በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የጋብቻ እና የቤተሰብ የምክክር አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተዘጋጀ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች አይ ቪ ኤድስ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ መምሪያ የልጅ አገረዶች እና ሴቶች ድህንነት ፕሮጀክት የመንፈሳዊ ጋብቻ እና የቤተ ሰብ ምክክር አገልግሎት መስጫ ሞዴል ማዕከል በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ግቢ በማዘጋጀት ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የክፍላተ ከተማ ቤተክህነት ተወካዮች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር ዕንግዶች የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ደብር መዘምራን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣች በተገኙበት ተከፍቷል፡፡
ማዕከሉ በተመረቀበት መርሐ ግብር ወቅት ቀሲስ ሶምሰን የማዕከሉን ዓላማ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከተቋቋመ አርባ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ ልማት ኮሚሽኑ የቤተክርስቲያንዋ የልማት ክንፍ በመሆን በሀገራችን የመጀመሪያው ነው፡፡ የቤተክርስቲያንን መዋቅር ተከትሎ በርካታ የልማት ሥራዎችንም እየሠራ ነው፤ ከልማት ሥራዎቹ መካከል ቤተሰብን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ ፈታኝ የሆነ ወቅት በመሆኑ ቤተሰብ ካልተጠበቀ የቤተክርስቲያንም ህልውና እየተሸረሸረ ሊሄድ ችሏል፡፡
ይህንን ለመጠበቅ እና ሀገርም ባለችበት እንድትቀጥል ለማድረግ ማህበረሰብ ወሳኝ በመሆኑ ይህንን በተመለከተ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጥቅምት ሁለት ሺህ ስድስት ጀምሮ የልጃገረዶች እና ሴቶች ደኅንነት ፓሊሲ በሚል ከኖሮይ ቤተክርቲያን ተራድኦ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ አስራ ስድስት አጥቢ አብያተ ክርስቲያናትን፣ በልደታ እና ቂርቆስ እንዲሁም አራዳ ክፍላተ ከተሞች ላይ ካህናትን የአሰልጣኞች ስልጠና እና ልዩ ስልጠና ለሰንበት ተማሪዎች እንዲሁም በኮሌጆች ለሚገኙ መምህራን እና ተመራቂ ተማሪዎች፣ ለአምስት ሶስት እና ሁለት ቀናት ተከታታይ ስልጠና ተሰጥቶአል፡፡ በተለይም ባለፉት ጊዜያት በጠቅላላው ለአንድ መቶ ሶስት ካህናት እና ለሃያ ስድስት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ለሃያ ሰባት ከቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ እና ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጆች ለተውጣጡ መምህራን እና ተመራቂ ተማሪዎች ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ ጋብቻ የተባረከና የተቀደሰ መሆኑን በማሳወቅ፣ ከጋብቻ የሚገኙ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ካህናት ዲያቆናት ሁሉ ጭምር የሚገኙበት በመሆኑ ይህንን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ስለሆነ በተለይ ካህናት የንሰሐ ልጆቻቸውን ሰብስበው ማስተማር ብቻ ሳይሆን በየቤታቸው በመሄድ እንዲአስተምሩ፡፡ በቤተክርስቲያን በሚከፈተው ማዕከል ተገኝተው የምክር አገልግሎት እንዲሰጡ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዓለም ወደ አንድ መንደር መጥታለች ኢንተርኔቱ እንደ ልብ ነው፡፡ ኢንተርኔቱ ትምህርት ብቻ አይደለም የሚአስተላልፈው ኃጢአትም ጭምር ነው፡፡ በሌላ መልኩ መረጃ በፍጥነት እየተላለፈ ነው ያለው፡፡
በሰንበት ት/ቤት የሚገኙ ወጣቶቻችን በትክክል ሕይወታቸው እየተመራ ነውን? ክትትልስ እየተደረገ ነውን? የንሰሐ ልጆችስ በትክክል እየተማሩ ነውን? እውነት አሁንስ ጸሎተ ተክሊል እየተካሄደ ነውን? በአብዛኛው የምናየው በማዘጋጃ ቤት የሚካሄድ ጋብቻ ነው ያለው በአስራ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አራት የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በተደረገ ጊዜ ከሚጋቡ ኢትዮጵያውያን መካከል በመቶ ሰላሳ ይፋታሉ ይላል፡፡ ይህ የሚአመለክተው ለወደፊቱ ፍቺ የጸና ጋብቻ እየቀረ መሄዱን ነው፤ ይህ አደጋ ነው ፡፡
ስለዚህ ይህንን አደጋ ለመከላከል የልማት ኮሚሽን የመንፈሳዊ ጋብቻ እና የምክክር አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ ጥረት ያደርጋል፡፡ በተለይም በፕሮጀክት የታቀፉ አስራ ስድስት አጥቢያ ላይ ወጣቶች እራሳቸውን እንደጠበቁ ቅድመ ጋብቻ የምክክር አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ ካህነት የንሰሐ ልጆቻቸውን መምከር ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ ካልሆነ ግን የሚመጣው ፈተና እጅግ ከባድ ነው፡፡
ስለዚህ ችግሩን ለመግታት ራዕይ ያላቸው መሪዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዛሬ ቆም ብለን ለነገ ካላሰብን እግዚአብሔር ይጠይቀናል፡፡ ስለዚህ ከጥያቄ ለመዳን ዛሬ መሥራት አለብን፡፡ ሥነ-ተዋልዶንም ስንመለከት ለወጣቶች የተዘጋጀ የምክክር አገልግሎት የለም፤ ቤተክርስቲያናችን ከስድስት ነጥብ ሳበት ሚሊዮን ያላነሱ ወጣቶች አሉአት ማለትም ዕድሜአቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ፡፡ የእናቶችን ቁጥር በተለያዩ የጽዋ ማህበራት ስንመለከት አስር ሚሊዮን የሚደርሱ እናቶች፣ በድዋ ማህበራት እንደታቀፉ ጥናቱ ያመለክታል፡፡
ስለዚህ እነዚህን እናቶች ማነው እየተከታተለ ምክር የሚሰጣቸው? ማን ነው ትዳራቸው እንዲጠበቅ የሚአግዛቸው? ማን ነው ጾታዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሚከላከልላቸው? ለዚህ ብቸኛ ባለቤት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ እኛም ኃላፊነታችንን ለመወጣት ቅዱስ እስጢፋኖስን መርጠናል፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስን የመረጥነው የቅዱስ እስጢፋኖስ አገልግሎት ከማስተባበር እና ቤተሰብን ከመምራት የተያያዘ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ስምንት ላይ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስምንት ሺህ የማኅበር አባላት ይመራ ነበር፡፡ ማኅበሩም ወጣቶች፣ እናቶችና ጎልማሶች ያሉበት ነበር፡፡ ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተደብድቦ ሰማዕትነቱን ከፈጸመ በኋላ እነዚያ ሲመራቸው የነበሩ ስምንት ሺህ የማኅበር አባላት በወንጌል ጨውነት ዓለምን አጣፍጠዋታል፡፡
ስለዚህ ቅዱስ እስጢፋኖስ ይህንን ሥራ የሠራ የሃይማኖት ምሰሶ ስለሆነ ነው፡፡ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያንን ለማዕከልነት ከመረጥንበት ምክንያት አንዱ ለመቶ ዓመት ሁለት ዓመት የቀረው ጥንታዊ እና ለከተማችን ማዕከላዊ የሆነ ደብር ስለሆነ ነው፡፡ መሪዎች የሚአልፉበት መስመር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ደብር የማዕከል ሞዴል እንዲሆን ተመርጦአል፡፡
በመቀጠልም ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የማዕከሉን መመስረት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ሚና አስመልክተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እግዚአብሔር አምላክ አዳምን እና ሄዋንን በገነት የፈጠራቸው እንዲበዙ፣ ምድርንም እንዲሞሉ፣ በንሕጽና በቅድስና እንዲኖሩ፣ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲአመልኩ፣ በደስታ እና በምቾት እንዲኖሩ ነው፡፡
ስለዚህ የልማት ኮሚሽናችን አሁን እየሠራ ያለው የቤተክርስቲያንን ተልዕኮ ነው፡፡ ሰዎች በሕግ የሚጓዙ ከሆነ ራሳቸውን ያስከብራሉ፡፡ በምቾትና በደስታ ይኖራሉ፤ ሕግን ያላከበሩ ሰዎች ስቃያቸው የበዛ ነው፤ እስር ቤት ባይገቡም በድንጋጤ፣ በፍርሐት ነው የሚኖሩት፤ የሥጋዊ ዕድሜአቸውም አጭር ነው፤ አዳምና ሄዋን በገነት ሕግን አክብረው እንዲኖሩ የተሰጣቸው ፀጋ ተገፎ ራቁታቸውን መሆናቸውን የተራዱት እና ፍርሐት የመጣባቸው ሕግን ስለጣሱ ነው፡፡
እኛም በዚህ ዓለም ስንኖር ሕግን አክብረን ከኖርን የምንኖረው ኑሮ የደስታ ኑሮ ነው፡፡ ሰዎች በዚህ ዓለም ሲኖሩ በትልቅ ወንበር ላይ ሲቀመጡ ምቾት ያላቸው ይመስለናል፤ ምቾት እሱ አይደለም፡፡ ምቾት የሚሰጠው መልካም ሥራ ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ በቅድስና በንጽሕና ተጠብቆ መኖር ሲቻል ነው፡፡ ሴት ከባሏ፣ ወንድም ከሚስቱ ጋር ጸንቶ የሚኖር ከሆነ ጤናማ ኑሮ ይኖራል፡፡ ዕድሜአቸውም ረጅም ይሆናል፡፡ የሚወልዷቸውም ልጆች የተባረኩ ይሆናሉ፤ በርካታ ፎቆችን የሠሩ ሰዎች ምቾት መስሎአቸው ሶስት እና አራት ሚስቶችን ሲአገቡ ከአንዷ ጋር እንኳን መኖር አቅቶአቸው አልፈዋል፡፡ በአንድ ሚስት ጸንተው የሚኖሩ ግን እስከ 80 እስከ መቶ ዓመት ይኖራሉ፡፡
ስለትውልድ ስናስብ ከሴቶች እና ከልጅ አገረዶች መጀመሩ አግባብነት አለው፡፡ ይህ ማዕከልም የተመሠረተው ትውልድ እንዲቀጥል በማሰብ ነው፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ማለት ጽ/ቤቱ ሳይሆን የአዲስ አበባ አድባራት፤ ገዳማት፤ ምዕመናን ናቸው፡፡ ልማት ኮሚሽን ፕሮግራም በመቅረጽ እና በማስተባበር እንጂ ዋናው ተልእኮ የእኛ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እናንተ የምትነበቡ ፊደሎች ናችሁ እንዳለ ካህናት፣ ልጆቻችንን ማስተማር አለብን ብለዋል፤
በማያያዝም ms. Insunn Brand voll የተባሉት የኖሮይ ቤተክርስቲያን ወኪል በበኩላቸው በዚህ ጠቃሚ መድረክ ስለተገኘሁ ደስተኛ ነኝ፡፡ በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያለው አንድነት ማለት መከባበር ነው፡፡ ይህንን ነው የሰው ልጅ ሉአላዊ ክብር የምንለው፡፡ ይህንን መከባበር ነው ለልጆቻችን የምናስተምረው፡፡ ለማህበረሰቡም የምናስተምረው ይህንን ነው፡፡ ልጆችም ከዚህ መከባበር ነው የሚማሩት፤ መከባበር የምንለው ለሌሎች ክብር መስጠትን ነው፡፡ የዚህ ማዕከል ጠቀሜታን ወደ ፊት ማየት እፈልጋለሁ፡፡
ዛሬ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ ካሉ በኋላ ለማዕከሉ የተዘጋጀውን ጽ/ቤት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ሪቫኑን በመቁረጥ በይፋ መርቀው ከፍተዋል፡፡ {flike}{plusone}