የአ/አ/ሀ/ስ/ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈ ስቅዱስ ከሀገረ ስብከቱና ከክፍለ ከተማ ሠራተኞች ጋር በጋራ ሥራ ለመሥራት በሚያስችል ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄዱ
በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ መጋቢት 16/2007 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱና እንዲሁም በገዳማትና አድባራት ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች እጅግ በጣም ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈ ስቅዱስ ከ2 ቀናት በኋላ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና ከ7ቱም ክፍላተ ከተማ መላው ሠራተኞች ጋር መጋቢት 18/2007 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ የስብሰባው አጀንዳዎቹም፡-
1.ሥራ በጋራ ለመሥራት በሚያስችል ሁኔታ ለመነጋገር፣
2.ስለ ፐርሰንት አሰባሰብ ጉዳይ በተመለከተ ሲሆን በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት መጋቤ ብሉይም በተጠቀሱት አጀንዳዎች ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እንደገለጹት ቤተ ክርስቲያኒቷ አስተምራ ለዚህ ደረጃ አድርሳኛለች፣በቤተ ክርስቲያኒቷ ስምም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ ችያለሁ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ እጅግ በጣም እኮራለሁ ስለሆነም ያስተማረችኝን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገልና ለመሥራት እንዲሁም መልካም አስተዳደር ለማስፍን ፅኑ ፍላጎት አለኝ ይሁንና ግን የእኔ ቁርጠኝነት ብቻ በቂ ሊሆን ስላማይችል የእናንተም ቁርጠኝነት ያሰፈልጋል፤ በቤተ ክርስቲያን ሳገለግል የቆየሁ እንደ መሆኔ መጠን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያለውን ችግር አውቀዋለሁ ብለዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የወቅቱን የሥራ ኃላፊዎች ዝውውርን ተገን በማድረግ ቅጥርና የሥራ ዝውውር ተካሂዷል የሚል ጥቆማ ለሀገረ ስብከቱ እያደረሰ መሆኑን ጠቁመው የሚመለከታቸው የሀገረ ስብከቱና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎች ጉዳዩን እንዲያብራሩ እድሉን ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠልም ይህ ዓይነት አሠራር ህገ ወጥ ሥራ በመሆኑ ከወዲሁ ሊቆምና ሊታረም ይገባዋል፤ የወረዳ ኃላፊዎችም ከወዲሁ ጥብቅ መመሪያ ልትሰጧቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ስላለፉ ጊዜያት ብዙ የምለው ነገር የለኝም ነገር ግን ካለፈው ጊዜ ብዙ መማር እንችላለን ፡፡በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የነበረውን ቅጥር፣እድገትና ዝውውር ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ አይቀጥልም፤ ሀገረ ስብከቱ ለቅጥር፣እድገትና ዝውውር የተቋቋመ ተቋም አስኪመስል መሆን የለበትም ይልቁንም በአጥቢያ ያለችውን ቤተክርስቲያን አቅም ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ የተለያዩ የልማት ተቅዋማትን በመገንባት የሥራ እድል መፍጠር አለብን ያኔ ለሰዎች ብለን ሳይሆን ራሱ ሥራው ሰው ያስፈልገዋል ቅጥርና እድገቱም ሥርአቱን ጠብቆ ይከናወናል ማለትም ገዳማትና አድባራት የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ ሳያሳውቁ ቅጥር በህጉና በሥርዓቱ መሠረት ተወዳዳሪዎች መስፈርቱን አሟልተው ሲገኙ በውድድር ይከናወናል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ አሁን ስላለው ሁኔታ ሲገልፁ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ሆነ ሀገረ ስብከቱ በሚያስተዳድራቸው ገዳማትና አድባራት የኢኮኖሚ ጥገኝነትና የአስተሳሰብ ድህነት ያመጣው ችግር መኖሩን ገልጸው ይህ ድህነት የወለደውን ችግር ልናስተካክለውና መስመር ልናስይዘው ይገባል ካሉ በኋላ በተለይም የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት ሊያዝኑብን አይገባም ካህናት ከእናት ቤተክርስቲያናቸው ውጭ ሌላ ቦታ ተቀጥረው ሊያገለግሉ አይችሉም ምክንያቱም የተማሩት ትምህርት በቤተክርስቲያን ብቻ የሚፈለግ ስለሆነ ነው ነገር ግን እንደ እኔና እንደ እናንተ የመሰልን ሰዎች በተለያዩ አለማዊ ድርጅቶች ተቀጥረን ሥራ ልንሰራ እንችላለን ስለሆነም ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ ካህናትና ሊቃውንት ልዩ ክብርና ቦታ ልሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በሀገረ ስብከቱ ጊዜው የሚጠይቀውን አሠራር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን እና የሥልጣን ክፍፍል ከነተጠያቂነቱ ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሰጥ የገለፁ ሲሆን ወቅቱን ጠብቆ ስብሰባና ግምገማ እንደሚኖርም አሳውቀዋል፡፡ ሰዎች ስራ ሲበድሉ ባሉበት ቦታ ለሌሎችም አስተማሪ በሆነ መልኩ እርምት ሊኖር እንደሚችልም ጭምር ለተሰብሳቢዎች ገልፀዋል፡፡
በጋራ ለመሥራት በሚያስችል ሁኔታ ስላላቸው ቁርጥ የሥራ ተነሳሽነት ከገለፁ በኋላ በ2ኛ አጀንዳ ለተያዘለት ስለፐርሰንት ጉዳይ ማብራሪያና መመሪያ የሰጡ ሲሆን የሀገረ ስብከቱ የሒሳብና በጀት መምሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነን ስላለው ሁኔታ እንዲያብራሩ የጋበዙ ሲሆን ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ሲያብራሩ እንደገለፁትም ከ100ሚሊየን ብር በላይ ያልተከፈለ የፐርሰንት ውዝፍ እዳ መኖሩንና ይህን በተመለከተም ለሚመለከታቸው አካላት በጽሑፍ ሪፖርት ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም የስብሰባው ተሳታፊዎች የተለያዩ ገንቢ የሆኑ ሐሳባዎችን ሰጡ ሲሆን በተለይም የሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በሀገረ ስብከቱ በዋና ሥራ አስኪያጅነት መመደባቸው ከመቼውም በላይ መደሰታቸውን ገልጸው በሥራም እንዲሚያግዟቸው እና እንደሚታዘዛቸው ቃል ገብተውላቸዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ክቡር ዋና ስራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ለተነሱ ገንቢ ሐሳቦችና አስተያየቶች የማጠቃለያ ሐሳብ በመስጠት የዕለቱን የስብሰባው መርሃ ግብር ተጠናቋል፡፡
{flike}{plusone}