የ2007 ዓ.ም.የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጀመረ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱ-ስ አሐዱ አምላክ አሜን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
ምሕረትና ይቅርታ፣ ትዕግሥትና ቸርነት የባህርዩ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ፣ ሰፊውን የወርኃ ጾም አገልግሎት በሰላም አስፈጽሞ ብርሃነ ትንሣኤውን በሰላም ስለአሳየን፣ እንደዚሁም ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ዓመታዊ ከሆነ ከዚህ የረክበ ካህናት ጉባኤ በሰላም ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ እናቀርባለን፡፡
‹‹ኀበ ሀለዉ ክልኤቱ ወሠለስቱ ጉቡአን በስምየ አነ እሄሉ ማእከሌሆሙ ህየ፤ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁ›› (ማቴ፡ 18÷20)፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የጌታችን፣ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ቃል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ጀማሪና ፈጻሚ ራሱ ጌታችን ቢሆንም ሥራው በአጠቃላይ በሰው ልጅ ድኅነት ላይ የሚከናወን ፍጹምና ምሉእ ተልእኮ በመሆኑ በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያልቅ አይደለም ፡፡
በመሆኑም ተልእኮው እስከ ዓለም መጨረሻ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ እንዲዳረስ፣ እርሱን ተከትለው የድኅነት አገልግሎት የሚሰጡ ሐዋርያት እንደሚያስፈልጉ ግልጽ ነበረ ፡፡
ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የቅብብሎሽ ሥራ በመሆኑ እነሆ አባቶች ሲያልፉ በልጆች እየተተኩ ሥራው እኛ ዘንድ ደርሶአል፤ በዚህም ‹‹ወናሁ አነ እሄሉ ምስሌክሙ እስከ ኅልቀተ ዓለም፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› (ማቴ፡ 28÷20) ብሎ የገባልን ቃል ኪዳን በተግባር እየተፈጸመልን አገልግሎታችን ከሀገር ውስጥ አልፎ መላውን ዓለም ባካለለ መልኩ እያካሄድን እንገኛለን፤ በዚህም እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም የዓለም ክልል ፈላጊዋ እየበረከተ መምጣቱ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያናችን አማካኝነት ሊሠራ ያሰበው ሥራ እንዳለ የሚያመለክት ነው፤ ይህ ዕድል ለቤተ ክርስቲያናችን በጣም ትልቅ ስኬት የሚያስከትል በመሆኑ በሚገባ ልንሠራበትና ልንጠቀምበት ይገባል ፡፡
በመሆኑም በውጭ ሀገራት የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና አገልጋይ ካህናት እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናን ከመጠበቅ ጋር በሙሉ ኃላፊነት፣ በአንድነትና በኅብረት ሆነው በውጭ ሀገር ያለው የቤተ ክርስቲያናችንን ተልእኮ በማስፋፋትና በማጠናከር ረገድ አብዝተው እንዲሠሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቅብናል ፡፡
ከሀገር ውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እየበረከቱ መምጣታቸው በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያናችን መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ በአጠቃላይ በኦርቶዶክሱ ዓለም የሌለ ገለልተኛ ነን የሚል ስም በመጠቀም ከእናት ቤተ ክርስቲያን መኮብለል ሊታረም የሚገባ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ካየነው ‹‹በሊቀ ጳጳስ ሥር ሆና የማትመራ ቤተ ክርስቲያን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናት ለማለት ያስቸግራል ፡፡
በመሆኑም ያለጥንቃቄም እንበለው ያለ ማወቅ በፈጠረው መነሾ የተጀመረው ስሕተት ጊዜ ሊሰጠው ስለማይገባ በዚህ ዙሪያ እንደካሁን ቀደሙ ጠንክረን በማስተማርና በማስረዳት ወደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ጉያ ማሰባሰብ ይገባናል፤
ምእመናንም ይህንን ጊዜያዊ ስሕተት ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ተባባሪ እንዲሆኑ በዚህ አጋጣሚ ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከሰበካ ጉባኤ መቋቋም በኋላ ያሳየችው እመርታ በተለይም በትላልቅ ከተሞች እየታየ ያለው
•በኢኮኖሚ የመለወጥ ሁናቴ፣
•የትምህርት ቤቶች በብዛት መገንባት፣
•የጤና ተቅዋማትና የምግባረ ሠናይ ድርጅቶችን ማቋቋም እየተለመደ መምጣት
•ወጣቶች በየሰንበት ት/ቤቱ ስለሃይማኖታቸው በቂ ዕውቀት መቅሰማቸው፣
•የስብከተ ወንጌል ሥራ እየሰፋና እየተወደደ መምጣቱ እጅግ ተስፋ ሰጭ ሆኖ ይገኛል ፡፡
እነዚህ ተስፋ ሰጭ ተግባራት ያላቸውን ክፍተት በመሙላትና በማስተካከል ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ብልሐት ከሠራንባቸው የዕጥፍ ዕጥፍ ዕድገትን ማምጣት እንደምንችል ሁኔታዎች ያሳያሉ፤
ስለሆነም ለበለጠ ዕድገት የተሻለ አሠራርና የጋራ ተነሣሽነትን አንግበን በመሥራት ዕድገታችንን በፍጥነት እውን ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀን ኃላፊነት ነው ፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ሁላችንም እንደምናውቀው ጥንካሬና ድክመት ምን ጊዜም ቢሆን የማይለያዩ አንጻራዊ ነገሮች ናቸውና በቤተ ክርስቲያናችን አሠራር ውስጥም ጥንካሬ እንዳለ ሁሉ ድክመትም እንደማይጠፋ ሳይታለም የተፈታ ነው ፡፡
በተለይም ካለፉት ዘመናት ጀምሮ እየተከሠተ ያለው የምእመናን ፍልሰት ወይም የበጎች መነጠቅና መኮብለል በመጀመሪያ ሊቀመጥ የሚገባ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ይታያል ፡፡
ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ከባድ ጥያቄ ሊያስነሣ የሚችል ጉዳይ መሆኑን ሁላችንም መገንዘብ አለብን፤ ስለሆነም ይህንን ችግር በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል ጊዜ ሳይወስድ ይህ ቅዱስ ጉባኤ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል ፡፡
ሌላው በቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች እየተስተዋለ ያለው ችግር በስደትና በዝርወት የሚከሠት የሰብአዊ መብት ጥሰትና የሃይማኖት ነጻነት እጦት፣ አልፎ ተርፎም ሕይወትን ማጣት ነው፤
ቤተ ክርቲያናችን በነዚህ ምክንያቶች የምታጣቸው ልጆች ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም፤ ልጆቻችን ለእንጀራ ፍለጋ ሲባል ወደ ባዕድ ሀገር ሲሄዱ ስመ ክርስትና ከመለወጥ ጀምሮ ሃይማኖት እስከመለወጥ የሚደርስ ተፅዕኖ ሁሉ እየገጠማቸው ብዙዎችን እያጣን ነው፤
ከዚህም ጋር በቅርቡ በሊቢያ እንደተከሠተው ያለ አረመኔያዊ ተግባር ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ እየተፈጸመባቸው ነው ፡፡
የዚህ ሁሉ ማባባሻ ሆኖ የሚገኘው ሀገራችን ከድህነት ወጥታ በኢኮኖሚ ሌሎች ሀገሮች ከደረሱበት ደረጃ ባለመድረሷ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ምክንያቱም በሌላ ሀገር የሚገኘው ጥቅም በሀገር ውስጥ ቢገኝ ኖሮ ልጆቻችን ለስደት አይዳረጉም ነበር፤ ካልተሰደዱም ከላይ የተገለፀው ግፍና በደል በልጆቻችንና በቤተ ክርስቲያናችን አይደርስም ነበርና ነው፡፡
ስለሆነም አሁን በሀገራችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በአሸባሪዎች እየተፈጸመብን ያለው ተግዳሮት በወሳኝ መልኩ ለመመከት በሀገራችን ያለውን የልማትና የዕድገት መርሐ ግብር ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ በማፋጠን ድህነትን ታሪክ ማድረግ ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ ሊሆን ይገባል ፡፡
ሆኖም ለብዙ ዘመናት ሥር ሰዶ የቆየው ድህነት በአንድ ጀምበር ይጠፋል ተብሎ ስለማይገመት ‹‹ከመሞት መሰንበት›› የሚለውን አባባል በመከተልና አሁን ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወጣት ልጆቻችን በሀገራቸው ሠርተው እንዲያድጉ ቤተ ክርስቲያናችን ያለማቋረጥ አዘውትራ ማስተማርና መምከር ይገባታል፤ እየመከረችም ትገኛለች ፡፡
በመጨረሻም፤
ይህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሚቀርቡ አጀንዳዎች መሠረት ለሰላም፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በመፈተሸና በመመርመር ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በመወሰን ጉባኤውን እንዲያካሂድ በማሳሰብ የ2007 ዓ.ም. የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ዛሬ መከፈቱን እናበሥራለን ፡፡
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ፣ ይቀድስ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.
{flike}{plusone}