አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ተመረቀ!!

m0177
ቅዱስነታቸው ፕሮጀክቱን ባርከው ሲከፍቱ

ቁጥራቸው ከ3000 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ሕዝብ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፖትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ አረጋሽ በየነ ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም የተመረቀው “አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠር ኑሮ መሻሻያ ፕሮጀክት” ዋና ዓላማ በሞት ሥጋ ከዚህ ዓለም የተለዩት ሊቅና ሊቀጳጳስ ብፁዕ አባ መርሐ ክርስቶስ የጨለቆት ገበሬን ከድህነት ጥገኛነት ለማላቀቅ ባላቸው ምኞት የተነሳ በሕይወት ዘመናቸው ፕሮጀክት ፕሮፖዛል አስቀርፀው ከአንዲት ጀርመናዊት የዕርዳታ ባለሙያ ጋር ያደረጉትን ውይይት ምክንያት በማድረግ ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን የልማት ክንፍ የሆነው ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ባደረገው ጥረት ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ተደርጓል፡፡
“አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” ሕዝቡ ሠርቶ እንዲበላ በማሰብ ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ይሰጡት የነበረውን ትምህርት መሠረት ያደረገ ሲሆን የፕሮጀክቱ መሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” 2 ተሰሎንቄ 3፤10
“He who does not work should not eat” 2 Thes. 3:10
በታላቁ የቤተ ክርስቲያን ምሁርና ሊቀ በብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ስም ተቀርፆ በሥራ ላይ የዋለው “አቡነ መርሐ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” የተከናወኑት የልማት ተግባራት ባለ16 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሥራ ፣ የመሥኖ ሥራ ፣ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማጠናከር ፣ የሥራ አጥ ወጣቶች የገቢ ምንጭ ማስገኛ ፣ የአካባቢው ሕዝብ የጤና አገልግሎት መስጠት ፣ ሲሆን ለፕሮጀክቱ በተመደበው ብር አስራ ሦስት ሚሊዮን ሁለት ትልልቅ ድልድዮች ፣ አስራ ስምንት የቱቦ ድልድዮች ፣ በመስኖ ልማት ዘርፍ ስድሳ አምስት ሄክታር መሬት ሊአለማ የሚችል የመስኖ ቦይ ፣ ሁለት የመስኖ ውሀ ማሸጋገሪያ ድልድዮች የተፈጥሮ ሀብትን ለማንቀሳቀስ የሚአስችል በስድሳ ሄክታር መሬት ላይ ዘጠኝ የጋራ ዕርከኖች መቶ አምስት ቀፎ ከነሙሉ ቁሳቁሳቸው የወተት ሀብት ልማት ሥራ ለሀያ አንድ ወጣቶች ፣ ሦስት መቶ ሃያ ሁለት ሺ ብር በሚገመት የገንዘብ ወጪ የተገዙ የህክምና መማሪያዎችና ቁሳቁሶች ተገዝተው በሥራ ላይ መሆናቸውን በምረቃ መርሐ ግብሩ ወቅት ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሎአል፡፡

m0253

የልማትና ክርስቲያናዊ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር አግደው ረዴ እንዳብራሩት በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ድጋፍና በልማት ኮሚሽኑ ከፍተኛ ጥረት እየተከናወኑ ከሚገኙት በርካታ የልማት ሥራዎች መካከል ደቦለዓለም በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት የተሠራ “አቡነ መርሐ ክርስቶስ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” አንዱ ነው፡፡ ኮሚሽነሩ አክለው እንደገለፁ የልማት ኮሚሽኑ በክልሉ የበለጠና የላቀ የልማት ሥራ ለመሥራት አቅዷል በማለት ማብራሮያ የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በጨለቆት ደብረ ምህረት ቅድስት ሥላሴ አውደ ምሕረት በአስተላለፉት መልእክት “ብፁዕ ሕዝብ ዘእግዚአብሔር አምላኩ”
በዚህ ታሪካዊ ቦታ በመገኘታችንና በዚህ ታሪካዊ ቦታ የተከናወኑ ሥራዎችን በዐይናችን በማየታችን የተሰማን ደስታ ወሰን የሌለው መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ ይህ ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታ የሊቃውንት ፣ የቅርሳ ቅርስ የብዙ ታሪካውያት መጻሕፍት ማህደር የሆነው ታላቁ ገዳም ለሀገራችን ጌጥ ሲሆን ለቤተ ክርስቲያናችንም ኩራት ነው፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሊቃውንት መፍለቂያ የቃለ እግዚአብሔር ምንጭ ናቸው፡፡ እነዚህ በዐይናችን የምናያቸው ጥንታውያን መጻሕፍትና የነገሥታት ዘውዶች ከቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የተበረከቱ ናቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ተጠብቀው መቆየታቸው በጣም ያስደስታል፡፡ ይህንን ታሪክ ጠብቆ የቆየ ሕዝብ “ብፁዕ ሕዝብ ዘእግዚአብሔር አምላኩ” ይባላል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላኩ ፣ እግዚአብሔር ፈጣሪው መሆኑን ያመነ ሕዝብ ንዑድና ክቡር ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ልጆቻችሁ ለወደፊቱ ተረክበውና ጠብቀው የእናንተን ፈለግ ተከትለው ሊጓዙ ይገባል፡፡
በብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ስም የተዘጋጀው መንገድ መታሰቢያነቱ ለብፁዕነታቸው ሆኖ ተጠቃሚው ግን ሕዝብ ነው፡፡ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ዞንና ሀገረ ስብከት በመተባበር የሠሩት ሥራ በእጅጉ የሚአስደስት ስለሆነ እግዚአብሔር አምላክ በበረከቱ ይባርካቸው እንላለን፡፡ በማለት ቅዱስነታቸው አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በበኩሉ ለማለት የሚፈልገው የልማት ክንፍ በመባል የሚታወቀውና በታታሪው ሊቀጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የሚመራው የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በመላው ሀገራችን እያከናወናቸው ከሚገኙት የልማት ተግባራት መካከል “አቡነ መርሐ ክርስቶስ ጨለቆት የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” በምናኔ ሕይወታቸው ፣የጠለቀ ዕውቀታቸው ፣ ዕረፍት በሌለው አገልግሎታቸውና በቤተ ክርስቲያን ወዳድነታቸው ወደር በማይገኝላቸው ሊቀጳጳስ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ስም እንዲሰየምና ብፁዕነታቸውን ታሪክ እንዲአስታውሳቸው ማድረጉ ልማት ኮሚሽኑ የተጣለበትን መንፈሳዊ አደራ በእጅጉ የተወጣ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል እንላለን፡፡

{flike}{plusone}