ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሙያ ማሻሸያ ስልጠና በመከታተል ላይ ላሉ የሒሳብ ባለሙያዎች በስልጠና ማዕከሉ በአካል በመገኘት የሥራ መመሪያና ቃለ ቡራኬ ሰጡ

03380
ቅዱስ ፓትርያርኩ በሀገረ ስብከቱ ተገኝተው ለሠልጣኞቹ አባታዊ ምክር ሲሰጡ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት የተወጣጡ የሂሳብ ባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና የሚወስዱበትን የስልጠና ማዕከል ለመጎብኘትና የሥራ መመሪያ ለመስጠት በተገኙበት ወቅት የሀገረ ስብከቱን ዋና ስራ አስኪያጅ ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ዋና  የክፍል ኃላፊዎች በሥፍራው በመገኘት እየተሰጠ ያለውን  በኮምፒውተር የታገዘ ስለጠና ለማየት ችለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ስልጠናውን በተመለከተ ለማን እና ለምን እየተሰጠ እንዳለ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን  ከሥራ አስኪያጁ በመቀጠል ስልጠናውን በመስጠት ላይ ዩሚገኙት የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም አሁን ስልጠናውን በመውሰድ ላይ ያሉት ሰልጣኞች ከየትም የመጡ ሳይሆን በዚህው በቤተክርስቲያን ውስጥ ያደጉና አሁንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት ላይ ያሉ በሙያቸው ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ናቸው፡፡ ለእነሱ ነው የሙያ ማሻሻያ ስልጥናው እይተሰጠ ያለው ሲሉ ገለጻ አድረገዋል፡፡
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና በክልል ትግራይ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት  ሊቀ ጳጳስ ስልጠናወን በተመለከተ ሰፋ ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው መካከል  መቅደም ያለበት ትምህርት ነው፡፡ እናንተም እያደረጋችሁ ላችሁት ይህንኑ ነው፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ማንም ሩጦ ሊቀድማት አይችልም፡፡ ይህ ዕውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ እናንተ የቤተክርስቲያኗ ልጆች በሃይማኖት እና በትምህርት በርትታችሁ ስትገኙ ነው፡፡ ስለዚህ ስትማሩ  የሰጡዋችሁን መቀበል ብቻ ሳይሆን ጠያቄዎችም ጭምር መሆን አለባችሁ ፡፡
መጨነቅ ያለባችሁ ሰዎች ምን ይሉናል? ምን እያሉን ነው ብላችሁ አየደለም መጨነቅ ያለባችሁ እየሠራችሁት ያላችሁት ሥራ  ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማል ወይስ  ይጎዳል ብላችሁ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ነገር እስከሠራችሁ ድረስ  ለምትሠሩት ሥራ እውቅና ይሰጣል፡፡ ካሉ በኋላ በተማሪና በአስተማሪ መካከል  ያለው ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት አባታዊ ለዛን በተመላ ምሳሌያዊ አነጋገር ሲያስረዱ፡- ስለግብርና እና የውሃ ሀብት እንዲሁም በከርሰ ምድር ውስጥ ስላሉ ማዕዳናት የሚማሩ ተማሪዎች ከመምህራቸው ፊት ቀርበው ሲማሩ መምህሩ ከሚያስተምሩበት ርዕስ ወጥተው መሬት ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ወይም ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ትዞራለች ስትዞርም እየተሽከረከረች ነው በማለት  ማስተማራቸውን ይቀጥላሉ፡፡  ተማሪዎቹ የሰጡዋቸውን ብቻ የሚቀበሉ ሳይሆኑ የሚጠቅማቸውን እና የሚመለከታቸውን ለይተው የሚያውቁ ስለነበሩ  መምህር መሬት ዕቃ እስካልሰበረች ድረስ  ትሽከርከር እኛ የምንፈልገው በከርሰ ምድር ውስጥ ስላሉ ማዕድናት እንዲያስተምሩን ነው፡፡ በማለት ወደ ርእሳቸው መለሷቸው፡፡ስለዚህ እናንተም ስትሰለጥኑ ለቤተክርስቱያኗ የሚጠቅመውን  ነገር መጠየቅ አለባችሁ፡፡ ይህን ስታደርጉ ነው ቤተክርስቲያኗን ከዘመናዊው አሰራር ጋር የምታገናኟት፡፡ ስለዚህ  ትኩረታችሁ እዚሁ ላይ መሆን አለበት በማለት መልዕክታቸውን አስትላልፈዋል፡፡ 
በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለአሰልጣኙ እና  ስልጠናውን  በበላይነት ለሚመሩት ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጀ ጥያቄዎች ከማቅረባቸውም በተጨማሪ ገንቢ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሥልጠና ለሁለት ነገር ይጠቅማል፡፡
-በመጀመሪያ ደረጃ ለራሳችሁ
-በሁለተኛ ደረጃ  ለሀገራችሁ እና ለቤተክርስቲያናችሁ ስለዚህ ራሳችሁንም ቤተክርስቲያናችሁንም ብሎም ሀገራችሁን ለመጥቀም የምትወስዱት ስልጠና እጅግ ይጠቅማችኋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው እየወሰዳችሁት ያለውን ስልጠና ጣዕሙን ለይታችሁ ማወቅ ስትችሉ ነው፡፡ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም ብላችሁ ጣዕሙን ካላወቃችሁት የተማራችሁትን ለሌላ ሰው ማስተማር አትችሉም፡፡ የምትሰለጥኑት ደግሞ የተማራችሁትን ለሌላው ለማስተላለፍ ነው፡፡
ቤተክርስቲያናችን እስካሁን  ስትጠቀሙበት የነበረውን የሒሳብ አሰራር በመተው መላው ዓለም እየሠራበት ወዳለው ዘመናዊ የሒሳብ አሠራር  መሸጋገር የምትችለው እናንተ የሚሰጣችሁን ስልጠና ኃላፊነት ተሰምቷችሁ በአግባቡ ስትረዱት ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን  የእውቀትም ሆነ የሰው ደሀ አይደለችም፡፡ አሁን ዓለም እየተጠቀመበት ያለው የሒሳብ ሙያ የተገኘው ከዚህችው ቤተክርስቲያን ነው፡፡  በመሆኑም  ቤተክርስቲያን የሰውና የእውቀት ብቻ ሳይሆን የገንዘብም ደሀ አይደለችም ገንዘቡ በአግባቡ እንዲያዝ ደግሞ በዚህ የስልጠና ማዕከል ተገኝታችሁ ስልጠናውን በመወሰድ ላይ ያላችሁ የቤተክርስቲያኗ ልጆች ጠንክራችሁ መሥራት ይጠበቅባችኋል፡፡
ምክንያቱም የምናሰለጥናችሁ ይህን እንድታደርጉ ነው፡፡ የሒሳብ ሥራ ታማኝነትን ይጠይቃል፡፡ ለቤተክርስቲያናችሁ ለራሳችሁም ስትሉ ታማኞች መሆን አለባችሁ፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ይህን የስልጠና መርሐ ግብር ያዘጋጃችሁ የሀገረ ስብከቱ የሥራ አመራሮች ሁላችሁም  ልትመሰገኑ ይገባል፡፡ በእውነቱ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡ በሀገረ ስብከታችን ስልጠናው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም ጠንክረን እንሠራለን በማለት ቃለ ምእዳንና ቡራኬ በመስጠት የዕለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ ስልጠናው ግን ይቀጥላል፡፡

{flike}{plusone}