የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስተር የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስ/ት/ቤት ወጣቶችን አነጋገሩ

                       በቀሲስ አሉላ ለማ የሀ/ስ/የሰ/ት/ቤት/ማ/ዋ/ክ/ኃላፈ

4001

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ የሰ/ት/ቤት ወጣቶች ጋር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዓርብ በ23/11/07 ከ8፡30 ሰዓት ጀምሮ አነጋገሩ፡፡ በስብሰባው የተነሱት የመወያያ አጀንዳዎች በሰላም፣ በአክራሪነት እና በቤተክርስቲያን አጠቃላይ ጉዳዮች ሲሆን፣ በርካታ ሐሳቦችና መወያዎች ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ አግኝተዋል፡፡
በስብሰባው የተሳተፉ የሰ/ት/ቤት ወጣቶችም ቤተክርስያናችን ለዘመናት ሰላምን ስትሰብክና የሌሎችንም እምነት በማክበር የኖረች በመሆኗ ይህን እሴት ጠብቀው እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል፡፡  በተጨማሪም አክራሪነትን በተመለከተ ቤተክርስቲያኗ በጽኑ እንደምትቃወም ተናግረዋል፡፡ የቤተክርስቲያናችን የውስጥ ጉዳዮች በተመለከተም ሌላው ተሳታፊዎች ያነሱት ነጥብ ሲሆን፤ መልካም አስተዳደርና የሥነ ምግባር ጉዳዮችን በተመለከተ ለምናነሳው ጥያቄ ምላሹ በፖሊስ መታሰርና አሸባሪ መባል በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተሳታፊዎቹ የግቢ ጉባኤያትን ፣ እምነት ሳይኖራቸው በቤተክርስቲያናችን ስለሚገኙ ግለሰቦች፣ እንዲሁም በከተማችን እየፈራረሱ ስለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና የአምልኮ ሥፍራዎች ለሰላም መደፍረስ አስተዋጽዖ ስለሚኖረው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሰ/ት/ቤት ወጣቶች ለተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ክቡር ሚኒስተር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም እና ሚኒስቴር ዲኤታው ውይይቱ መልካምና ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልጸው ለምታነሷቸው የአስተዳደርና የሥነ ምግባር ጥያቄዌዎች ምላሹ አሉታዊ ከሆነ፤ ጥያቄአችሁን የምታቀርቡበት መንገድ መፈተሽ እንደሚገባ በሰልፍ፣ ለረብሻና ለብጥብጥ ተጋላጭ በሆነ መልኩ ከሆነ ጥያቄ አቀራረቡን መገምገም እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ያለውን የሀሣብ ልዩነት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ ሊፈታ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ከአክራሪነትም ጋር በተገናኘ ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በምንም ዓይነት በአክራሪነት እንዳልተፈረጀች ነገር ግን በሥሯ በሚተዳደሩ አንዳንድ ማኅበራት ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በማኅበራት ውስጥ ተደብቀው የአክራሪነት ተግባራትን እንደሚያራምዱ፣ የጥገኝነት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትን በስፋት በማካሄድ ራሳቸውን እንደሚያበለጽጉ እንደሚታወቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 
በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ሥፍራዎች እየፈረሱ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት በተገናኘ በጋራ መፍትሔ እንደሚገኝ ገልጸው በአሁኑ ሰዓት ሀገረ ስብከቱ እያደረገ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማድነቅ ወጣቶቹም ለዚህ የለውጥ ሂደት አጋር እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ሰባክያነ ወንጌል እና ካህናት ጋር ተመሳሳይ ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

{flike}{plusone}