የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በሦስት አብያተ ክርስቲያናት የሥራ ጎብኝት አደረጉ

0161
ክቡር ዋና ሥራአስከያጁ የአብነት ተማሪዎችን ሲጎበኙ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የሀገረ ስብከቱ ዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ፣ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ፣ አርብ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም ከሰዓት በፊት በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ቅ/ማርያም ካቴድራል በመገኘት የብሎኬት ማምረቻ ማዕከልን፣ የተለያዩ ልማታዊ የግንባታ ሥራዎችን ለረጅም ዘመን በግለሰቦች እጅ ተይዞ የነበረውን የፉካ መቃብር፤ ከብዙ ክርክር  በኋላ ለካቴድራሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውና ተጨማሪ የፉካ መቃብር ግንባታን፤ በተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች ያሸበረቀውን የካታድራሉን ግቢ፣ የካቴድራሉ ቀዳሚ ይዞታ የነበሩት እና ነገር ግን በግለሰቦች እጅ ተይዘው ከቆዩ በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ ለካቴድራሉ የተመለሱ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችን እና ካቴድራሉ ያስገነባቸውን የአብነት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል፡፡
የደብር ምጥማቅ ቅ/ማርያም ካቴድራል  ሁለት መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ያለው ሲሆን በዚህ ሰፊ መሬት ላይ የልማት ሥራውና መንፈሳዊ አገልግሎቱ ጎን ለጎን እኩል ሲከናወን ማየት እጅግ የሆነ መንፈሳዊ እርካታን ይሰጣል፡፡
ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ መጠነ ሰፊ የሆነውን የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅ/ማርያም ካቴድራል የልማት ሥራዎችን እየተዘዋወሩ ከጎበኙ በኋላ፣ በካቴድራሉ ቅጽር ግቢ ጥግ ይዘው ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያናችንን የዜማ፣ የአቋቋም፣ የቅዳሴ፣ የቅኔ፣ የመጽሐፍተ ብሎያት ትርጓሜ እና የንባብ ትምህርቶችን ለበርካታ ደቀመዛምርቶቻቸው የሚያስተምሩ መምህራንን በማስተማር ተግባራቸው በተሰለፉበት ወቅት፣ የጉብኝት ተግባር ፈጽመዋል፡፡በደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅ/ማርያም ካቴድራል  ሰበካ ጉባኤ የሚያስተምራቸው ደቀመዝሙርት የደጓ 35፣ የብሉያት 10፣የአቋቋም 25፣ የቅዳሴ 10ና የቅኔ 20 በጠቅላላው ለመቶ ደቀመዛሙርት ለእያንዳንዳቸው ብር 500 ወርሃዊ ደመወዝ /ድርጎ/ ተመድቦላቸው የሚማሩ ሲሆን ነገር ግን በተመላላሽነት ብዙ ደቀ መዝሙት በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸው ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ተስፋ ነው፡፡
የካቴድራሉ መምህራን በዋና ሥራ አስከያጁ በመጎብኘታቸው  የተሰማቸውን ልባዊና ያልታሰበ ደስታ የገለጹ ሲሆን ይህ የሥራ አስኪያጁ ጉብኝትና የማበረታቻ መልዕክት ደቀ መዛምርቱ ለሚከታተሏቸው ትምህርቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡና  ጠንክረው ለመማር እንዲችሉ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

0204
ክቡር ዋና ሥራአስከያጁ የልማት ሥራዎችን ሲጎበኙ

ይህ በእንዲህ እያለ በዚሁ ዕለት ሥራ አስኪያጁ ከልማትና ዕቅድ ክፍል ኃፊው ጋር ወደ የረር ቅዱስ ኡራአል ቤተክርስቲያን ያመሩ ሲሆን ለረጅም ጊዜ በክርክር ላይ የቆየውን የየረር ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ይዞታን አስመልክተው በግቢው እየተዘዋወሩ ከጎበኙ በኋላ በጉዳዩ ዙሪያ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር አጭር ውይይት አድርገዋል፡፡ ከዚያም በኋላ በአያት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ጎብኝተዋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን ሥራ ዋና አስከያጁ እንዲህ አይነቱን ጠቃሚ የሆነ የሥራ ጉብኝት ተግባር አጠናክረው ሊቀጥሉበት እንደሚገባ እየጠቆምን በጉብኝቱ ወቅት ከታዩት የልማት ተግባራት የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምሕረት ካቴድራል እያከናወናቸው ያሉት የልማት ተግባራት እጅግ በጣም ዘርፈ ብዙ ሲሆኑ በሁሉም የልማት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውጤታማ የሆነ ሥራ እየተሠራ የሚገኝ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
እየተሠሩ የሚገኙትን የልማት ሥራዎችን በዝርዝር የምናቀርብ መሆኑኑ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ሌሎች ሰፊ የልማት ይዞታ ያላቸው አድባራት፤ ካቴድራሎችና ገዳማትም የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ካቴድራልን አብነት ሊአደርጉ ይገባቸዋል፡፡ የሀገር ስብከቱ የዕቅዱና ልማት ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለም ይህ የሥራ ጉብኝት እንዲጠናከር የማስባበር ተግባር እየፈጸሙ በመሆናቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባቸው እየጠቆምን ለወደፊቱም ከዚህ የበለጠ የሥራ እንቅስቃሴ ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል እንላለን፡፡

{flike}{plusone}