ቋሚ ሲኖዶሱ ለአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች ማስጠንቀቂያና ጥብቅ መመሪያ ሰጠ
ቋሚ ሲኖዶስ (ፎቶ ፋይል)
ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራው ቋሚ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎችንና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮችን አነጋገረ፡፡ ቋሚ ሲኖዶሱ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ የሚመራውን ሦስት አባላት ያሉትን የአስተዳደር ኃላፊዎችን እና የአንድነቱን አመራሮች ያነጋገረው ከርክበ ካህናት ጀምሮ በአንድነቱ መሪነት እየተከናወነ ያለውን የሰ/ትቤቶች እንቅስቃሴ በተመለከተ ሥርዓት ማስያዝ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ነው፡፡
ስብሰባው ቅዱስ ፓትርያኩ ስለ ጉዳዩ በባለቤትነት ማስረዳት የነበረበት የማደራጃ መምሪያ ኃላፊ በተደረገላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ ሊገኙ ባለመቻላቸው፤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እንዲያስያስረዱ ተጠይቀው፤ ከአንድነቱ አመራሮች ጋር አንድ ጊዜ በጽ/ቤታቸው ከግማሽ ቀን በላይ እንዲሁም ሰኔ 2 ቀን 2007 ዓ.ም. አስከትለው ከመጡት ከ800 በላይ ወጣቶች ጋር ከግማሽ ቀን በላይ የፈጀ ውይይት እንዳደረጉና በስምምነት መለያየታቸውን ገልጸው፤ የእነሱን ከመዋቅር ውጭ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በማጋነን የሚጽፉ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ግን ያለ ስምምነት እንደ ተቋጨ ገልጸዋል ብለዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ በአንድነቱ የተነሱት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸውና ወቅታዊ መሆናቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን መዋቅሩን የጠበቀ አካሄድ አለመፈለጋቸው፣ የአንድን አጥቢያ ችግር እንደ ሀገር አቀፍ ችግር አድርገው ማቅረባቸው እና የበላይ አካል የሚሰጠውን መፍትሔ ለምን እኛ እንደፈለግነው አልሆነም በሚል ብቻ ባለመቀበል ለጥያቄአችን ምላሽ አላገኘንም በሚል እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የዋና ሥራ አስኪያጁን ማብራሪያ ተከትሎ የቅዱስ ፓትርያኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ መጋቢት 27 ቀን 2007 ለርክበ ካህናት የደንብ ልብስ የለበሱ ወጣቶች በዝማሬ ሲቀርቡ የሀገረ ስብከቱም ሆነ የማደራጃ መምሪያው ፈቃድና ዕውቅና አለመኖሩን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ በቅሬታ አቅራቢዎቹ የቀረበው ወረቀት አድራሻ የሌለውና ኃላፊነት የወሰደ አካል እንደሌለው ጠቁመው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰ/ት/ቤቶችን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የወሰነው የአንድነቱ መመሪያ እንደሚያለክተው አንድነቱ ከማደራጃ መምሪያ እና ከሀገረ ስብከቱ ዋና ክፍል ኃላፊዎች ሥር እንደሆነ በግልጽ ቢያስቀምጥም ይህ እየተተገበረ አለመሆኑን በስፋት አብራርተዋል፡፡
በመቀጠል ያላቸውን ሀሳብ እንዲያስረዱ መድረኩ የተከፈተላቸው የአንድነቱ አመራሮች ያነሷቸው ነጥቦች በዋናነት የሙስና መስፋፋት፣ የመናፍቃን ተሐድሶ እንቅስቀሴን እና የአስተዳደር ችግርን በተመለከተ ሲሆን፤ የቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለእያንዳንዱ ጥያቄያቸው በቂ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ዘወትር እኛ ያልነው ብቻ ካልሆነ በማለት ግትር አቋም ይዘው የሚቀርቡት የአንድነቱ አመራሮች “ከእኛ በስተጀርባ ሃያ አምስት ሺህ ወጣቶች አሉ እነርሱን ይዘን እንወጣለን” በማለት ድፍረት በተመላበት አነጋገር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በአባትነት መንፈስ ሲመክሩ የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳትም “ወጣቱን የት ልትወስዱት ነው? ከቤተ ክርስቲያን ለመውጣት ከመዘጋጀት የበለጠ ተሐድሶነት ከየት ይምጣ፣ እናንተስ በየትኛው ጉባዔ ቤት ተምራችሁ ነው አንድን ሰው መናፍቅ ለማለት የምትደፍሩት? የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ጥሪ ውግዘት ሳይሆን ምክርና ተግሳጽ ነው፡፡ ከሲኖዶስ ውሳኔ ውጭ ምን እንዲሆን ነው የምትፈልጉት” በማለት ምሬት በተቀላቀለበት ድምጽ ተናግረዋል፡፡
በስተመጨረሻም ቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት ቃለ ምዕዳን የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራሮች በተደጋጋሚ ከመዋቅር ውጭ እየተንቀሳቀሰ ባለው ሂደት ማዘናቸውን ገልጸው፤ ከአሁን በኋላ ይህ እንዲታረም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከመጋቢት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ወጣቶችን የአገልግሎት ልብስ በማስለበስ የሚያደርገው እቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ምእመናንን ማሳዘኑ የሚታወስ ነው፡፡
{flike}{plusone}