የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአድባራትና ገዳማት የሒሳብ ሠራተኞች ሲሰጥ የቀየውን አንደኛ ዙር የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና በኮምፒውተር በተደገፈ የተግባር ሥልጠና መስጠት ቀጥሏል!!

00336
የሀ/ስ/ሒ/በ/ዋ/ክ/ኃ/ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ሥልጠናውን ሲሰጡ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥሩ ለሚገኙ አድባራትና ገዳማት የሒሳብ ሠራተኞች ሲሰጥ የቆየውን አንደኛ ዙር የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና በኮምፒውተር በተደገፈ መልኩ የተግባር ሥልጠና መስጠት የቀጠለ ሲሆን ሥልጠናውን በበላይነት በማስተባበርና በመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የትግበራ ሥልጠናውን አስመልክተው ለሠልጣኞቹ ባስተላለፉት መልእክት የለውጥን መሠረታዊ ምንነት የቤተ ክርስቲያን ለውጥ ምንን እንደሚአካትት፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚአስፈልገው ለውጥ ምን ዓይነት እንደሆነ፣ ለውጥ የማያስፈልገው በምንና በምን  እንደሆነ፣ የለውጥ መሪያዎች የሚባሉት የትኞቹ እንደሆኑ፣የለውጡ ተጠቃሚዎች እነማን እንደሆኑ፣የለውጥ ሥራ የሚአሠጋቸው አካላት የትኞቹ እንደሆኑ፣ ለውጥ ከየት መጀመር እንዳለበት በሚሉት ንዑሳን አርእስቶች፣ የሥልጣኞችን ልብ ሰርሥሮ በሚገባ ሁኔታ ዋና ሥራ አስኪያጁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከዚያም በማያያዝ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር በሥልጠናው ማዕከል ተገኝተው ለሰልጣኞቹ ባስተላለፉት መልእክት በቤተክርስቲያናችን ስለገንዘብ ያለው አስተያየትና አመለካከት ሊያድግ እንደሚገባው ፣ሙዳዬ ምፅዋት ከማስተዳደር ፋይናንስን ማስተዳደር ወደሚለው ዘመናዊ አስተሳሰብ መድረስ እንደሚገባ፣ በፍትሐ ነገሥት ቀኖና ላይ የሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ የእግዚአብሔር ገንዘብ በመሆኑ ይህንን የእግዚአብሔር ገንዘብ ማስተዳደር ያለበት የእግዚአብሔር አገልጋይ ሊቀ ጳጳስ እንደሆነ መደንገጉንና በመጽሐፍ ቅዱስም ገንዘብ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ስለሆነ የእግዚአብሔር ሰው ሊያስተዳድረው የሚገባ መሆኑ በአካውንትና በሙዳዬ ምፅዋት መካከል ያለው ፅንሰ ሐሳብ እኩል ነው፡፡ ስለዚህ አካውንትም ሙዳዬ ምፅዋትም እኩል ቢሆኑም ነገር ግን የሰው እይታ እንዲያድግ ወደ አካውንት ለማድረግ ፅንሰ ሐሳብ መለወጥ አለበት በማለት ዘመናዊነትን በተላበሰ አገላለፅ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም የሥልጠናው አቅራቢ በመንፈሳዊ የትምህት ዘርፍ የድጓና የዝማሬ መዋስት እና በዘመናዊና በአካውንቲክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከባህርዳር ዩንቨርስቲ ያገኙት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ በኮምፒውተር የታገዘውን የትግበራ ሠልጠና ማሠልጠን በጀመሩበት በዚሁ ዕለት በመግቢያ ንግግራቸው እንደለፁት ወጪያአችን ከገቢአችን መብለጥ የለበትም ወጪያችን ገቢአችን ከበለጠ የሚኖረን ሀብት የተጣራ ሀብት ሳይሆን ዕዳ ብቻ ነው የሚኖረን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ማድረግ ያለብን ሥራውንና ሠራተኛውን ማመጣጠን ነው ካሉ በኋላ ሳይንሳዊ ወደ ሆነው የሒሳብ ጥበብ በመግባት የትግበራ ሥልጠናውን መስጠት ጀምረዋል ከሠልጣኞቹም ጋር የሚአሳዩት መግባባት ይበል የሚባል ነው፡፡
ይህን ሳይንሳዊ የትግበራ ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከብር ሁለት መቶ ሺህ ባላነሰ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ብዛታቸው አስራ ስድስት የሚሆኑ ዘመናዊ ኮምፒውተሮችን ገዝቶ በስልጠና ማዕከሉ ቋሚ ሆነው ሁል ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ያደረገ በመሆኑ ሊመበገን ይገባዋል፡፡

{flike}{plusone}