላይ፡-
ሀየመድኃኔ ዓለም በጎ አድራጎት እየተባለ ይጠራ የነበረውን ማኅበር አደራጅተዋል፤
-የተማሪዎች አንድነት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አቋቁመዋል፤
-ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው ይሠሩ በነበረበት ወቅት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ተሸመዋል፤
-ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ለምግባረ ሠናይ የትሩፋት ሥራ ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጡ አባት በመሆናቸው በምግባረ ሠናይ የአረጋውያን እናቶችና አባቶች መርጃና መረዳጃ ማኅበርን በማቋቋም በርካታ ችግረኞች እንዲረዱ አድርገዋል ፡፡
ክፍል ሁለት
1.ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በመጀመሪያ የአለቃ በዛብህ ወንድም በአሠሩት በሐውልተ ስም መድኃኔ ዓለም ገዳም አለቃው እነደአረፉ ተተክተው ማገልገል ይችሉ ዘንድ በገዳሙ ማኅበር ተመርጠው ለብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ቀርበው የገዳሙ መምህርና አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ተሰይመዋል ፡፡
2.ከዚህ በኋላ የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል፤
3.የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣
4.የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ በመሆን ሠርተዋል፤
5.የጠቅላይ ቤተ ክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ፣
6.የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ሠርተዋል፤
7.ብፁዕነታቸው ባላቸው ከፍተኛ የአስተዳደር ብቃት በቅዱስ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በትጋት አገልግለዋል፤
8.ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቆይታቸው በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል እጥረት በየነበረበት ቦታ በመዘዋወር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በስፋት እንዲደርስ ከማድረጋቸውም በላይ በአዲስ አበባ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ ጧት ጧት የግብረ ገብ ትምህርት በማስተማር የስብከተ ወንጌል ማኅበራትን በየትምህርት ቤቶቹ እያቋቋሙ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦን አበርክተዋል ፡፡
ክፍል ሦስት
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በቁምስና ደረጃ የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲያገለግሉ በተፈቀደላቸው መሠረት፤ በ1986 ዓ.ም. ወደ ኢሉባቦር የቀድሞው መንበረ ጳጵስና መቱ ከተማ ላይ ሆነው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ጵጵስና ምርጫ አፈጻጸም የወጣውን መመዘኛ አሟልተው በመገኘታቸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በማዕርገ ጵጵስና እንዲያገለግሉ ኅዳር 4 ቀን 1987 ዓ.ም. ‹‹ጳጳስ ዘኢሉባቦር›› ተብለው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድ ተሾሙ፡፡
ብፁዕነታቸው በመጀመሪያ በቁምስና ደረጃ ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲመጡ የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ፈርሶ በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር እንዲተዳደር ተደርጎ ስለነበረ የመንበረ ጵጵስናውን የማደራጀትና የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት የማቋቋም ሥራ የብፁዕነታቸው ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ ቆይቶ ነበር፤
ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከቱን ካህናትና ምእመናንን በማስተባበር ገንዘብ በማሰባሰብ በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርተዋል፤ ከነዚህም መካከል በዘመናዊ ፕላን የተሠራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሕንፃ ተጠቃሽ ነው ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲመጡ የነበሩት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 217 ሲሆኑ በዘመነ ጵጵስናቸው ባደረጉት የማስተባበር ሥራ በአሁኑ ወቅት 320 የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ ፡፡
የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር ሊያድግ የቻለው፤ ብፁዕነታቸው በየወረዳው ሐዋርያዊ ጉዞ እያደረጉ በየመቃብር ቤቱ እያደሩ ስብከተ ወንጌልን በመስጠት የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ በማድረግ ታላላቅ ተግባራትን በማከናወናቸው ነው ፡፡
ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከቁምስና ደረጃ እስከ ማዕርገ ጵጵስና ድረስ በቆዩባቸው ሃያ ሁለት የሥራና የአገልግሎት ዘመናቸው በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት አዲስ ተቋቁመው በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ የተመረቁ ጠቅላላ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 93 መድረሱ ተረጋግጦአል ፡፡
ከዚህም ሌላ በሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና አካባቢ ከሚገኙት አድባራት መካከል የፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ገዳም ሆና እንድታገለግል አድርገዋል ፡፡
ክፍል ዐራት
ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 22 ቀን 1992 ዓ.ም. ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ደርበው እንዲሠሩ ተወስኖ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በደረሳቸው መመሪያ መሠረት ሁለቱን አህጉረ ስብከት አጣምረው በመምራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው የጋምቤላን ሀገረ ስብከት በሊቀ ጵጵስና እንዲመሩ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን አከናውነዋል፤ ከዚህም መካከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክን በመጋበዝ የክልሉን ብሔረሰብ ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ በማስጠመቅ ወደ ክርስትና ሕይወት እንዲገቡ አድርገዋል፤ ከዚህም ጋር በክልሉ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ አድርገዋል ፡፡
-ብፁዕነታቸው በጎደሬ ወረዳ ከስምንት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል፤
-ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በ1996 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የርእስ በርስ ግጭት የልጆቼን ችግር አብሬ መቋደስ አለብኝ በማለት ከቦታው ድረስ በመገኘት ሕዝቡን በማጽናናት የማረጋጋቱን ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አከናውነዋል፤ በቦታውም ዘላቂ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ በማስተባበር ድርሻቸውን በሚገባ ተወጥተዋል ፡፡
ክፍል አምስት
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በነዚህ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ክብርና አገልግሎት ከተሰየሙ ጀምሮ ባላቸው የሥራ ልምድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በመልካም አስተዳደር ሲመሩ ቆይተዋል ፡፡ ብፁዕነታቸው ባላቸው የብዙ ዓመታት የሥራ ልምድ በመጠቀም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ከሐምሌ 24 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየምና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመው ሲሠሩ ቆይተዋል ፡፡ ከዚህም ሌላ፤
-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ለሦስት ዓመታት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል ፡፡
-በዚህ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነታቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ተጠግተው በሥራ አጥነት የሚቸገሩትን አቅም በፈቀደ መጠን ሥራ እንዲያገኙ በማድረግ ከመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ጋር በመተባበር የዋና ሥራ አስኪያጅ ታላቅ ኃላፊነታቸውን በምስጋና አጠናቀዋል ፡፡
ክፍል ስድስት
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው በዓለም አቀፍ ጉኤያት ላይ ተሳትፈዋል ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በሕይወት ዘመናቸው ለሰው የሚራሩ ትሁትና ደግ የትሩፋት አባት እንደነበሩ በርካታ የደሀ ልጆችን በማሳደግ በማስተማር ራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለሀገር፣ ለወገን የሚጠቅሙ ልጆችን አፍርተዋል ፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በጊዜ ሳይገደቡ ዘወትር የጸሎት መጻሕፍት ከእጃቸው የማይለይ ለጸሎት የተጉና የትሩፋት አባት ነበሩ ፡፡
ብፁዕነታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሀገርና በውጭ ሀገር ሲታከሙ ቆይተው ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ፡፡ የቀብራቸውም ስነ ሥርዓት፤ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ተወካዮች ወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የብፁዕነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጋር ይደምርልን፤

{flike}{plusone}