ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ
ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡
– በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
– ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
– የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
– በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
– እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
በሞትና በመቃብር ላይ ሥልጣን ያለው ኃያሉና አሸናፊው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ ፡፡
‹‹ወበከመ በእንተ አዳም ኵልነ ንመውት ከማሁ በክርስቶስ ኵልነ ነሐዩ፤ ሁላችን በአዳም እንደምንሞት እንደዚሁም ሁላችን በክርስቶስ ሕያዋን እንሆናለን›› (1ቆሮ. 15÷22)፡፡
እዚህ ላይ በተገለፀው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት የሰዎች መጻኢና የመጨረሻ ዕድል ከሁለት አዳማዊ ውርስ ጋር የተያያዘ ሆኖ ይገኛል ፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ በግልጽ እንደተጻፈው ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ተወልዶአል፤ የእርሱ የሆነውንም ሁሉ ወርሶአል፤ይህም ማለት በሥጋው በኩል የግብረ ኃጢአት ዝንባሌን፣ ሞተ ሥጋን፣ ወሪደ መቃብርን፣ በመቃብር ውስጥ መበስበስንና መፍረስን ሲወርስ በነፍሱ በኩል ደግሞ ከእግዚአብሔር መለየትን፣ በኃጢአት ተሸንፎ የዲያብሎስ ሎሌ መሆንን፣ በኃጢአቱ ምክንያት ለኵነኔ ሲኦል ተጋላጭ መሆንን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ወርሶአል ማለት ነው፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው ቀዳማዊ አዳም በሥጋና በነፍስ ከባድ ውድቀትን ለልጆቹ አውርሶአል ማለት ነው ፡፡
ከቀዳማዊ አዳም የውድቀት ዘመን ጀምሮ
እስከ ስቅለተ ክርስቶስ በነበረው ረጅም ዘመን የሰው ዘር በአጠቃላይ ከቀዳማዊ አዳም ባገኘው ውርስ ምክንያት በሥጋው ርደተ መቃብርን፣ በነፍሱ ርደተ ሲኦልን ተፈርዶበት በድርብ መከራ ሲማቅቅ ኖሮአል ፡፡
ያ ዘመን ከመከራው ብዛት የተነሣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ፣ ዓመተ መርገም ተብሎ ተሰይሞአል ፡፡
ይሁን እንጂ ለምሕረቱና ለይቅርታው ወሰን የሌለው እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ውድቀት በትንሣኤ ለመቀልበስ ሲል የባህርይ ልጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከ፡፡
እርሱም የኛን ሥጋ ተዋሕዶ ሰው ሆነ፤ በመካከላችን ተገኝቶም ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመቃብር ወደ ትንሣኤ የሚወስደውን መንገድ በቅዱስ ወንጌሉ አስተማረን ፤ (ዮሐ.5÷24)
የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ የአብ ልጅ ቢሆንም በሥጋው የሰው ልጅ ነውና ዳግማዊ አዳም ተብሎ ይጠራል (1ቆሮ15÷45 – 48)፡፡
በመሆኑም ዳግማዊ አዳም የተባለው ጌታችን፣ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በበኩሉ ቀዳማዊ አዳም ለልጆቹ ላወረሰው ውርስ ተቃራኒ የሆነውን ለሰው ዘር ሁሉ አውርሶአል፤ ይኸውም፡-
– በኃጢአት ዝንባሌ ፈንታ ጽድቀ መንፈስን፣
– በሞት ፈንታ ዘላለማዊ ሕይወትን፣
– በርደተ መቃብር ፈንታ ትንሣኤን፤
– በርደተ ሲኦል ፈንታ ዕርገትን፣
– በመለያየት ፈንታ ከእግዚአብሔር ጋር በአንድነት መኖርንና የመሳሰሉትን ለልጆቹ አውርሶአል፡፡
ይህ ሁሉ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ለሰው ልጅ በመሰጠቱ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ያለው ዘመን ዓመተ ሥጋዌ፣ መዋዕለ ንሥሐ፣ ዓመተ ምሕረት ተብሎ ይጠራል፡፡ ይሁንና ሰው ሁሉ ከቀዳማዊ አዳም በሥጋ ዘር በመወለዱ የእርሱ የሆነውን ሁሉ እንደወረሰ፣ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ የዳግማዊ አዳም የሆነውን ሁሉ ለመውረስ ከዳግማዊ አዳም በመንፈስ መወለድ የግድ ያስፈልገዋል፡፡
ሰው በእምነት ተፀንሶ በጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድ የዳግማዊ አዳም ልጅ ይሆንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይወርሳል፤ ከዚህ ዳግም ልደት በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የቀዳማዊ አዳም ውርስ አይነካቸውም (ሮሜ.8÷1 )፡፡የዳግማዊ አዳም ውርስ በዳግም ምጽአተ ክርስቶስ እውን ለማድረግ ቀጠሮ ተይዞለታል፤ ያን ጊዜ በመቃብር ያሉ ሙታን ሁሉ በቅፅበት ሲነሡና በሕይወት ያሉትም በአንድ ጊዜ በቅፅበት ሲለወጡ የዳግማዊ አዳም ውርስ በግልጽ ይታያል ፡፡በዚህ ጊዜ የሚሞተውና የሚበሰብሰው አካላችን የማይሞተውንና የማይበሰብሰውን ሲጎናፀፍ ሞትና መቃብር ይሸነፋሉ፤ ህልውናቸውም ያከትማል፡፡ /1ቆሮ. 15÷52-57)
በዚያን ጊዜ ከቀዳማዊ አዳም በመጣ የኃጢአት ውርስ ምክንያት የሞቱ ሁሉ ከዳግማዊ አዳም በተገኘ የጽድቅ ውርስ ምክንያት ሕያዋን ሆነው ይነሣሉ /1ቆሮ.15÷49)
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል አድርጎ የተነሣበትን በዓለ ፋሲካ ዛሬ በታላቅ ድምቀትና በደስታ ማክበራችን ‹‹ሞቴንና ትንሣኤዬን አስቡ›› (1ቆሮ.11÷26) ያለውን ቃሉን ከመፈጸም ባሻገር የኛንም ትንሣኤ በእርሱ ትንሣኤ እያየን በሃይማኖትና በማይናወጽ ተስፋ ፀንተን እንድንኖር ለማድረግ ነው፡፡
በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤዛነቱ ካቀዳጀን ጸጋ አንዱና ዋነኛው እኛን ለትንሣኤና ለዘላለማዊ ሕይወት ማብቃቱ ነው፡፡
ከጌታችን ትንሣኤ የምንገነዘበው ዓቢይ ነገር እርሱ በመቃብር ውስጥ ሙስና መቃብር ማለትም መበስበስና መፍረስ ሳይነካው ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ወደሰማያዊ ክብሩ እንዳረገ፣ እኛም ከእርሱ በወረስነው የጽድቅ ውርስ መሠረት እንደእርሱ ከመቃብር ተነሥተንና የዘላለምን ሕይወት ተቀዳጅተን ወደሰማያዊ መንግሥቱ የምናርግ መሆናችንን ነው፡፡
የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ማሳያ መስተዋትና የዘላለማዊው ሕይወታችን ማረጋገጫ ነውና (1ተሰ.4÷13 – 18)፡፡ ይሁን እንጂ የትንሣኤያችን ጉዞ የሚጀምረው ዛሬ በሕይወተ ሥጋ እያለን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡ ገበሬ በመኸር ወራት ጥሩ ምርትን ለማፈስ ልፋቱን በግንቦትና በሰኔ እንደሚጀምር፣ ያን ካላደረገ ደግሞ የሚያገኘው ምርት እንደማይኖር ሁሉ፣ እኛም የትንሣኤያችን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ጉዞ ዛሬ በዚህ ዓለም ሳለን ካልጀመርነው በዳግም ምጽአት የምናገኘው ነገር አይኖርም (ማቴ 25÷ 1 – 13)፡፡
ሁላችንም እንደምንገነዘበው አምላካችን እግዚአብሔር ሠርቶ የሚያሠራ አምላክ እንጂ መክሊቱን ቀብሮ በስንፍና የሚኖረውን የሚወድ አምላክ አይደለም፤(ማቴ.25÷24 – 30)
አምላካችን ከባህርይ አምላክነት በስተቀር ሁሉን በሁሉ የሚያሳትፍ አምላክ እንደሆነ ምን ጊዜም አንርሳ፤ ቅዱስ ተብሎ ቅዱሳን እንድንባል፣ ጻድቅ ተብሎ ጻድቃን እንድንባል፣ ክቡር ሆኖ ክቡራን እንድንሆን፣ ሕያው ሆኖ ሕያዋን እንድንሆን ፈቅዶልናል (1ጴጥ. 1÷16)፡፡
በመሆኑም እርሱ የመልካም ሥራ ሁሉ ባለቤት እንደሆነ እኛም የመልካም ሥራ ባለቤቶች በመሆን ትንሣኤያችንን ከዚህ እንድንጀምር ተሳትፎውን ማለትም እርሱን መምሰልን ከእኛ ይፈልጋል፡፡ /ማቴ. 5÷48)
ዛሬ ዓለማችን በፀጥታ እጦት እየታመሰች የምትገኘው ከሥነ ምግባር ጉድለት የተነሣ እንደሆነ ሁሉም ሊያውቀውና ሊገነዘበው ይገባል ፡፡
በልዩ ልዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሚገኙ የትምህርት ተቅዋማት የሥነ ምግባር ትምህርትን እያስተማሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዓለማችን በመልካም ሥነ ምግባር ከመበልፀግ ይልቅ በዘቀጠና ለአእምሮ በሚዘገንን ነውረ ኃጢአት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች ፡፡ ይህ ሁሉ የሥነ ምግባር ውድቀት ሊመጣ የቻለው በየትምህርት ቤቱ የሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት በፈሪሀ እግዚአብሔር ያልተቃኘ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል (መዝ. 110÷10፤ 1ቆሮ 1÷20 – 21)፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ኢትዮጵያ ሀገራችን በእግዚአብሔር ፊት ልዩ ተቀባይነት ያላት ሀገር እንደሆነች ቅዱስ መጽሐፍ ሊመሰክርላት የቻለው በተቀደሰው ባህሏና በመልካም ሥነ ምግባሯ፣ በጸናው ሃይማኖቷና በእውነተኛው ትውፊቷ እንጂ በሌላ በምንም እንዳልሆነ በአጽንኦት መገንዘብ ያሻል፡፡ (መዝ. 71፡9፤ 67፡31)
በሀገራችን ከምናስታውሰው ነባሩና ሃይማኖታዊ ባህላችን አንዱ ለብቻ መመገብ እንደነውር የሚወሰድ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መልካም ሥነ ምግባራችንና ቅዱስ ባህላችን ዛሬም ተጠብቆ እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ፡፡
የትንሣኤያችንን ጉዞ ዛሬ እንጀምር ስንል የተራበውን ማጉረስ፣ የተጠማውን ማጠጣት፣ የታረዘውን ማልበስ፣ ያዘነውን ማጽናናት፣ የታመመውን መጠየቅና መርዳት፣ ስደተኛውን ማስተናገድ፣ የታሠረውን መጠየቅ፣ የሥራ ጊዜን በአልባሌ ቦታ አለማጥፋት፣ ለሰላም፣ ለሀገር ልማትና ለዕድገት በአንድነት መሰለፍ፣ ሁሉንም ነገር በፍቅርና በስምምነት ብቻ መፍታት የመሳሰሉትን ሁሉ የሕይወታችን መርሆዎች አድርገን በተግባር እናውላቸው ማለታችን ነው፤ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እውነትም የትንሣኤን ጉዞ በትክክል ጀምረናል ማለት ነው ፡፡
በመጨረሻም
ሁላችሁም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን በተቀደሰው እምነት ጸንታችሁ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን መሠረት ያደረገ ሥነ ምግባር አንግባችሁ፣ የሀገራችንን ሰላም በጽኑ እንድትጠብቁ፣ ልማቷንና ዕድገቷን እንድታፋጥኑ፣ አንድነታችሁንና እኩልነታችሁን አጥብቃችሁ እንድትይዙ፣ በዓለ ፋሲካውንም የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስና የተጠሙትን በማጠጣት፣ በሰላምና በፍቅር እንድታከብሩ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
{flike}{plusone}