በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙ የአድባራትና ገዳማት የሰንበት ትምህርት ቤቶች የሥራ አመራር አባላት የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ የሥራ መመሪያ ትምህርት ተሰጣቸው

0219

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ባሉ አድባራትና ገዳማት ለሚገኙ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ረዳት፣የከንባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት እሁድ የካቲት 8 ቀን 2007 ዓ.ም የሥራ መመሪያ ትምህርት ተሰጥቶአቸዋል፡፡

በጉባኤው ወቅት የተገኙት ወጣቶች ብዛት ከ500 በላይ የሚገመት ሲሆን ብፁዕነታቸው ጉባኤውን በጸሎት በከፈቱበት ወቅት ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ልትሆኑ ይገባል፡፡ የቤተክርስቲያን ባለጋራ ሰይጣን ነው፡፡ በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ እንደተባለው ምርመራ ከመምህራን፣ከመጻሕፍትና ከህሊና ይገኛል፡፡ባህርያችን ከእሳት፣ከነፋስ፣ ከውሃና ከመሬት ነውና እነዚህ ባህርያት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ ሁሉም የየራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ ሕዋሳቶቻችን አዛዥ አላቸው፡፡ ይህም አሠራር መዋቅራዊ አሠራር ነው፡፡

በጥበብ መበልፀግ ያስፈልጋል፡፡በጥበብ የበለፀጉ ሰዎች ትህትና እና ትዕግስት ይታይባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ፍሬ የተሸከሙ ዛላዎች ጎንበስ ብለው ይኖራሉ ራስን ለበጎ ነገር ማዘጋጀት እንደሚገባ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለወጣቱ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት እንረዳለን ዘመኑ የሥራ ዘመን እንጂ የእንቅልፍ ዘመን አይደለም፡፡ እንቅልፍ ታበዢ ከነበር ትፋዘዢ እንደሚባለው ነቅተን መሥራት አለብን፡፡ ድህነት ቆሻሻ ልብስ ያስለብሳል፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች የሚሆን የመዝሙር መጽሐፍ አዘጋጅተናል መጽሐፉ ድምፅ ያስፈልገዋል ስለተባለ ወደ ድምጽ ለመቀየር እቅድ ይዘናል በማለት ብፁዕነታቸው የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ዋና ክፍል ኃላፊ መምህር ደምስ አየለ “የወጣትነት ሕይወትን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መቀደስ(መለየት)” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

d0003
መ/ር ደምስ አየለ በአ/አ/ሀ/ስ/የሰ/ት/ት/ማ/ዋና ክፍል ኃላፊ

በማያያዝም ተሰብሳቢዎቹ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡በስብከተ ወንጌልና በአስተዳደር፣በሰንበት ት/ቤቶችና በአስተዳደር ዙሪያ የማጋጨት ሥራ የሚሠሩ ክፍሎች አሉ እንደዚሁም ወጣቶችን ከምዕመናን ጋር ለማጋጨትና ለማከፋፈል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሄ ቢሰጠው? ካህናቱ በአውደ ምህረት ሰንበት ት/ቤቶችን እየዘለፉ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሰንበት ት/ቤቶችን የማዳከም ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡ በሰበካ ጉባኤ የተመረጡ ተወካዮች በደብዳቤ እየታገዱ ናቸው በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙ መናፍቅን በአውደ ምህረት እየሰበኩ ነው፡፡ በሰንበት ት/ቤቶች ይልቅ ለማህበራት ማህተም ሲቀረፅላቸው ለሰንበት ት/ቤቶች ግን ማህተም አይቀረፅላቸውም፡፡ ወጥ የሆነ መመሪያ ይሰጠን ህፃናት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የመሥራት ሁኔታ አይታይም ወዘተረፈ በማለት ከተሰብሳቢዎቹ የተለያየ አስተያየትና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ይህንኑ መነሻ በማድረግ ብፁዕነታቸው የሚከተለውን አባታዊ መልእክትና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሰንበት ት/ቤት ራሱን የቻለ ተቋም ነው ስለዚ ለሰንበት ት/ቤት ሌላ ማህበራት አያስፈልጉትም፡፡
በመሠረቱ ማህበራት የተለያየ ታሪካዊ አነሳስ አላቸው፡፡ በመሆኑም ሰንበት ት/ቤቶች እየታደከሙ ማህበራት እየተስፋፉ ናቸው፡፡
ማህበራት በሰንበት ት/ቤቶች ሥር ናቸው ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖአል፡፡ ማህበራት በሕግ ሥር ካልሆኑ ጉዳታቸው ሊአመዝን ይችላል፡፤ ሰንበት ት/ቤቶችን ለማጠናከር የማያቋርጥ ትግል እናደርጋለን፡፡ አንድነቱም ጠንክሮ ሊሠራ ይገባዋል መመሪያ እያራርቀንም ነገር ግን የተራራቅነው እኛው ራሳችን በፈጠርነው ችግር ነው፡፡
በአድባራቱና በየገዳማቱ የነበሩትን ችግሮች አብዛኛዎቹን አስወግዶናል፡፡ ቀሪዎችንም ችግሮች ለመፍታት ጥናት እያደረግን ነው ያለነው፡፡
ስለዚህ ወጣቶች በትዕግስት መጠበቅ አለባቸው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ ብሎ እንዳስተማረን በጥበብና በየዋህነት ማገልገል አለብን ድርሻዎቻችንን አውቀን መስራት አለብን በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ መልእክትና አባታዊ መመሪያ ካስተላለፉ በኋላ የዕለቱ መርሐ ግብር በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቅቆአል፡፡

{flike}{plusone}