በአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቁጥራቸው ከስድስት መቶ ካላነሱ የሃይማኖት ተወካዮች ጋር የአንድ ቀን የጋራ ውይይት አካሄዱ
በአዲስ አበባ ከተማ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባኤ ወጣቶች ለሰላም ያላቸውን ሚና እና የሽብር ቡድኖችን እኩይ ተግባር አስመልክቶ ቁጥራቸው ስድስት መቶ ለሚደርስ ከሃይማኖቶች ተወካዮች ጋር ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም ሜክሲኮ በሚገኘው የተግባረ ዕድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የቆየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሄዷል፡፡
ጉባኤው የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ በሆኑት በሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የተመራ ሲሆን የሃይማኖት ተቋማትን ህብረት ሊአበሥር የሚችል የእጅ ለእጅ መጨባበጥና የጋራ የጸሎት መርሐ ግብር ተፈጽሟል፡፡
በሊብያ ባህር ዳር ለተሰውት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
በማያያዝም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጉባኤውን አስመልክተው ባስተላለፉት የመክፈቻ ንግግር፡-
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊ የሀገራችን የሃይማኖት ተቋም ስትሆን ሌሎች ሃይማኖቶችን በማስተናገድና ሰላማዊ አኗኗርን ለተከታዮቹ በማስተማር በሀገራችን ሰፍኖ ለሚገኘው ብርቅዬ ተሳስቦ የመኖርና ከመቻቻል የሚለቅ ውህደት የበኩሏን አበርክታለች፡፡ አሁንም በበርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሁና ሰላምን ማስተማርዋን ትቀጥላለች፡፡
በአንድ ወቅት በቆጵሮስ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የሰላም ጉባኤ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እንደተናገሩት ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በጦርነት መገዳደል የለባቸውም፡፡ በሃይማኖተኞች ያልመጣ ሰላም በማን ሊመጣ ይችላል?
ይህ የሰላም እሴት ግንባታ ጉባኤ በሰባቱም ቤተ እምነቶች ተከታዮች የሚካሄድ በመሆኑና ሁሉም የሀገራችን ሃይማኖቶች ሠላም ሠማያዊ ዋጋ የሚያስገኝ ተግባር ነው ብለው የሚያምኑ በመሆናቸው የጋራ የሆነውን እሴት ለማጎልበትና የጋራ እሴቶቻቸውን ለማበልጸግ የሚያግዝ ነው፡፡
የርስበርስ ትውውቅን በማጠናከር መልካም ስሜት የሚፈጥርና የመተሳሰብ ባህላችንን ቀጣይ ለማድረግ የሚያግዝ ነው፡፡
የመድረኩን ፋይዳ በውል ስለሚገነዘቡ ተሳታፊዎች በንቃት በመሳተፍ ዕርስ በርስ ትውውቅና የጋራ እሴቶቻቸውን መረዳት ይጠቀሙበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተለይም ቤተ እምነቶቻችን በተለያዩ ውጫዊ ጫናዎች ምክንያት እሴቶቻቸውን ላለማጣት ከፍተኛ ጥረት በሚያደርጉበት በአሁኑ ወቅት ይህ መድረክ መዘጋጀቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጣቸዋል የበለጠ ክብደት ሰጥተውት ይጠቀሙበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀገረ ስብከታችን ሌሎች መድረኮች በተናጠልም በጋራም እንዲዘጋጁ በማድረግ የሰላም እሴት ግንባታ ጥረቱ እንዲሳካ የበለጠ ይሠራል፡፡
ይህ መድረክ እንዲዘጋጅ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስላደረጉት ጥረት ላመሠግናቸው እወዳለሁ፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ለጉባኤው ስኬት ያደረገው ጥረት አርአያነት ያለው በመሆኑ ከፍ ያለ ምስጋናዬን በራሴና በሀገረ ስብከታችን ጽ/ቤት ስም አቀርባለሁ፡፡
መልካም የውይይትና የመማማሪያ መድረክ እንዲሆን ምኞቴን በድጋሚ እገልጻለሁ ፤ አመሠግናለሁ፡፡ በማለት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡
{flike}{plusone}