ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም የዘመን መለወጫ መልእክት አስተላለፉ
መልእክት ዘእምኅበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ ርእሰ ዓውደ ዓመት ዓቢይ ዘዕሥራ ምእት ወሰብዓቱ ዓመተ ምሕረት፤
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
• በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
• ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
• የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
• በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
• እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤
የመልካም ስጦታ ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ከ2006 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ ወደ 2007 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ፡፡
‹‹ ወዓመቲከኒ ዘኢየኃልቅ፤ ዘመንህም አያልቅም (መዝ 101÷27)
ሁሉን ፈጥሮ የሚመግብ እግዚአብሔር አምላክ በባህርዩ ፍጹም ነውና በእርሱ ዘንድ ኅልፈት፤ መለወጥ፤ ማርጀትና የዘመን ፍጻሜ የለም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እርሱ ራሱ ወደር የሌለው ብርሃን ነው፣ የሚገለጽበት ዓለምም በሚያስደንቅ ብርሃን ያሸበረቀና ጨለማ የማይፈራረቀው በመሆኑ ዘመን አይቆጠርለትም፡፡
በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የምናየው የዘመናት ኅልፈትና መተካት፣ ኃላፊው የብርሃን ዑደት ከጨለማ ጋር እየተፈራረቀ የሚፈጥረው ሂደት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስቀመጠውና እኛም በዓይናችን የምናየው ነው፤ (ዘፍ 1÷14-19)
የምንኖርበት ዓለምና ከእርሱ የወረስነው ሁሉ ኃላፊ እንጂ ቀዋሚ ባለመሆኑ ዘመን ጨምሮ ሁሉም ሲያልፍና ሲተካ እናያለን፡፡
የመንፈሳውያን ፍጥረታት መኖሪያ የሆነው ብርሃናዊው ዓለም ግን ዘመን የማይቆጠርለት፣ ኅልፈትና ውላጤ የሌለበት፣ ጨለማ የማይፈራረቅበት፣ የብርሃናት ዑደት የማይታይበት ነው፣ ነዋሪዎቹም እንደዚሁ የማያልፉና የማያረጁ፣ ዘመንም የማይቆጠርላቸው ቀዋሚና ዘላለማዊ ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡
በኃላፊው ዓለም ያሉና በብርሃናት ዑደት ምክንያት የሚቆጠሩ ዘመናት ኃላፍያን ቢሆኑም፣ በእነርሱ መሣርያነት ዘመን ወደማይቆጠርለትና ወደ ማያልፈው ብርሃናዊ ዓለም ሊያደርስ የሚችል ሥራ መሥራት ስለሚቻል፣ ዘመናት በሰው ልጅ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡
የሥራው ዓይነት የተለያየ ቢሆንም፣ ሁለቱም ዓለማት የሚያመሳስላቸውና አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ሥራ ነው፤ በሁለቱም ዓለማት ያሉ ፍጡራን በሥራ ተጠምደው እንዲኖሩ እግዚአብሔር ፈጥሮአቸዋል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ሥራ የመንፈሳዊም ሆነ የሥጋዊ ሕይወታችን መድኅን ነው፣ ለሥራ የተፈጠርን ስለመሆናችን አካላችንና ባህርያችን ራሱ ይመሰክራል፣
አፍአዊ አካላችንም ሆነ ውሣጣዊ ባህርያችን ሥራን ካልሠራ ሰላምና ጤና አያገኝም፤ እግዚአብሔር አምላክ ለሥራ የሚያገለግሉ ውጫዊ መሣሪያዎችን በብዛት ሰጥቶናል፡፡
ከሰጠን ብዙ ስጦታዎች አንዱና ዋነኛው ዘመን ነው፤ ሥራን መሥራት የምንችለው በዘመን ውስጥ ሆነን ነውና ጊዜን በሥራ መጠቀም ትልቅ ብልህነት ነው፣
ዘመን በሥራ ከምንቀድመው በቀር ሮጦ የማይደክም ፍጡር ስለሆነ ለአፍታ እንኳ የማናስቆመው ነገር ነው፡፡
ስለሆነም ጊዜን ለሥራ የማንጠቀም፣ ይልቁንም በተራ ነገርና በአሉባልታ፣ በነገር ትብትብና በጠማማ አስተሳሰብ ጊዜን የምናባክን ከሆነ፣ በአንገት ላይ ሰይፍን እንደመሳብ ይቆጠራል፣
የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው የሥራን ክቡርነት ጠንቅቀው በመረዳታቸው እስከዛሬ ድረስ የዓለም ጠበብቶች ሊደርሱበት ያልቻሉ ጥበባዊ ሥራን ሠርተው እንዳስረከቡን በእጃችን ያለ ውድና ብርቅ ቅርስ ምስክር ነው፡፡
በመካከሉ በተፈጠረው ክፍተት ጥበባዊ ሥራችንና ሥልጣኔአችን ለተወሰነ ጊዜ ቆም ቢልም፣ አሁን በአዲስ መንፈስ እየተጋጋለና እየተቀጣጠለ መታየቱ እጅግ የሚያስደስትና የሚያኮራ ነው፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት አጥታው የነበረው ይህንን ዕሤት ነው፤
አሁን የሕዳሴ ዘመን ተበሥሮአል፤ ልማቱና ዕድገቱ በሁሉም መስክ በዐራቱም መዓዝን ተጧጡፎአል፣ ይህ የእግዚአብሔር በረከትና ስጦታ ነው፣ ሕዝባችንም ይህ ዕድል እንዳይቀለበስ አጥብቆ መንከባከብና መጠበቅ አለበት፡፡
ሕዝባችን ከልማት፣ ከአንድነት፣ ከሰላምና ከእኩልነት የተሻለ ሌላ ጠቃሚ ነገር ሊኖረው አይችልም፡፡
ስለሆነም በአዲሱ ዘመን ጅምር የልማትና የሰላም ሥራዎቻችንን ከግብ በማድረስ፣ አዳዲስ የልማት ሥራዎችንም በመጀመር የሀገራችንን የሕዳሴ ጉዞ ማፋጠን አለብን፡፡
የተጀመረው የልማትና የዕድገት ሥራ ሁሉ ግቡን ሊመታ የሚችለው ሰላም፣ ፍቅር ስምምነት፣ አንድነት መቻቻል፣ መከባበር፤ ፍትሕና እኩልነት የነገሠበት ማኅበረ ሰብ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም እያንዳንዱ ቅን ዜጋ ይህንን በመገንባትና በማስጠበቅ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሠርቶ ከመልማት በቀር ሌላ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም፡፡
በመጨረሻም
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በጤናው ዘርፍ በተለይም በእናቶች የጤና እንክብካቤ፣ በአካባቢያዊ የሰላም ጥበቃ፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ አሰጣጥ ወዘተ በመሳሰሉት ዓበይት ተግባራት እየፈጸመችው ያለ ተግባር ኢትዮጵያ ሀገራችን በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት በእጅጉ የሚያሳድግና መልካም ገጽታችንን የሚያጎላ መሆኑን የተገነዘብንበት ወቅት በመሆኑ ሕዝቡ በቀጣዩ አዲስ ዓመትም ይህንን አጠናክሮ እንዲቀጥልበት መልእክታችንን እናስተላልፋለን፣ አዲሱን ዓመት የሰላም፣ የልማትና የዕድገት ዘመን ያድርግልን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መስከረም 1 ቀን 2007 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
{flike}{plusone}