የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አንደኛ ደረጃ፣ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ለሦስት ዓመታት ባስመዘገበው ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም ከአስር ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑ ተገለፀ
በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን አንደኛ ደረጃ፣ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ላለፉት ሶስት ዓመታት ባስመዘገበው ከፍተኛ የሥራ አፈጻጸም ከግል ት/ቤቶች ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 1ኛ፣ከአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ ከተመረጡ አስር ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑ ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ/ም በደብሩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ የሀ/ስብከቱ የሰው ኃይል አስተዳደር ዋና ክፍል ኃላፊ ሊቀ ስዩማን ወልደ ሰንበት አለነ፣የደብሩ አስተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ዘርዓ ዳዊትና የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ስዩማን ኪዳነ ማርያም በተገኙበት የትምሀርት ቤቱ ማኅበረሰብ፣ተማሪዎች፣ወላጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን በመርሐ ግበሩ መሠረት አሁን የያዝነውን የትምህርትቤቱን የለውጥ ሂደት በበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል በዚህ ቦታ ሕፃናትንና ወጣቶችን ማስተማር ማለት ለሥጋዊ ትርፍ ብቻ ሳይሆን የዘለዓለም ሕይወት ማግኘት መንገድ ጭምር መሆኑን በዕለቱ የቀረበው የክንውን ሪፖርት ያመለክታል፡፡
የደብሩ ሰበካ ጉባኤና የት/ቤቱ ቦርድ ተማሪው ባስገኘው ውጤት የተሰማውን ደስታ በመግለጽ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ የሁለት ዓመት ሁለት ተርም ክፍያ በነጻ እንዲማር በደብሩ ሰበካ ጉባኤና በትምህርት ቤቱ ቦርድ እስፖንሰር የተደረገ መሆኑን የቀረበው ሪፖርት አክሎ አብራርቷል፡፡
በመጨረሻም የእለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራአስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የእንኳን ደስ ያላችሁ መርሐ ግብርን አስመልክተው ባስተላለፉ መልእክት እናንተ መምህራን በዚህ ስኬታማ በሆናችሁበት ጉዳይ እንኳን ደስ አላችሁ፡፡
ማስተማር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያ ባህላዊ ሥራዋ ነው፣ አዲስ የምንጀምረው አይደለም፡፡
በቀደመው ዘመን ቤተክርስቲያን የትምህርት ሚንስትር ነበረች፡፡
ቤተክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ ያሉ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ናቸው፡፡
ስለዚህ በቅዱስ ራጉኤል የተጀመረው ጥረት ሊቀጥል ይገባዋል ሀ/ስብከቱም አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል፣ በማለት ሥራ አስኪያጁ ሰፋ አድርገው መልእክታቸውን ካስተላለፉ በኋላ የእለቱ መርሐ ግብር በደብሩ አስተዳዳሪ በሊቀ ሊቃውንት አባ ዘርዓ ዳዊት ጸሎትና ቡራኬ እነደተጠናቀቀ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አሲኪያጅ በተገኙበት ነባር ትምህርት ቤቱና አዲስ ተጨማሪ እየተገነባ ያለው ትምህርት ቤት ተጎብኝቷል፡፡
{flike}{plusone}