በአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም እሴት ግንባታ በሚል ርዕስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የቆየ የአሰልጣኞች ስልጠና ተካሄደ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስና የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን እና የተለያዩ የቤተ እምነት ተወካዮች በተገኙበት ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም ስልጠናው ተጀምሮአል በአሠልጣኞች ስልጠና ጉባኤ ላይ የሰባት የተለያዩ የቤተ እምነት ተወካይ አባላት የሥልጠናው ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡
የአሠልጣኞች ስልጠና መርሐ ግብር የተመራው በክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ ባላይ መኮንን ሲሆን በጉባኤው መክፈቻ ወቅት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ስልጠናውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት ‹‹ እያንዳንዱ ሃይማኖት ሥርዓት ሰላምን ይሰብካል የህዝቦች መፈቃቀር ፀንቶ እንዲኖር ያስተምራል ዛሬ እኛ በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኘነው በሙሉ ከእግዚአብሔር አምላካችን ሰላምን የተማርን በመሆኑ ሰላምን ልንሰብክ ይገባል፡፡ ሰላም ካለ ደስተኞች አንሆናለን ከእኛም አልፎ ዕፀዋትና አዝርዕት በሰዎች ሰላም እንክብካቤ ሊገኙ ይችላሉ፡፡
በሀገራችን ያለው ሰላም ትልቅ ሥፍራ አለው በእየምነታችን ሁላችንም የምንሠራው የሰላም ጉዳይ እንዳለ ሆነ በጋራ ሆነን ደግሞ ለሀገራችን ሰላም፣ብልፅግና በመመካከር ልንሰራ ይገባል፡፡ ሀገራችን የጋራችንና የሁላችንም ናትና፣ ስለዚህ  ወደ ሕዝቡ የምንገባውና የምንደርሰው እኛ እንደመሆናችን መጠን ሕዝባችን የሚፈልገውን ይህንን ሰላም ልንሰጠውና በዚህ ጉዳይ ላይ ልንሠራና ሕዝባችንን ወደ ልማትና ወደ ዕድገት፣ወደ መተሳሰብ ልናመጣው ይገባናል በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመቀጠልምም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ ቤተ እምነት ተወካዮች በሰላምና በልማት ዙሪያ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የጉባኤው አስተባባሪ የሆኑት ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የስልጠናውን አላማና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እምነት ተቋማት  ተወካዮች እያከናወኑት ስለሚገኘው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ አስመልክቶ  ሰፋ ያለ መግለጫና ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ የጉባኤው በይፋ መከፈቱን እንዲአበሥሩና የመክፈቻ ንግግርም እንዲአደርጉ የከንቲባ ተወካዩን በመጋበዝ ጉባኤው በይፋ እንዲጀመር አድርገዋል፡፡
ከመክፍቻ ንንግግር በመቀጠል የሃይማኖት መሠረታዊ የጋራ ዕሴቶች እና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሃይማኖት አንጻር በሚል አርዕስት ስልጠናው የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት ገንቢና አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን በመስጠት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ መልሶችንና ግንዛቤ ያገኙ ሲሆን በስልጠናውም የተገኘው የግንዛቤ ማስጨበጫ ዕውቀት ለህብረተ ሰቡ ጠቃሚ በመሆኑ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በመግልፅና ይህንን የተቀደሰ ጉባኤ ያዘጋጀውን ክፍል በማመስገን መርሐ ግብሩ ተጠናቅቆአል፡፡

{flike}{plusone}