የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ጥያቄና የሀገረ ስብከቱ ዋናሥራ አስኪያጁ በሳል አመራር!!
ማክሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2007 ዓ.ም ከጧቱ አራት ሰዓት ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ከአጥሩ ግቢና ከአጥሩ ውጭ ባለው ከሜዳ ላይ ዩኒፎርም የለበሱና በመቶወች የሚቆሩ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በሜዳው ላይ በመትመም ጭብጨባና ከበሮ የተለየው ዝማሬ ያሰማሉ፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በር ላይ እንዲህ አይነቱ የወጣቶች ዝማሬ አልፎ አልፎ የተለመደ ቢሆንም በዚህ ቀን የሚሰማው የዝማሬ ድምጽ ግን ውስጡ ቁጣ የሚንጸባርቅበት መሆኑ በጉልህ ያስታውቃል፡፡
ከአፍታ የዝማሬ ድምፅ በኋላ በፈጣኑ እና በአስተዋዩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስፈጻሚ ቡድን በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በመገኘት ከአድባራትና ገዳማት ተወክለናል ከሚሉ ቁጥራቸው ከ835 የማያንሱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ጋር ውይይቱ በይፋ ተከፈተ፡፡
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤ አመራር የሆኑ አንድ ተናጋሪ የውይይቱን አቅጣጫ ለማሳየት በሞከሩበት ወቅት በሰሚት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እናቶች እና ወጣቶች በፖሊስ ጣቢያ ታሥረዋል፣ ሰንበት ት/ቤቱ ተበትኗል ፣ የሰንበት ት/ቤቱ አዳራሽ ታሽጓል፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሙስናን የሚፀየፉ መሆናቸው ቢታወቅም ነገር ግን ሙስና እየተፈጸመ ነው፣ ቤተ ክርስቲያኑ ድሀና ሀብታምን በመለየት አገልግሎት እየሰጠ ነው፣ ሌቦች እየተበራከቱ ናቸው፣ የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የግል መኪና እና ቤት ከየት በመጣ ገንዘብ ነው የተገዛው? በሀገረ ስብከቱ ባለሥልጣናት የሚመኩ ክፍሎች አሉ ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የፖለቲካ ድርጅት ደጋፊዎች ናቸው በመባል ስማችን በከንቱ እየጠፋ ነው ፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት እየተስፋፋ ነው በማለት ሲገልፁ ቀጣዩና ሁለተኛው የአንድነቱ አመራር የሆኑት ግለሰብ ሲናገሩ የእኔ እና የደብሩ አስተዳዳሪ መብት እኩል ነው ፣ ካህናት የንስሐ አባት እንዳይሆኑን በደብዳቤ መመሪያ እየተሰጣቸው ነው፣ ከእንግዲህ ዝም አንልም እስከ ሕይወት የደረሰ ዋጋ እንከፍላለን፣ ሀገረ ስብከቱ ሙስናን ለመዋጋት የባንክ ካሽ ሪጀስተር ሥራ እንዲጀመር ማድረጉን እንደግፋለን፣ ፓትርያርኩን ይቃወማሉ የሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተደረገብን ነው ፣ ቅዱስ አባታችን እኮ የተቀደሱ አባት ናቸው ፣ እኚህን ቅዱስ አባት አናስቀይምም ፣ እሳቸውን ብናስቀይም እንቀሰፋለን ብለን እናምናለን በማለት ሲያብራሩ ቀጣዩና ሦስተኛው ተናጋሪ ደግሞ ሀገረ ስብከቱ በክብር ስለአስተናገደን ደስተኞች ነን ፣ ከእናንተ የበለጠ መሪ አያስፈልገንም ፣ ቤተ ክርስቲያን ምንም እንደማትሆን እናምናለን ፣ ነገር ግን መንገዳገድ የለባትም ፣ የሙዳዬ ምፅዋት ፣ የሕንፃ ኪራይ ፣ የሠራተኛ ቅጥር ችግሮች ይፈቱ ፣ በየአጥቢያው የሚታየው የተሐድሶ እንቅስቃሴ መፍትሔ ይሰጠው፣ ሰበካ ጉባኤ ያልተቋቋመበት ቦታ አለ ፣ በተቃራኒው ደግሞ ዕድሜልካቸውን በሰበካ ጉባኤ አባልነት የተቀመጡ ግለሰቦች አሉ ፣ ቤተ ክርስቲያን በእኛ ዘመን መዋረድ የለባትም፡፡ ከአንዱ ደብር በመናፍቅነት የተወገደ ሰው በሌላ ደብር እየተቀጠረ ነው ፣ በዘር ፣ በቀለም ፣ በቋንቋ መከፋፈል የለብንም ፣ ያሬዳዊ ዝማሬያችን እየተቀየረ ነው ፣ የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል፡፡
በመጨረሻም እሳት ለብሶ ፣ እሳት ጎርሶ የመጣውን ወጣት ወደ ልቡ እንዲመለስ ያደረጉት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ የወጣቶችን የልብ ትርታ በማዳመጥ ፣ በሰከነ እና በሰለጠነ አገላለፅ ከላይ ለተዘረዘሩት አስተያየቶች ምላሽ በሰጡበት ወቅት “ቤተ ክርስቲያናችንን የምንከተላት ትክክለኛ እና እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ ነው ፣ ከጽድቅ መንገድ ሊአወጡን የሚፈልጉትን አንቀበላቸውም ፣ የምንሠራው እግዚአብሔር የፈቀደልንን ነው ፣ ተጠያቁነት ይቀራል ማለት ውሸት ነው ፣ የሰው ዘር በአቅም የተወሰነ ነው ፣ በአንድ ጊዜ በየትኛውም ቦታ መገኘት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው ፣ እኛ ግን መገኘት የምንችለው በአንድ ቦታ ብቻ ነው ፣ ማንኛውም ተናጋሪ ብዙ ሊናገር ይችላል ፣ ተናጋሪዎቹ ሁሉ ግን ትክክለኛ ናቸው የሚል ድምዳሜ አይኖረኝም ፣ ሕገወጥ ሰዎችን አልደግፍም ፣ ረጅም የሥራ ዕድሜ የለንም ፣ ግማሹን ዕድሜ ኖረንበታል አንድ ቀን ሲርበንና ጉልበታችን ሲደክም የአቅማችንን ልክ እናውቃለን ፣ ሙስና በሰንበት ት/ቤትም አይፈቀደም ፣ የሙዳዬ ምፅዋት ገንዘብን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የንብረትን ብክነትም እንቃወማለን ፣ ንጉሥ ፈርኦን ከነሠራዊቱ በአንድ ሰጥመዋል ፣ እኛ ግን ብዙ ፈርኦኖችን በአንደ ጊዜ ማስጠም አንችልም ፣ አሠራሩን ስናስተካክለው አሁን እያጣላን ያለው የገንዘብ ችግር ይቀንስልናል ፣ ሰዎችን ሠረቃችሁ ለማለት ማስረጃ ያስፈልጋል ፣ የሙስና ቦታዎችን ለይተናቸዋል ፣ ሙዳዬ ምፅዋት ካህናትን ጥገኛ ያደረገ ሥራ ነው፡፡ ከሙዳዬ ምፅዋት ጥገኝነት ተላቀን በልማት ሥራ መሠማራት አለብን፡፡
አለመረጋጋትና ሁከት ከመጣ ግን ዋነኛውን ሥራችንን አቁመን የማረጋጋት ሥራ እንሠራለን፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በእጁ ፈጠረ ፣ ሌላውን ግን በቃሉ ፈጠረ፡፡ አሁን የእኛ ችግራችን አለመወያየት ነው፡፡ ሌባውን ብቻ ነጥለን መጥላት ይገባናል፡፡ መፍትሔ የሚመጣው በመንጫጫት ሳይሆን በመመካከር ነው፡፡ ሙስና መወገድ አለበት፤
ሀገረ ስብከታችን ቅጥር እየፈጸመ ያለው በማወዳደር ነው፡፡ የሚአወዳድረውም መምህራንን ነው፡፡ ካህናት ሙሰኞች ናቸው ብለን አናምንም፤ ካህናቶቻችን መኪና ቢኖራቸው ቪላ ቤት ቢኖራቸው ደስ ይለናል፡፡ ካህናት የሀብት ችግር አለባቸው እንጂ ታማኞች ናቸው፡፡
ሙስናን ስንዋጋ ሙስና የሆነውን ሁሉ መዋጋት አለብን ፤ ለውጡን ባናጠናቅቀውም ከጀመርነው መልካም ነው ፤ በተሐድሶ ጉዳይ በሀገረ ስብከቱ እና በእናንተ መካከል የአቋም ልዩነት የለንም፡፡
ሃይማኖታችን ርትዕት ፣ ንፅህትና ቅድስት ስለሆነች ብዙ ፈተና ይበዛባታል፡፡ እኛ የምንከተለውና የምናስፈጽመው ቤተ ክርስቲያን ያወጣችውን መመሪያ ነው፡፡ ያልተፈቀደለት ሰባኪ ሊሰብክና ሊአስተምር አይገባውም፡፡ የዚያኛው ማህበርተኛ ይስበክ የዚህኛው ማህበርተኛ አይስበክ ማለት የለብንም፡፡ የሃይማኖቱን ጉዳይ የሚአጣራ አካል አለ፡፡ ቤተ ክርስቲያን መናፍቅ ነው ብላ ያለየችውን ሰው መናፍቅ ነው ማለት አይገባንም፡፡
በሰው ሚዛን የወደቀ በእግዚአብሔር ሚዛን ሊነሣ ይችላል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ራሳችንን የተሻለ አድርገን አንውሰድ፡፡ ሌላው ማየት ያለብን አእምሮአችንን በውጥረት የተሞላ የሚአደርገውን ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ነውጥ መዋጋት አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ተጠቃሚ እንድትሆን መሥራት አለብን፡፡
ሀገረ ስብከታችን ሚዲያ አቋቁሞአል፡፡ መነሻ የሚሆን የሰው ኃይል አለን፡፡ ማቴሪያልም አለን ሌላው የያሬዳዊ ዜማ አዋቂዎችን መሰብሰብ አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀብታም ድሀ አትልም፡፡
የወጣቶቹን መታሠር በተመለከተ በአሁኑ ሰአት ሰው በፖለቲካ አስተሳሰቡ ይታሠራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን የሕግ የበላይነት እንዳለ አምናለሁ፡፡ ሰንበት ተማሪ ቢሆንም ወንጀል ከፈጸመ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን በሰላማዊ መንገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በይቅርታ የሚታለፉ ነገር መኖር አለበት በማለት እና ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጪ ማብራሪያ በመስጠት ዋና ሥራ አስኪያጁ ለተሰብሳቢ ወጣቶች ያስተላለፉት ትምህርታዊ መልእክት በሁሉም ህሊና ውስጥ ጠልቆ የገባ በመሆኑ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ የመጣው ወጣት በጋለ ጭብጨባ መመሪያውን ተቀብሎ ጉባኤው ተጠናቅቋል፡፡
በመጨረሻም የዝግጅት ክፍላችን በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሳል አመራር የተገኘውን የመግባባት ውጤት በእጅጉ እያደነቀ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችም በበኩላቸው ፣ የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች ማክበር ፤ ሆደ ሰፊ ነገር አሳላፊ እና ትዕግሥተኛ በመሆን አልግሎታቸውን ማከናወን ይገባቸዋል እንላለን፡፡
{flike}{plusone}