ለጋራዥ አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ የነበረው የቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ቀደሞ የመማር ማስተማር ታሪኩ ተመለሰ!
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ትምህርት ቤትን አስመልክቶ የካቴድራሉ የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀ መንበር ኮ/ል ክፍሉ ሀብተወልድ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ት/ቤቱ በወቅቱ በነበረበት የሥራ አፈጻጸም ጉድለት የተነሳ ከትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው መመሪያ መሠረት የመማር ማስተማር ተግባሩን እንዲያቆም መደረጉን ምክንያት በማድረግ በወቅቱ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ውሳኔ ት/ቤቱ ወደ ጋራዥነት ተለውጦ በብር 17,000.00 ለግለሰቦች እንዲከራይ ተደርጎ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን የመማር መስተማር ሥራውን እንዲቀጥል ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ከግለሰቦች ጋር የተደረገው የኪራይ ውል ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ከውሉ መቋረጥ ጋር ተያይዞ በውሉ አፈጻጸም ላይ አለመግባባት በመፈጠሩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ የአመራር አቅጣጫ በመስጠታቸው ጋራዡ ከነሐሴ ወር 2007 ዓ/ም ጀምሮ ሥራውን እንዲያቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ለስምምነቱም የ500,000 ብር የዋስትና መረጃ ካቴድራሉ ተቀብሏል፡፡ በስምምነቱ ሰነድ ላይ የመማሪያ ክፍሎቹ በቅድሚያ እንዲለቀቁ በመደረጉ አብዛኞቹ የመማሪያ ክፍሎች ከተከራዮች እጅ ወጥተው በካቴድራሉ እጅ ገብተዋል፡፡ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር አክለው እንደገለጹት ትምህርት ቤቱ ወደ ቀደመው የማስተማር ተግባሩ እንዲመለስ ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር የመጻጻፍ ተግባር ተጀምሯል፡፡
አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላም ትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ተግባሩን እንደሚጀምር የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ገልጿል፡፡
{flike}{plusone}