ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ተመለሱ!!

0572

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ኪልቅያ ካቶሊኮስ የአርመን ሰማዕታትን አንድ መቶኛ ዓመት አከባበር ምክንያት በማድረግና በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ይቻል ዘንድ ባደረጉላቸው ይፋዊ ጥሪ መሠረት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን አስከትለው ከሐምሌ 9-14 ቀን 2007 ዓ/ም በቤይሩት ሊባኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝት አደርገዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በቤይሩት ሊባኖስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በቤይሩት የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ሐሊማ መሐመድና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአካባቢው ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም በሊባኖስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮች ጋር በመሆን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ በሊባኖስ በነበራቸው ቆይታ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባዘጋጀችው ዓለም አቀፍና የተለያዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ላይ በተሳተፉበት ወቅት ታሪካዊ መልእክት አስላልፈዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በንግግራቸው የኢትዮጵያና የአርመን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በማኅበረሰብ ትሥሥር ላይ የተመሠረተ ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ የሆነ መልካም ግንኙነት የነበራቸው መሆኑን ከመግለጽ በተጨማሪ የአሁኑ ትውልድም የሁለቱን ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር መጣር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክትም ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ስለ ሃይማኖታቸው ሰማዕትነት የተቀበሉት አርመኖችን ስናስብም በወቅቱ የተፈጸመውን ድርጊት ለመበቀልና ጥላቻን ለማስፋፋት ሳይሆን ሰማዕታቱን በክብር በመዘከር ተመሳሳይ እልቂትና፣ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የሚገባውን ክብር እንዲሰጠውና ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግለት ለማሳሰብ ነው በማለት ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በሊቢያ የሜድትራንያን ባህር ዳርቻ በኢትዮጵያውንና በግብፃውያን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ተግባር የዚህ ማሳያ ስለሆነ ከታሪክ መማርና ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያ መስጠት ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡   
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ከዚሁ ይፋዊ ጉብኝታቸው ጎን ለጎን በሊባኖስ ቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመሠረቱት የደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በመገኘት በዚያ ለሚገኙ ምእመናን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም በሊባኖስ ቤይሩት የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሰዳር፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና በአካባቢው የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት ለሁለት ቀናት ያህል ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መልእክቶች አስተላልፈዋል፡፡ በተለይ ወጣቶች በስደት በሚኖሩበት አካባቢ መልካም ስማቸውን በመጠበቅ፣ በምግባራቸው ታማኝ፣ በሥራቸው ትጉ እንዲሆኑ በጥሩ ሥነ ምግባርና በሐቀኝነት የሚኖሩበትን ሀገር ሕግና ሥርዓት በደንብ በማወቅና በማክበር ራሳችሁን እንድታስከብሩ በማለት አባታዊ ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያውን መገለጫ የሆኑ ልዩ ዕሴቶቻችን በማክበር ከራሳችሁ አልፋችሁ የሀገራችሁንም መልካም ገጽታ እንድታሳዩ፣ ወገኖቻችሁን እንድትጠቅሙ ምግባራችሁ የቃና፣ ባህላችሁን የምታከብሩ መሆን ይገባችኋል፤ ይህን ካደረጋችሁ የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ትሆናላችሁ ብለዋል፡፡
አያይዘውም ቅዱስ ፓትርያርኩ፡- “ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መተዛዘንና መደጋገፍ የኢትዮጵያውያን ጥንታውያን ልምዶችና መልካም ዕሴቶቻችን ስለሆኑ እናንተም እንደአባቶቻችሁ በዚሁ ብትኖሩ ሳይከፋችሁ፣ ሆድ ሳይብሳችሁ፣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ እንደ አባትና እናት ሆናችሁ፣ ችግር ፈችዎች መሆን ይገባችኋል፡፡ በተለይ እናንተ ልጆቻችን በበለጠ እንደምታውቁት ብዙ ወገኖቻችን በሕገ ወጥ ስደት ምክንያት ለበርካታ ያልተጠበቁ አደጋዎች እየተጋለጡ፣ ሠርተው ያፈሩት ሀብትና ንብረት እየተቀሙ፣ ሕይወታቸውን እያጡ ስለሆነ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመግታት ከሀገር መውጣት ካለባቸውም በሕጋዊ መንገድ እንዲወጡ፣ አለበለዚያ በሀገራቸው ሠርተው እንዲለወጡ እንድትመክሩ እና  የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራየ የጸና ነው” ብለዋል፡፡
በሊባኖስ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ሐሊማ በበኩላቸው በሊባኖስ የምትኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን አጠቃላይ ኮሚኒቲው ከኤምባሲው ጋር በመተባበር እጅግ የሚያስመሰግን ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ገልጸው ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በምንልክበት ጊዜ ያለ ምንም ልዩነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሁሉአቀፍ የሚያስፈልገውን በማድረግና በማስተባበር ወገኖቻችንን በማቀፍና በመደገፍ ተምሳሌታዊ ሥራ እየሠሩ ስለሚገኙ ቅዱስ አባታችን በተገኙበት የቤተ ክርስቲያንዋ አባቶችና ምዕመናን ሁሉንም ማመስገን እወዳለሁ ካሉ በኋላ ለወደፊትም ይህንን ወገንን የማገዝ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ በማለት አሳስበዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ በተጨማሪ የአኀት አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮችና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ልዩ ልዩ መሪዎችን ያነጋገሩ ሲሆን ወደ ሀገር ቤት ከመመለሳቸው በፊትም በአርመንና በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት ስለሚጠነክርበት ሁኔታ፣ ክብርት አምባሳደር፣ በቤይሩት የሚገኘው አጥቢያ ተወካዮች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዑክ በሊባኖስ ያደረጉትን የ5 ቀን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናቆ ማክሰኞ ሐምሌ 14/2007ዓ.ም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

{flike}{plusone}