የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአድባራትና ገዳማት የሒሳብ ሠራተኞች የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት ጀመረ

0244
ክቡር ዋና ሥራአስከያጁ በሥልጠናው ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሥሩ ለሚገኙ አድባራትና ገዳማት የሒሳብ ሠራተኞች የሙያ ማሻሸያ ሥልጠና መስጠት የጀመረ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሥልጠናው በተከፈተበት ወቅት ሐምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ የሥልጠና ማዕከል በመገኘት ለሰልጣኞቹ ባስተላለፉት መልእክት ይህ ሥልጠና በቤተክርስቲያናችን እየተከናወነ ያለውን የሒሳብ ሥራ ለማዳበር የተዘጋጀ ሥልጠና ነው፡፡ ዛሬ ይህንን ሥልጠና በመሳተፍ ላይ የምትገኙ ነገ ሌላውን ማሠልጠን ትችላላችሁ ብለን እናስባለን ÷ ሥልጠናውን ውጤታማ ለማድረግ በሀገረ ስብከታችን አይቲ ክፍል ለኮምፒውተሮቻችሁ አስፈላጊው ሶፍትዌር ይሰጣል፡፡ በመሠረቱ ትምህርት ማለት ከአንዱ ወደሌላው የሚዛዋወር ነው ዛሬ በዘመናችን የተለያዩ ትችት አቅራቢ ክፍሎች አሉ በመሆኑም እነዚህ ተችዎች በሚአነሱአቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ከእናንተ ጋር ውይይት ማድረግ እፈልጋለሁ በማለት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሥልጠናውን በከፈቱበት ወቅት አስተዳደራዊ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡
በማያያዝም የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ የሥልጠናውን መሠረታዊ አላማ አስመልክተው በሰጡት ትምህርታዊ ሐሳብ ይህ ሥልጠና በ2001 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያቶች ተቋርጦ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንደተባለው ዛሬ በይፋ ሊጀመር ችሏል፡፡ የሥልጠናው ጊዜ አሁን ነው ማለት እንችላለን ÷ ይህ ሥልጠና በጣም አስፈላጊ ነው ምክንያቱም የምናንቀሳቅሰው ገንዘብ ከብዙ ድርጅቶች የበለጠ ነው፡፡ የሒሳብ አያያዛችን የመቀየሪያ /የለውጥ/ ጊዜው አሁን ነው÷ ምክንያቱም የተፈጠረልን ምቹ ሁኔታ አሁን ስለሆነ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ይከናወን የነበረው የቅጥር ፣የዕድገትና የዝውውር ተግባር ብቻ ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት በሂሣብ አያያዛችን ዙሪያ ለውጥ ሊመጣ አልቻለም፡፡

0253
የሀ/ስ/ሒ/በ/ዋ/ክ/ኃ/ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ሥልጠናውን ሲሰጡ

የሥራ መሪዎች የነበሩት የሒሳቡ ሥራ የማይመለከታቸው ይመስላቸው ነበር÷ አሁን ያለው አመራር ግን እንደዚያ አይደለም ÷ለሒሳብ የሚአስብ መሪ አለን÷ የሥልጠናውም ዋና ዓላማ ወጥ የሆነ ሥራ መሥራት እንድንችል በማሰብ ነው በማለት ሊቀ ጠበብቱ የመግቢያ ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላ “ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በፋይናንስና በጀት የተዘጋጀ የሒሳና መዝገብ አያያዝ ሥልጠና “ በተሰኘ መሪ ርዕስ ለሠልጣኞቹ የሙሉ ቀን ትምህርታዊ ሥልጠና ሰጥተዋል በስልጠናው ዝግጅት ላይ ከተቀመጡት ዋና ዋና ነጥቦች የሒሳብ ሥራ ምንነት፣ የሒሳብ ሥራ ጥቅም በሒሳብ ሥራ ውስጥ በጥቅም ላይ የሚውሉ ቃላትና ጽንሰ ሐሳብ ፣የሒሳብና መዝገብ አያያዝ ዓላማ፣የገንዘብ ነክ ክንውኖችን መመዝገብ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
በዓይነቱ ልዩ የሆነው ይህ ሥልጠና የመጀመሪያ ዙር ቁጥራቸው 30 የሚደርሱ የሒሳብ ሠራተኞችን የሚአቅፍ ሲሆን ሥልጠናው ለ3 ተከታታይ ሳምንታት እንደሚቆይ ከበጀትና ሒሳብ ዋና ክፍል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ኢኮኖሚአዊ እንቅስቃሴዎችን በገንዘብ በመተመን ጠቃሚ መረጃን በመስጠት የሚታወቀው  ይህ የሒሳብ ጥበብ በየዙሩ ለሁሉም አድባራትና ገዳማት ሒሳብ ሹሞች ሊሰጥ እንደሚችል የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ኃላፊው ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ አክለው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን በየወቅቱ የሚሰጠውን  ጠቃሚ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና እየተከታተለ ለአንባብያን መረጃ የምንሰጥ መሆኑን ለመጠቆም ይፈልጋል፡፡

{flike}{plusone}